የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በባለበጀት የመንግስት ተቋማት አሠራሮች ላይ የሚያካሂዳቸው ኦዲቶች ተጠያቂነትንና ግልጸኝነትን በማረጋገጥና ሙስናንና ብልሹ አሠራርን በመከላከል ረገድ ያመጡትን ፋይዳ ለመለየት በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ባለሙያዎች ያስጠናው ሳይንሳዊ ጥናት ውጤት ጥቅምት 8 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው የፓናል ውይይት ቀርቦ ግምገማ ተደርጎበታል፡፡
ጥናቱ የኦዲት ግኝቶችን ተከትሎ በተገቢ ህጋዊ እርምጃዎች መረጋገጥ የሚገባቸው የተቋማዊ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት አሠራሮች በውጤታማነት እንዳይተገበሩ እና የሙስናና ብልሹ አሠራር ዝንባሌዎችን በአግባቡ መከላከል እንዳይቻል እያደረጉ ያሉ ክፍተቶችም ጥልቀት ባለውና በበቂ መረጃ ታግዞ በተካሄደው ጥናት መዳሰሳቸው ተጠቅሷል፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ኃላፊዎችና ሌሎች የምክር ቤቱ አባላትን ጨምሮ የተለያዩ ቁልፍ የኦዲት ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት የፓናል ውይይት መድረክ ዝርዝር የጥናቱ ግኝቶች በጥናት አድራጊዎቹ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ለፓናሉ ተሳታፊዎች ባቀረቡት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ጥናቱ ገለልተኛ በሆነ አካል እንዲካሄድ የተፈለገበት ዋና አላማ የጥናቱን ተአማኒነት ለማረጋገጥና በጥናት ግኝቱ የሚጠበቀው መሠረታዊ ጉዳይ ከተቋማት አልፎ የሀገርና የህዝብን መሠረታዊ ፍላጎት ተገቢና ህጋዊ በሆነ የሀብት አጠቃቀም ከማረጋገጥ አንጻር ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
አክለውም የኦዲት ግኝቶችን ተከትሎ ግልጸኝነትንና ተጠያቂነትን በህጋዊ እርምጃዎች ለማረጋገጥ ስልጣን የተሰጣቸው አካላትና ሌሎች ቁልፍ ባለድርሻዎች ለተሻለ የኦዲት አሠራር ውጤታማነት በተግባር የሚገለጽ አስተዋጽኦ አስካላበረከቱ ድረስ ጥናቱ ለብቻው የሚፈለገውን ውጤት እንደማያስገኝ ገልጸዋል፡፡
ፓናሉን በንግግር የከፈቱት የመድረኩ የክብር እንግዳ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ም/አፈጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው የመስሪያ ቤቱ የኦዲት ስራዎች ተቋማዊ ግልጸኝነትንና ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አንጻር ያመጡትን ውጤት ለመለካት በገለልተኛ አካል ሳይንሳዊ ጥናት እንዲካሄድ መደረጉ ለሌሎች ተቋማትም አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን ገልጸው በጥናቱ ለተለዩ ጉዳዮች ተግባራዊነት የምክር ቤቱን ተገቢና ቁልፍ ሚና ጨምሮ የሁሉም የኦዲት ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ድጋፍ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ከ2001 ጀምሮ አስከ 2015 ዓ.ም ድረስ በነበሩት 15 ዓመታት የተካሄዱ ኦዲቶችን መሠረት አድርጎ የተካሄደው ጥናት አላማ በጥናት ግኝቶቹና በግኝቶቹ ላይ በቀረቡ አስተያየቶች መሠረት ተቋማዊ የግልጸኝነትና የተጠያቂነት አሠራር የበለጠ በማረጋገጥ እና በመላ ሀገሪቱ ከሙስናና ብልሹ አሠራር የጸዳ የመንግስት ተቋማት አሠራርን በመፍጠር ሂደት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ያላቸውን ሚና ማበረታታት መሆኑ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡
የመ/ቤቱን ስልጣንና አሁን ያለበት የኦዲት አፈጻጸም ደረጃ፣ የኦዲት ግኝቶችና በመ/ቤቱ የተሰጡ የግኝት ማሻሻያ አስተያየቶች፣ የኦዲት ተደራጊ ተቋማት የግኝት ማሻሻያ የክትትል ስራዎች፣ በኦዲቱ የተገኙ ስኬቶች፣ በባለድርሻ አካላት ሚና ላይ የታዩ ክፍተቶች፣ በኦዲት ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት የተወሰዱ ተግባራዊ እርምጃዎች እንዲሁም ኦዲቱ ተቋማዊ የግልጸኝነትንና ተጠያቂነትን ሥርዓት ለማረጋገጥ እና ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል ያመጣው ፋይዳ በጥናቱ እንዲሸፈኑና ምላሽ እንዲያገኙ የተቀመጡ መሠረታዊ ጉዳዮች እንደነበሩ ተጠቅሷል፡፡
መ/ቤቱ በህግ በተሰጡት ስልጣንና ተግባራት መሠረት የተለያዩ ኦዲቶችን እያካሄደ እንደሆነ፣ የውጭ የኦዲት ተቋማትንና አካላትን ጨምሮ ከክልል ኦዲት ተቋማት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሠራር አበረታች መሆኑ፣ በሚያካሂደው ኦዲት በመንግስት ተቋማት ላይ ግልጸኝነት፣ ተጠያቂነት እና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ቁርጠኝነት ያለው መሆኑ፣ የመ/ቤቱ አመራሮች የመ/ቤቱን ተልእኮና ህጋዊ ማእቀፍ ተረድተው በቁርጠኝነት ተቋሙን የመምራት ብቃት ጠንካራ መሆኑ፣ የፋይናሽያልና አስተዳደራዊ ነጻነትን ከማረጋገጥ አንጻር ክፍተት ቢኖርም መ/ቤቱ የአሠራርና ሪፖርቱን ለህዝብ ይፋ የማድረግ ነጻነት ያለው መሆኑ እና ሰፊ ሽፋን ያለው ኦዲት እያካሄደ መሆኑ በጥናቱ መረጋገጡ የተገለጸ ሲሆን በተለይም የኦዲት ግኝቶችን ተከትሎ ተገቢ ስልጣን ባላቸው አካላት መወሰድ የሚገባቸው ተጠያቂነትን የማረጋገጥ እርምጃዎች በሚፈለገው የቁርጠኝነት ደረጃ ላይ የሚገኙ ያለመሆናቸውን ጥናቱ ማሳየቱ ተገልጿል፡፡
የም/ቤቱን የመንግስት ተጠሪ ጨምሮ በመድረኩ የተገኙ የቋሚ ኮሚቴና ሌሎች የም/ቤት አባላት እንዲሁም ሌሎች የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች በቀረበው የጥናት ውጤት ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ አስተያየቶቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን በተለይም የመንግስት ተቋማትን የግልጸኝነትና ተጠያቂነት አሠራር ለማረጋገጥ በሚመለከታቸው አካላት መወሰድ የሚገባቸው ህጋዊ እርምጃዎች አሁን ካሉበት ደረጃ መሻሻልና መጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመው በየደረጃው የሚገኙ የኦዲት ባለድርሻ አካላት ለኦዲቱ ስራ ውጤታማነት የሚጠበቅባቸውን ድርሻ በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል፡ ፡
በፓናል ውይይቱ ከ150 በላይ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የስራ ኃላፊዎችና አባላት፣ የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግስት ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር ኦዲት መ/ቤቶች የስራ ኃላፊዎች እና ሌሎች ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
Panel Reviews Federal Auditor General’s 15-Year Impact on Governance
A high-level panel discussion convened in Addis Ababa to evaluate the long-term impact of the Office of the Federal Auditor General, Ethiopia /OFAG/work on enhancing transparency and accountability across public institutions.
The forum, organized under the auspices of OFAG, examined the outcomes of audits conducted over a 15-year period — from 2008 to 2023 — across government budget institutions. The study aimed to measure institutional progress in good governance, the reduction of corruption, and the strengthening of financial discipline.
The session was inaugurated by the Federal Auditor General, H.E. Mrs. Meseret Damtie Chaniyalew, who extended a cordial welcome to participants and highlighted the significance of evidence-based accountability in public administration. The Deputy Speaker of the House of People’s Representatives, Hon. Mrs. Lomi Bedio, delivered the opening address, commending the Office for its sustained efforts in promoting transparency and reinforcing citizens’ trust in public finance management.
The event brought together members of parliament, senior government officials, regional auditor generals, representatives from key audit stakeholders, and development partners. Researchers presented comprehensive findings from the multi-year audit evaluation, sparking interest in how auditing practices have evolved and influenced governance culture in Ethiopia.
The discussions that followed explored the implications of the findings in depth, highlighting both the progress achieved and the persistent gaps in institutional oversight. Participants underscored the importance of strengthening audit follow-up mechanisms, improving coordination among oversight bodies, and enhancing the capacity of public institutions to implement audit recommendations effectively.
The panel concluded with a consensus that the Auditor General’s sustained efforts have significantly contributed to promoting transparency and accountability within the governance system. The forum’s outcomes are expected to inform future policy directions aimed at reinforcing integrity, curbing malpractice, and fostering a culture of responsible public financial management across all sectors.

