ለፌዴራል_ዋና ኦዲተር መ/ቤት የማኔጅመንት አባላት፣ የቅሬታ ሰሚ እና የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባላት በተቋሙ እና በፌዴራል መንግስት ሰራተኞች አስተዳደር ህጎች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አወቀ ጤናው በስልጠናው መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ተቋሙ ሁለንተናዊ ሪፎርም ላይ መሆኑን አስታውሰው ምቹ የሥራ አከባቢን ከመፍጠር ባለፈ የተቋሙ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ የኮሚቴ አባላትና ሠራተኞች በሠራተኞች አስተዳደር ህጎች ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ እንዲሁም በሠራተኞች መካከል መልካም ግንኙነት ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከፍተኛ የህግ ባለሙያ አቶ ኪዳኔ አብርሃም ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የማኔጅመንት አባላት፣ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ እና የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባላት በተቋሙ የአስተዳደር ህግ እና በሲቪል ሰርቪስ ህጎች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ እንዲሁም በህግ አሰራር ስርዓት ላይ ያሉትን ክፍተቶች ለመሙላት የሚያግዝ ገለጻ አድርገዋል፡፡
አቶ ኪዳኔ በገለጻቸው ስለፌዴራል የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የሠራተኞች አስተዳደር ደንብ ቁጥር 8/2010፣ የፌዴራል መንግስት ሠራተኞች የዲስፕሊን አፈጻጸምና ቅሬታ አቀራረብ ስነ-ስርዓት ደንብ ቁጥር 77/1994 ምንነትና የህጎቹ ተደጋጋፊነት፣ ስለአስተዳደር ፍርድ ቤት፣ የዲስፕሊን ኮሚቴ እና የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አወቃቀርና ተግባር እንዲሁም የተቋሙ የበላይ ኃላፊዎች፣ ዳይሬክተሮችና ማኔጀሮች ስላላቸው ስልጣንና ኃላፊነት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በስልጠናው የተለያዩ ጥያቄዎችና ሀሳቦች ተነስተው ሰፊ ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ከመድረኩም ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡