በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲት አሰራርና ኦዲቱን ለመተግበር በተዘጋጀው ማኑዋል ላይ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትና ከክልል የዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ለተወጣጡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲተሮች፣ የሌሎች የኦዲት ዘርፍ ኦዲተሮችና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከግንቦት 18-25፣ 2009 ዓ.ም በሞሞና ሆቴል ተሰጠ፡፡
ስልጠናው በእንግሊዝ መንግስት አለም አቀፍ የልማት ድርጅት (DFID) ድጋፍ የተሰጠ ሲሆን በስልጠናው መክፈቻ ላይ የተገኙት የድርጅቱ ተወካይ ሚስተር ኮንሌዝ ሄሮን ስልጠናው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲትን በዋና ኦዲተሮች መ/ቤት በተጠናከረ ሁኔታ ለማቋቋም፣ ለማስጀመርና ለማከናወን እንዲያግዝ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው ሰልጣኞች ትኩረት ሰጥተው በመከታተል ወደ ተግባር እንዲቀየር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
ስልጠናው በዋናነት በኦዲት ተቋማት ውስጥ የሚሰሩት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲተሮች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲት ምንነትና አሰራር እንዲሁም ኦዲቱን ለማከናወን እንዲረዳ በተዘጋጀው ማኑዋል ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ ስልጠናው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲተሮች የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስጋቶችን፣ መልካም አጋጣሚዎችንና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲት አካባቢዎች እንዲሁም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲት አላማንና አድማስን እንዲለዩ የሚያስችላቸውና በሚሰሩበት የዋና ኦዲተር ተቋም ውስጥ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲት ስራን ተግባራዊ ለማድረግና ስራውንም በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን የሚያግዛቸው ነው፡፡
በሀምሌ 2008 ዓ.ም የተሻሻለው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲትን እንዲያከናውን ለመ/ቤቱ ስልጣንና ኃላፊነት የሠጠ በመሆኑ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲት ሂደቱን ለማስጀመርና ለማቋቋም እንዲቻል፣ በውስጡ ያሉትን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲተሮችን አቅም በመገንባትና የተመረጡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲት አካባቢዎችን ኦዲት በማድረግ ጥራት ያለው ውጤታማ ኦዲት ማከናወን አስፈላጊ በመሆኑ ስልጠናው ልዩ ጠቀሜታ አለው፡፡
ስልጠናው በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲት ምንነት፣ ከኦዲቱ ዓለም አቀፋዊ መዋቅርና መስፈርቶች፤ ኦዲቱን ከማቋቋም፣ ከማሳደግና ከማቀድ፤ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የውስጥ ቁጥጥሮችን ከማጠናከር፣ በተለያዩ የኦዲት አካባቢዎች ላይ የመስክ ኦዲትን በዘመናዊ መንገድ በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ከማናወንና ጥራት ያለውን ሪፖርት ከማዘጋጀት ጋር የተያያዙና ሌሎች ተዛማጅ ርዕሰ ጉዳዮችን የሸፈነ ነበር፡፡
ስልጠናው ሚ/ር ፒተር ሙራይ በተባሉ የአለም አቀፍ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲት ባለሙያ የተሰጠ ሲሆን በንድፈ ሃሳብና በተግባር በተናጠልና በቡድን የተለያዩ ምሳሌያዊ ልምምዶችን በማድረግ የተከናወነ ነበር፡፡ በተሰጠው ስልጠና የተገኘውን ዕውቀትም በተግባር ለማየት ሁለት የሙከራ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲቶችን በቀጣይ 7 ወራት ውስጥ ለማከናወን ታቅዷል፡፡
በስልጠናው መዝጊያ ላይ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኢንፎርሜሽን ሲስተም ሰርቪስ ዳይሬክቶሬት ተጠባባቂ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ይግረም መንገሻ ከስልጠናው የተገኘውን ዕውቀት በተግባር በመተርጎም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲት ተጠናክሮ እንዲያድግ በማስቻል እንደዚሁም ሰልጣኞች በሚሰሩባቸው የዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ውስጥ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲትን ከማስተዋወቅ ጀምሮ ወደ ተግባር እንዲገባ በማድረግ በሚከናወኑ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲቶች (IT Audit) ተግባራት የፌዴራልና የክልል መንግስታት መ/ቤቶች፣ ተቋማትና ሌሎችም የተሻለ የመረጃ ስርዓቶች ልማት፣ ዝርጋታ፣ አያያዝና አጠባበቅ እንዲኖራቸው በማስቻል የመረጃ ሚስጥራዊነትን፣ አቀማመጥን፣ ደህንነትንና ተገቢነትን እንዲረጋገጥ በማድረግ ረገድ ሰልጣኖች የየበኩላቸውን ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡ በመቀጠልም ለዚህ ስልጠና መሳካት ከፍተኛ ትብብር ያደረጉትን DFIDን እና DAIን በተጨማሪም አሰልጣኙንና ተሳታፊዎችን ለነበረው የተሳካ ቆይታ በማመስገን የስልጠናውን ፕሮግራም ዘግተዋል፡፡
በስልጠናው ላይ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እንደዚሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከኦሮሚያ፣ ከትግራይ፣ ከአማራ እና ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስታት ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የተወጣጡ 4 ሴቶችና 8 ወንዶች በድምሩ 12 የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲተሮች፣ የሌሎች የኦዲት ዘርፍ ኦዲተሮች፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎችና የስራ ኃላፊዎች ተካፍለዋል፡፡