ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ስርዓት (IFMIS) እና በኤሌክትሮኒክ የመንግስት ግዥ ሥርዓት (E-GP) አሠራር ዙሪያ ሥልጠና ተሰጠ፡፡
ከታህሳስ 08 -25 / 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በ5 ዙር በተሰጠው ስልጠና በጥቅሉ 341 የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን ስልጠናው በገንዘብ ሚኒስቴር እና በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የተዘጋጀና የተሰጠ መሆኑ ታውቋል፡፡
ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ሰልጣኞች በተሳተፉባቸው የስልጠና ቀናት የተለያዩ የፋይናንስና የግዥ ሥርዓቶችን መሰረት አድርገው የሚከናወኑ የኦዲትና ኦዲት ነክ አሠራሮችን የተመለከቱ የስልጠና ርዕሶች ተሸፍነዋል፡፡
በስልጠናው በተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ስርዓት (IFMIS) ሂሳብና አፈጻጸም ምርመራ ሥርዓት ማለትም ጄነራል ሌዠር፣ ተከፋይ ሂሳብ፣ ተሰብሳቢ ሂሳብ፣ የጥሬ ገንዘብ አስተዳደር፣ በጀት፣ ቋሚ ንብረት፣ ኢንቬንተሪ፣ ግዥ እና የሰው ሀይል አስተዳደር ስርዓት እንዲሁም በኤሌክትሮኒክ የመንግስት ግዥ ሥርዓት( E-GP) ማለትም ኤሌክትሮኒክ የመንግስት ግዥ ምዝገባ፣ ፐርቼዚንግ፣ የግዥ ዕቅድ እና ጨረታ የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች የተሸፈኑ መሆኑን ዳይሬክቶሬቱ ገልጿል፡፡
ስልጠናው በኦዲት ስራ ላይ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንና በሙያቸው ዙሪያ አዳዲስ አሰራሮችን ለማወቅ አይነተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑ ታውቋል፡፡

