የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ2009- 2011 በጀት ዓመት የግሉ ሴክተር ብድር አቅርቦት፣ አጠቃቀምና አሰባሰብ አፈጻጸምን አስመልክቶ ያደረገውን የክዋኔ ኦዲት ግኝቶች መሰረት ያደረገ የመስክ ምልከታ ተደረገ፡፡
ጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መ/ቤት የተካሄደውን የመስክ ምልከታ ያደረጉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ፣የፌዴራል ዋና ኦዲተር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ናቸው፡፡
የምልከታው ዓላማ የኦዲት ግኝቶቹን መሰረት አድርጎ ቀደም ሲል በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በተደረገው ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ የተሰጡ የማሻሻያ ሀሳቦችና አቅጣጫዎች ተግባራዊ መሆናቸውን መለየትና የታዩ ለውጦችን ማረጋገጥ መሆኑ ታውቋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት መሰረት ባንኩ ከ2009- 2011 በጀት ዓመት ለግል ሴክተሩ ባቀረበው የብድር አሰጣጥና እና የብድር አሰባሰብ ስርዓት ዙሪያ ክፍተቶች መታየታቸው ተጠቅሷል፡፡
በመስክ ምልከታው ላይ በመገኘት ግኝቶቹን ለማስተካከል በተወሰዱ እርምጃዎች ዙሪያ የባንኩ አመራሮች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የማሻሻያ ሀሳቦችና አቅጣጫዎች ከተሰጡ በኋላ የባንኩ የውስጥ ኦዲት በግኝቶቹና በተወሰዱ እርምጃዎች ላይ አስፈላጊውን ፍተሻ አድርጎ አብዛኞቹ ግኝቶች መስተካከላቸውንና ቀሪ እርምጃዎችም እየተወሰደ መሆኑን ማረጋገጡን የባንኩ የውስጥ ኦዲት የስራ ኃላፊ በሪፖርት መልክ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በበኩላቸው ከይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባው በኋላ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ጋር በመመካከር በርካታ የማስተካከያ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቁመዋል፡፡
በኦዲቱ ወቅት እንደታየው ቀደም ሲል የፋይል አደረጃጀትን ጨምሮ ሌሎች የአሠራር ክፍተቶች የነበሩ መሆኑን የገለጹት የባንኩ ፕሬዚዳንት ባሁኑ ወቅት በአዲሱ የባንኩ ቦርድና የማኔጅመንት ጥረት የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በማልማትና አሠራሮችን በማዘመን ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በመስክ ምልከታው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት የሱፐርቪዥን ዘርፍ ም/ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታና ሌሎች አመራሮችም የኦዲት ግኝቶቹን መሰረት በማድረግ ቀደም ሲል በተሰጡ አቅጣጫዎች መሰረት በባንኩ እንቅስቃሴ ላይ አስፈላጊው የክትተልና የድጋፍ ስራ እየተከናወነና መሻሻሎችም እየተያዩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፋይናንስ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ሱመያ ደስ አለው እና ሌሎች የቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው በተሰጡ የማሻሻያ ሀሳቦችና አቅጣጫዎች መሰረት እየተወሰዱ ያሉ የማስተካከያ እርምጃዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቁመው ቀሪ ክፍተቶችን ለማስተካከል በዘመናዊ ቴክኖሎጂና አሠራር የታገዙ ቀጣይ እርምጃዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው ባንኩ ክፍተቶቹን ለማስተካከል እየወሰደ ያለው ተግባራዊ የማስተካከያ እርምጃ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እያደረገ ባለው የክትትል ኦዲት ውጤት በድጋሜ የሚረጋገጥ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በመስክ ምልከታው ወቅት የታዩ ጥረቶች በበጎ የሚታዩና ዕውቅና የሚሰጣቸው ናቸው ብለዋል፡፡





