በአሜሪካ የኦዲት ልህቀት ማዕከል (CAE- Center of Audit Excellency) ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከተለያዩ የስራ ክፍሎች ለተውጣጡ ሰልጣኞች ከጥቅምት 9 -15 /2015 ዓ.ም በ 4 ዙሮች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡
ስልጠናው የኦዲት ተግባር መነሻ አስከ ኦዲት ሪፖርት አዘገጃጀትና የክትትል ኦዲት ሂደት፣ የመልዕክት እና ኦዲት ሪፖርት አዘገጃጀት፣ የኦዲት ቡድን አመራር እና የውስጥ ቁጥጥር ምንነትና ሂደት የሚሉ የስልጠና ርዕሶችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ቴዎድሮስ ሽመልስ እንደገለጹት ስልጠናው በገለጻ፣ በቡድን ውይይትና በጥያቄና መልስ ተሳትፎ የተካሄደ ነው፡፡
ስልጠናው በ USAID ድጋፍ በአሜሪካ ዋና ኦዲተር መ/ቤት ስር ከሚገኘው የአሜሪካ የኦዲት ልህቀት ማዕከል (CAE- Center of Audit Excellency) በመጡ አሰልጣኞች የተሰጠ መሆኑንም አቶ ቴዎድሮስ ሽመልስ አክለው ጠቁመዋል፡፡
በስልጠናው የተሳተፉ የፌዋኦ መ/ቤት ሰራተኞች ስለ ስልጠናው ተጠይቀው በሰጡት አስተያየት ስልጠናው ለሚሰሩት ስራ ፋይዳ ያለው ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑንና በአቀራረብ ሂደቱም የረኩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከአሜሪካ የኦዲት ልህቀት ማዕከል የመጡት አሰልጣኞች ስለ ስልጠናው ሁኔታና ስለሰልጣኞች ተሳትፎ ሁኔታ ተጠይቀው በሰጡት አስተያየት ስልጠናው ለኦዲተሮች እጅግ ጠቃሚና በኦዲት ሂደት ያለውን ግንዛቤ የሚያሰፋ መሆኑን ጠቅሰው ሰልጣኞች በስልጠና ቆይታቸው በስልጠናው የቀረቡትን ፍሬ ሀሳቦች በከፍተኛ ትኩረት መከታተላቸውንና ተሳትፎዋቸውም የላቀ እንደነበር አብራርተዋል፡፡
በአራት ዙሮች ለአምስት ቀናት በተሰጠው ስልጠና በአጠቃላይ 140 የሚሆኑ ሰልጣኞች የተሳተፉ መሆኑ ታውቋል፡፡