የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሁሉንም አመራርና ሠራተኞች የሚያካትትና በተለያዩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክህሎቶች ላይ ያተኮረ የአንድ ወር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት ጀመረ፡፡
የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ስርዓቶች ግንዛቤ ማስጨበጫ ወር በሚል በመ/ቤቱ የኢንፎርሜሽን ሲስተም ሰርቪስ ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀው ስልጠና 19 በሚሆኑ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የስልጠና ርዕሶች ላይ አተኩሮ ከግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡
ስልጠናው በመ/ቤቱ የስልጠና ክፍሎች በገጽ-ለገጽ ወይም በመስክ ሥራ ላይ ለሚገኙ ሠራተኞች ደግሞ በአማራጭ በኦንላይን ሥርዓት በማይክሮሶፍት ቲምስ (Microsoft Teams) አማካይነት የሚሰጥ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ሰልጣኞች በተለያዩ ምድቦች በመሆን በተመረጡላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በጽንሰ-ሀሳብ እና በተግባር የተደገፈ ስልጠና እንደሚከታተሉም ተመልክቷል፡፡
ስልጠናው ከመሰረታዊ የኮምፒውተር ዕውቀትና ክህሎት ጀምሮ ሰፊና ጥልቀት ያላቸው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስስና በቀጥታ በመ/ቤቱ ሠራተኞች ስራ ላይ አጋዥ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ በመሆኑ ጠቀሜታው እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ተቋም የጎላ መሆኑን ከመ/ቤቱ የኢንፎርሜሽን ሲስተም ሰርቪስ ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡


