18ኛው የአፍሪካ የእንግሊዘኛ ተናጋሪ የዋና ኦዲተሮች ማህበር /AFROSAI-E/ የ2022 ስትራቴጂክ ሪቪው ኮንፍረንስ በጋምቢያ ብሔራዊ የኦዲት ቢሮ /NAO/ አዘጋጅነት በባንጁል- ጋምቢያ እየተካሄደ ይገኛል።
መድረኩ የአፍሪካ ሀገሮች በኦዲት ሪፖርት ዝግጅትና ትግበራ ዙሪያ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።
በመድረኩ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን በመወከል ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ከሌሎች ሁለት የመ/ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በመድረኩ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን ተሞክሮ ያቀረቡ ሲሆን መ/ቤታቸው የኦዲት ሥራውን በገለልተኝነት እና በነጻነት ከሚሠሩ ጥቂት የአፍሪካ ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች አንዱ መሆኑን እና በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓት አተገባበርም መልካም ተሞክሮ ያለው መሆኑ ገልፀዋል።
የአፍሮሳይ-ኢ ሴክሬተሪያት ሚስተር ጎርደን ካንዳሮ በኢትዮጵያ በኩል የቀረበው ተሞክሮ በሴክሬታሪያቱም እውቅና ያለውና ትክክለኛ እንደሆነ እና ሌሎች ሀገራትም ከኢትዮጵያ ተሞክሮ ሊወስዱ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
አያይዘውም በሊማና ሜክስኮ ስምምነት መስረት የዋና ኦዲተር መ/ቤት ሙያዊ ነጻነት በህገ-መንግስት፣ በአዋጅና በደንቦቻቸው ካካተቱ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ መሆንዋን ሚስተር ጎርደን ተናግረዋል።
ከግንቦት 1 – 4 ቀን 2014 ድረስ በሚቆየው ኮንፈረንስ የ26 የአፍሪካ ሀገራት ዋና እና ምክትል ዋና ኦዲተሮች እንዲሁም ሌሎች የአፍሮሳይ-ኢ ሴክሪተሪያት፣ የአይ ዲ አይ ኃላፊዎችና የኦዲት የሥራ ኃላፊዎች እየተሳተፉበት ይገኛሉ።






