News

በኦዲት ተደራጊ ተቋማት ላይ ለሚደረገው የክትትልና የቁጥጥር ስራ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ተጠየቀ

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከኦዲት ግኝት ባለድርሻ አካላት ጋር በ2009 በጀት አመት የጋራ አፈጻጸምና በ2010 በጀት አመት እቅድ ዙርያ ጥቅምት 29፣ 2010 ዓ.ም ውይይት አደረገ፡፡

በውይይቱ መክፈቻ ላይ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሪት ወይንሸት ገለሶ በ2008 በጀት አመት በመንግስት አስፈጻሚ አካላት ዘንድ የግልጽነትና ተጠያቂነት አሰራርን ለማስፈን የኦዲት ግኝት ባለድርሻ አካላት የጋራ መድረክ መመስረቱንና በ2009 በጀት አመት ወደስራ መግባቱን አስታውሰው ውይይቱ በጋራ መድረኩ የ2009 በጀት አመት አፈጻጸም ላይ በተዘጋጀው መነሻ ጽሁፍና በ2010 እቅድ ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል፡፡

በቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ በተከበሩ ወ/ሮ ሶፍያ አልማሙን በቀረበው መነሻ ጽሁፍ አስፈጻሚውን አካል ከመከታተልና ከመቆጣጠር አኳያ በ2009 በጀት አመት በቋሚ ኮሚቴውና በጋራ መድረኩ አባል መስሪያ ቤቶች የተሰሩ ስራዎች ጥንካሬና ድክመት እንዲሁም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ቀርበዋል፡፡

በበጀት አመቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በ16 የሂሳብና 10 የክዋኔ በድምሩ በ26 ኦዲቶች ላይ ይፋዊ የህዝብ ውይይት መድረኮች መካሄዳቸው፣ በነዚህ መድረኮች አብዛኞቹ ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውና ስለ ኦዲት ተደራጊ መ/ቤቶቹ መረጃ በመስጠትና ሊወሰዱ ስለሚገቡ እርምጃዎች በማመላከት ገንቢ ሚና መጫወታቸው እንዲሁም መድረኮቹ ባለድርሻ አካላቱ በተገኙበት በጋራ በመከናወናቸው በተወሰኑ መ/ቤቶች ውስጥ በኦዲት ሪፖርቱ መነሻነት በተሰጡ የእርምት አስተያየቶች ላይ እርምጃ የመውሰድ አሰራር እየተሻሻለ መምጣቱና የኦዲት ተደራጊ ተቋማቱ አመራሮች ለመ/ቤታቸው የውስጥ ኦዲት ቁጥጥር ክትትልና ድጋፍ የሚሰጡበት አግባብ እየተጠናከረ መምጣቱ በጠንካራ ጎን ተነስተዋል፡፡

ከነዚህ በተጨማሪም ባለድርሻ አካላት የተሳተፉባቸው የመስክ ክትትልና ቁጥጥር ስራዎች በአስራ ሶስት ዩኒቨርስቲዎች ላይ መሰራቱና ዩኒቨርስቲዎቹ ያሉባቸውን ችግሮች ለቀጣይ ውይይት መለየት መቻሉ እንዲሁም የመንግስትም ሆነ የግል ብዙኃን መገናኛዎች ለይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባዎች  የሚሰጡት የሚድያ ሽፋን እየተሻሻለ መምጣቱ ህዝቡ በመንግስት የገንዘብና የንብረት አጠቃቀም እና በክዋኔ ኦዲት ላይ ግንዛቤ እንዲኖረው ማስቻሉ በጥንካሬ ተነስተዋል፡፡

በአንጻሩ ግን አንዳንድ ባለድርሻ አካላት ለአብነትም የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን፣ አንዳንዴም የትምህርት ሚኒስቴርና የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባው ላይ አለመገኘት፣ የተገኙ ባለድርሻ አካላትም ስለ ኦዲት ተደራጊው መ/ቤት በቂ መረጃ ሳይዙ መምጣትና በቂ ተሳትፎ አለማድረግ፣ በቋሚ ኮሚቴው በኩልም ለባለድርሻ አካላት በትክክል ጥሪ ያለማድረስና የኦዲት ግኝት የተገኘባቸው ተቋማትን ማዕከል በማድረግ የህዝብ ክንፍ አካላትን ለይቶ በኦዲት ባለድርሻ መድረኮች ላይ በማሳተፍ ረገድ ጉድለት መኖሩ እንደድክመት ተጠቅሰዋል፡፡  

ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ መ/ቤቶች በይፋዊ ውይይቶች የሚሰጣቸውን አስተያየትና አቅጣጫ ተቀብለው እርምጃ በመውሰድ ላይ ጉድለት ቢኖርባቸውም በዚህ ረገድ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር ውስነት ያለበት መሆኑ እንዲሁም በመድረኮቹ የሚሰጡ አቅጣጫዎችን የተመለከተ መረጃ በተገቢና በተሟላ ሁኔታ ለህዝብ በማድረስ ረገድ የሚድያ ሽፋን በመስጠት በኩል እጥረት መታየቱ ተገልጿል፡፡

ከዚህ በመነሳት ሁሉም የባለድርሻ አካላት በ2009 በጀት አመት በተጀመረው መሰረት በይፋዊ መድረኮችም ሆነ በመስክ የክትትልና የቁጥጥር ስራ ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ ማድረግ በተለይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ችግሮች ላይ ጥናት ያካሄደው ኮሚቴ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያስገኝና ችግሩ እንዲፈታ ማስቻል ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መሀከል ተጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ሌላም የመድረኩ አባላት በኦዲት ግኝቶቹ ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ በመረጃ የተደገፈ፣ አቅጣጫ አመላካችና ለእርምጃ አወሳሰድ ጠቃሚ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ከተቋማቸው ተልዕኮ አኳያ በኦዲት ግኝት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ሚናቸውን የለየ ጠንካራ እቅድ እንዲያዘጋጁ ማድረግና ቋሚ የግምገማ ስርአትን ማበጀት ትኩረት እንደሚሹ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም እንደ ፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትና የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ያሉ ባለድርሻ አካላት ለኦዲት ግኝት ሪፖርት ክትትልና ቁጥጥር የሚያግዝ የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲሰጡ ማድረግ እንዲሁም የብዙኃን መገናኛዎች መረጃ አሰጣጥ የተደራጀ፣ ውጤታማና የልማታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታን በሚያጠናክር መልኩ እንዲሆንና ለህዝብ መረጃ በመስጠት በኩል ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እንደሆኑ ተነስቷል፡፡

በመነሻ ጽሁፉ በተነሱት ጉዳዮች ላይ ባለድርሻ አካላቱ ከመድረኩ የ2009 በጀት አፈጻጸምና ከየራሳቸው ተቋም እንቅስቃሴ ጋር በማያያዝ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት አስተያየት መድረኩ ባለድርሻ አካላት በኦዲት ተደራጊ ተቋማት ላይ የሚታዩ የኦዲት ግኝቶች ላይ መረጃ እንዲያገኙ በማስቻል  የተቋማቱን አፈፃፀም ለማገዝ፣ እርምጃዎችን ለመውሰድ ባጠቃላይም የመንግሥትን አፈፃፀም ለማሳደግ ከተልዕኳቸው አኳያ ሚናቸውን እንዲጫወቱ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡ ለዚህም  ባለድርሻ አካላቱ በዚህኛውም መድረክ ሆነ እንደአስፈላጊነቱ በይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንደሚጠበቅባቸውና በተለይ የተቆጣጣሪ አካላት የበላይ አመራሮች ከዚህ አኳያ በመድረኮቹ ላይ በመገኘት ለክትትልና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን መረጃ ማግኘት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በአቅም ግንባታ በኩልም የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን ለተቀላቀሉ  የምክር ቤት አባላትም ሆነ ለሌሎች ቋሚ ኮሚቴዎች አባላት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትና የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በጋራ መስጠት እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ባለድርሻ አካላት ከነዚህ መድረኮች እንዴት እንደተጠቀሙ ለማወቅ ከመድረኮቹ የተገኙ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ የተወሰዷቸው የእርምት እርምጃዎች ለቋሚ ኮሚቴው ቀርበው የሚገመገሙበት ሁኔታ ቢፈጠር መልካም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ቋሚ ኮሚቴው የሚያደርገው ይፋዊ ስብሰባ በመገናኛ ብዙኃን መቅረቡ ተቋማት በኦዲት ግኝቶቻቸው ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ስለሚያደርግ መጠናከር እንዳለበት ነገር ግን ሚዲያው የይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ ዜናዎችን ወቅታዊነትና የመረጃ ትክክለኛነትን ሳይጠብቅ የሚያስተላልፍበት ሁኔታ ስላለ ከሚዲያው ጋርም በዚህ ዙሪያ መድረክ ፈጥሮ መወያየት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘውም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2009 በጀት አመት በኦዲት አዘጋገብ ላይ ለሚድያ አካላት ስልጠና ሰጥቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚያስተዳድሩት ሰፊ ሀብትና የሰው ሃይል እንዲሁም በሀገሪቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ላይ ከሚያሳድሩት ከፍተኛ ተፅዕኖ አንፃር በውጤታማነት መንቀሳቀሳቸውን ማረጋገጥ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ እንዲሁም በ2010 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከኦዲት ግኝት ነፃ እንዲሆኑ ለማድረግ በመታቀዱና ዩኒቨርሲቲዎች ከኦዲት ችግር ነፃና በዓለምአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆነው ውጤታማና አምራች ሃይል እንዲያፈሩ ስለሚያግዝ የጋራ መድረኩ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከኦዲት ግኝት ነፃ እንዲሆኑ የሚበቁበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግና ለዚህም ከሚመለከታቸው አካላት በተወጣጣ አጥኚ ኮሚቴ ተቋቁሞ በተቋማቱ ችግሮች ላይ ጥናት እንደተካሄደ፤ በውጤቱም ተቋማቱ የተመደበላቸውን ሀብት የሚያስተዳድሩበት ብቃት ያለው በቂ ሰው ሀይል እንደሌላቸው እንዲሁም ተቋማቱን ለማስተዳደር የወጡ ህጎች ከሌሎች ህጎች ጋር ያልተጣጣመበት ሁኔታ እንዳለ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም እነዚህን ህጎች ማጣጣም እንደሚያስፈልግ፣ በአጠቃላይ ግን በአሁኑ ወቅት የዘርፉን አሰራር ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ እንደሆነና ይህንን ጥረት በቅርበት መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በተጨማሪም የሚኒስቴር መ/ቤቱ የውስጥ ኦዲት ዳይሬክተር አሠራሮች የኦዲት ግኝት ከመሆናቸው አስቀድሞ በፋይናንስ፣ በግዥ፣ በንብረት አስተዳደር፣ በአደረጃጀት ወዘተ. ላይ ያሉ ችግሮችን በመከላከል ላይ አትኩሮ መስራት እንደሚያሻ ገልጸዋል፡፡

የፀረ-ሙስናና ሥነምግባር ኮሚሽን የስራ ሀላፊዎች በበኩላቸው የመንግሥት ተቋማት የተቀናጀ የፀረ-ሙስና መከላከያ ስትራቴጂን እንዲተገብሩ ኮሚሽኑ በሚሰራው ስራ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን መረጃም አንደ ግብዓት ወስዶ እነደሚጠቀምና እስካሁን ድረስም ከዚህ የባለድርሻዎች መድረክ ውጪ ከመ/ቤቱ ጋር መረጃ የመለዋወጥ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ሌላም በጋራ መድረኩ አባል ለሆኑ ባለድርሻ አካላት ተልዕኮ መስጠትና አፈጻጸማቸውን ለመገምገም የሚያስችል እቅድ ማዘጋጀት እንደሚገባ፣ እንደ ፌዴራል ፖሊስ ያሉ አካላትንም በጋራ መድረኩ ውስጥ ማካተት እንደሚያስፈልግ፣ የኦዲት ግኝቶች ከአመት አመት እየጨመሩ በመምጣታቸው በኦዲት ግኝት ላይ ተመስርቶ እርግጠኛ በተሆነባቸው ጉዳዮች ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባና የጋራ መድረኩ ውጤታማነትም በተወሰደው እርምጃ መጠን መለካት እንደሚኖርበት እንዲሁም የህግ አስፈጻሚ አካላት ወደ መሬት ወርደው እንዲሰሩ አቅጣጫ መሰጠት አንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በኩል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በይፋዊ መድረኮች እንዲገኝ ጥሪ ቀርቦለት ስላለመገኘቱ መረጃ እንደሌላቸውና ተጠርቶ ያልተገኘ ከሆነ ይቅርታ በመጠየቅ ወደፊት እንደሚታረም የመ/ቤቱ ተወካይ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ መ/ቤቱ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት ጥረት እያደረገ እንደሆነና ተቋማት እንደየባህሪያቸው ያለባቸውን የኦዲት ችግር ለይቶ ለማስተካከል የተሰራ ስራ ያለ እንደማይመስላቸው ተናግረዋል፡፡ ባለስልጣን መ/ቤቱ በገቢ አሰባሰቡና በሰው ሀይል አስተዳደሩ ላይ የሚታዩ በአሰራር መደገፍ ያለባቸው አቅም የሚጠይቁ ችግሮች እንዳሉበት በመጥቀስም በነዚህ ችግሮች ላይ ተጋግዞ መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡ ከዚህ አኳያ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ገቢዎችንና ጉምሩክን ብቻ ለይቶ የሚከታተል ዳይሬክቶሬት አቋቁሞ ድጋፍ እያረገ እንደሚገኝ በበጎ ጎን አንስተዋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የስራ ሀላፊ መድረኩ ችግሮች ሳይከሰቱ ለመከላከል የሚያስችል በመሆኑ መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም መ/ቤታቸው ህግ ከማርቀቅና ከማስረጽ በተጨማሪ ለተቋማት በህግ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ የመስጠት ስራ እንደሚሰራ ገልጸው በተለይ ከውል ስምምነቶች አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ተቋማት ችግር ውስጥ ገብተው የኦዲት ግኝት እንዳይገኝባቸው እገዛ ማድረግ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ከዚህ አልፎም ተገቢ ያልሆኑ ተግባራት ሲፈጸሙ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ ህጋዊ እርምጃ እንደወሰድ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ ፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በጠቅላይ አቃቤ ህግ ለሚቀርቡለት የመረጃ ጥቄዎች ፈጣን ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰው ነገር ግን ወቅቱ ከሚፈልገው አንጻር የበለጠ ራሱን ማጠናከር እንዳለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የስራ ኃላፊ በበኩላቸው መ/ቤታቸው በተጠራባቸው መድረኮች ላይ ያልተገኘ ከሆነ ይቅርታ በመጠየቅ ለወደፊቱ እንደሚታረም ተናግረው የጋራ መድረኩ ህብረተሰቡ በመንግስት የሀብት አስተዳደር ላይ ያለው ገንዛቤ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያድግ፤ በመንግስት ላይ ያለው  እምነትም እንዲጎለብት የሚያደርግ በመሆኑ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

ቀደም ብሎ በትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው በተገለጸው ጥናት ውስጥ መ/ቤታቸው ተካፋይ እንደነበረ የገለጹት የስራ ኃላፊው በዩኒቨርስቲዎች ላይ እንደተደረገው ሁሉ በሌሎች ተቋማትም ላይ መሰል ጥናት እንዲደረግ ቋሚ ኮሚቴው እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ እንደዚሁም ኦዲት ተደራጊና አድራጊ ተቋማት በሚጠቀሙባቸው አንዳንድ ህጎች ላይ የሚታየውን አለመጣጣም ማጥራት እንደሚያሻ አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም መ/ቤቱ የተጠያቂነትና የግልጽነት መርህን ለመተግበር የሚያስችሉ እንዲሁም ወጪን ለመቀነስ የሚረዱ አሰራሮች በአስፈጻሚ አካላት ውስጥ እንዲተገበሩ ማድረግ መጀመሩን አስታውሰው እነዚህ አሰራሮች ውጤታማ እንዲሆኑ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ መገናኛ ብዙኃን ለህዝብ የሚያስተላልፉት መረጃ ላይም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ከሚድያው ጋር አብሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ጨምረው የተናገሩት የስራ ኃላፊው መ/ቤታቸው ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ጋር በመሆን የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ለሚመለከታቸው አካላት መስጠት እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

ኃላፊው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከሰው ሀይል እጥረት ጋር ተያይዞ ያለባቸውን ችግር ለመፍታት ከሚያሰለጥኗቸው ተማሪዎች መካከል ብቃት ያላቸውን በመቅጠርና በነባር ሰራተኞች  እንዲታገዙ በማድረግ ችግሩን መፍታት እንደሚችሉ እንደተገለጸላቸውና ሌሎች አስፈጻሚ አካላትም እንደዚሁ እንዲያደርጉ ውክልና እንደተሰጣቸው አስረድተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰጡት አስተያየት በጥቅሉ ሲታይ መድረኩ በ2008 በጀት አመት ከተጀመረ ወዲህ ተለይም በ2009 በጀት አመት ኦዲት ተደራጊ ተቋማትን በይፋዊ ስብሰባ በመደገፍ በኩል የተሻለ ስራ መሰራቱን ለዚህም በተለይ የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት እና የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርና የትምህርት ሚኒስቴር ለተሰራው የክትትል ስራ ድጋፍ እንደሰጡ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ግን ቋሚ ኮሚቴው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ባደረገው ይፋዊ ስብሰባ ላይ ትምህርት ሚኒስቴር የተገኘ ቢሆንም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍሎች ባሉ ዩኒቨርስቲዎች ላይ በነበረው የመስክ ክትትል ላይ አለመገኘቱንና የሚኒስቴሩ የበላይ አመራር የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንዳልሰጠ ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በተጨማሪም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመደጋገፍ በተሰሩባቸው አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ውጤት እየተገኘ እንደሆነ ገልጸው አንዳንድ ኦዲት ተደራጊ መ/ቤቶች በኦዲት የተገኙ ግኝቶችን አስቀድሞ የማረም ሌሎቹም ከድጋፍና ክትትሉ በኋላ እርምጃ የመውሰድ ሁኔታ እንዳሳዩ ተናግረዋል፡፡

ከፋይናንስና ንብረት አስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት በመድረኩ ተገኝተው በጋራ መስራት አስፈላጊነት ላይ ግንዛቤ መያዛቸው በመልካም ጎኑ እንደሚታይና የጸረ-ሙስናና ስነምግባር ኮሚሽን ተወካዮችም መድረኩን መካፈላቸው ባሉት ሁኔታዎች ላይ የጠራ መረጃ እንደሚያስገኝላቸው አክለው ተናግረዋል፡፡ በይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባም ሆነ በመስክ የክተትልና ቁጥጥር ስራዎች ላይ ሚናቸውን በሚገባ ያልተወጡ ባለድርሻ አካላትም በቀጣይ ድክመታቸውን ማስተካካል እንዳለባቸው የገለጹት የቋሚ ኮሚቴው አባላት የፌዴራል ፖሊስንም ሆነ ሌሎች ወደ ጋራ መድረኩ መካተት ያለባቸውን ባለድርሻ አካላት የማካተት ስራ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

እንደዚሁም የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት ከተቆጣጣሪነት ባለፈ የአጋዥነት ሚናውን መጫወት እንዳለበት፣ አሰራርን በሚጥሱ በተለይም የኦዲት ሪፖርት ከደረሳቸው በኋላ በ15 ቀናት ውስጥ የማስተካከያ የድርጊት መርሀግብር አዘጋጅተው ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በማይልኩና ሂሳባቸውን በወቅቱ ዘግተው ለኦዲት በማያቀርቡ አካላት ላይ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሪት ወይንሸት ገለሶ በማጠቃለያ ሀሳባቸው ቋሚ ኮሚቴው አስፈጻሚ አካላት አሰራራቸውን የሚያሻሽሉበትንና ከኦዲት ግኝት ነጻ የሚሆኑበትን ሁኔታ ለመፍጠር ድጋፍና ክትትል ማድረግና አስፈጻሚው አካል የመንግስት አሰራርንና ህግን ተከትሎ እንዲፈጽም የማገዝ ሚና ቢኖረውም ይህንን በዋናነት መወጣት ያለበት ግን ራሱ አስፈጻሚው አካል መሆኑ መታወቅ አለበት ብለዋል፡፡  

የሚድያ ሽፋንም ሆነ የመረጃ ትክክለኛነትና ወቅታዊነት ችግር እንዳለበት የተገመገመ መሆኑንና ከዚህ አንጻር የምክር ቤቱን የሚድያ ኮሙኒኬሽን ክፍል የማጠናከር ስራ መስራትና ክቡር ዋና ኦዲተሩ አስቀድመው እንደገለጹት የሚድያውን አቅም መገንባት ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ምክር ቤቱ ተቋማት የኦዲት ግኝትን መሰረት አድርገው ለምን የእርምት እርምጃ አይወስዱም የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ባለው አቅም ጥናት ለማስጠናት ማቀዱንና በጥናቱ ውስጥም ባለድርሻ አካላቱ መካፈል እንደሚችሉ የተከበሩ ወ/ሮ ወይንሸት ገልጸዋል፡፡ በስራ ላይ ያሉ አርስ በርስ የማይጣጣሙ ህጎችን በተመለከተም ለወደፊቱ የሚወጡ ህጎች እንዳይጋጩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መስራትና ችግሩ ሲያጋጥምም በቶሎ ማረም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የተከበሩ ወ/ሮ ወይንሸት ፎረሙ የጋራ ተልዕኮን ለመወጣት፣ እርምጃ ለመውሰድና ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል በመሆኑ በአመት ሶስት ጊዜ ለማካሄድ መታቀዱን ገልጸው የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የኦዲት ግኝት በተመለከተ በተካሄደው ጥናት ላይ በህዳር ወር የውይይት መድረክ ለማካሄድ መታሰቡን አሳውቀዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ በመጨረሻ የ2010 በጀት አመት እቅድን ለመድረኩ ተሳታፊዎች አቅርበው ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *