News

በመ/ቤቱ የኦዲት ስራ ላይ የሚዲያ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ-* ተቋማት በኦዲት ግኝቶች ላይ ሊወስዷቸው የሚገቡ የማሻሻያ እርምጃዎችን በተመለከተ የሚዲያዎች ክትትል አስፈላጊ ነው ተብሏል

የኦዲት ተደራጊ ተቋማትን የኦዲት ግኝት ማስተካከያ እርምጃዎችን ሂደት ከመከታተልና የደረሱበትን ውጤት ለህዝብ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የሚዲያ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው ሰኔ 23 ቀን 2015 ዓ.ም _በፌዴራል_ዋና_ኦዲተር መ/ቤት ከተለያዩ የሚዲያ አካላት ለተውጣጡ ጋዜጠኞች በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡

ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት _ክብርት_ወ/ሮ_መሠረት_ዳምጤ የፌዴራል ዋና ኦዲተር የመ/ቤቱን አሠራርና የኦዲት ተግባር አወቃቀር በሚመለከት ከዓለም አቀፍ እና ከአህጉራዊ የዋና ኦዲተር ተቋማት አሠራሮችና ሞዴሎች ጋር በማነጻጸር ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

መ/ቤቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁት ሦስት የኦዲት አሠራርና አወቃቀር ሞዴሎች ውስጥ ፓርላሜንታዊ ስርዓት የሚከተሉ ሀገራት የሚተገብሩትን የ “Westminster ” የኦዲት ሥርዓት ሞዴል የሚከተልና ስልጣንና ኃላፊነቱም በተለያዩ ተቋማት ላይ ያከናወናቸውን የተለያዩ ኦዲቶች መሠረት ያደረጉ ግኝቶች ሪፖርቶችን ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ማቅረብ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የኦዲት ግኝቶቹን መሠረት ያደረጉ ደረጃቸውን የጠበቁ እርምጃዎችን የመውሰድና ተጠያቂነትን የማስፈን ህጋዊ ስልጣን የም/ቤቱ መሆኑን ጨምረው የገለጹት _ክብርት_ዋና_ኦዲተሯ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በአለም አቀፉ የኦዲት አሠራር መመሪያ መሠረት በሜክሲኮ “ዴክላሬሽን” የተጠቀሱ ስምንት አለም አቀፋዊ የኦዲት ተቋማት መመሪያዎችን ለመ/ቤቱ በህገ መንግስቱና በአዋጅ ከተሰጡት ስልጣንና ተግባራት ጋር በማሳለጥ የሚተገብር ነው ብለዋል፡፡

ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ መ/ቤቱ በተለያዩ ተቋማት ላይ ያካሄዳቸውን የተለያዩ ኦዲቶች መሰረት ያደረጉ ዋና ዋና ግኝቶችን በዝርዝር የገለጹት _ክብርት_ዋና_ኦዲተር_ወ/ሮ_መሠረት_ዳምጤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከተለያዩ ግኝቶች አንጻር ነቀፌታ የሌለበት አስተያየት የተሰጠባቸውን፣ ከጥቂት ጉድለቶች በስተቀር አጠቃላይ አጥጋቢ ውጤት የታየባቸውን፣ አስተያየት ለመስጠት ያልተቻለባቸውን እና ተቀባይነት የሚያሳጣ የኦዲት ግኝት የታየባቸውን በመለየት በአኃዛዊ መረጃ አቅርበዋል፡፡

በክብርት ዋና ኦዲተር የተሰጠውን አጠቃላይ መግለጫ ተከትሎ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት የሚዲያ አካላት ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ አንጻር የሀገሪቱን የኦዲት ስራ አወቃቀር፣ ኦዲታቸው በልዩ ኦዲት ስለሚከናወን ተቋማት፣ ከኦዲት ግኝት በኋላ በአጥፊዎች ላይ መወሰድ ስለሚገባው እርምጃና ተጠያቂነት፣ በኦዲት ሂደት ላይ ሊኖር ስለሚገባው የሚዲያዎች ሚና፣ መ/ቤቱ ከክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ጋር ስላለው ግንኙነት እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ጥያቄ አቅርበው በክብርት ዋና ኦዲተሯ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ሀገሪቱ የፓርላሜንታዊ ስርዓት ተከታይ እንደመሆኗ እንደሌሎች ይህንን ስርዓት እንደሚከተሉ ሀገራት ዋና ኦዲተር ተቋማት ሁሉ የመ/ቤቱ ስልጣንና ተግባር በእቅድ የያዛቸውን ተቋማት ኦዲት የማድረግና ግኝቶችንም ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በሪፖርት ማቅረብ መሆኑን ክብርት ዋና ኦዲተሯ በምላሻቸው ጠቅሰዋል፡፡

በመ/ቤቱና በክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች መካከል የነበረውን የኦዲት ስራ ድግግሞሽ ክፍተት ለማስቀረት በአዋጅ የተደገፈ ተግባር መከናወኑንና የክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶችን አለም አቀፋዊ የኦዲት አሠራር እንዲከተሉ ለማድረግ በሰው ኃይል አቅም ግንባታም ሆነ በቁሳቁስ ለመደገፍ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በኦዲት ግኝቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃዎች ሊወሰዱና በአጥፊዎች ላይ የተጠያቂነት አሠራርም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው በመግለጫቸው ላይ ያነሱት ክብርት ዋና ኦዲተሯ ለዚህ ተግባር ውጤታማነትም የሚዲያ አካላት የኦዲት ግኝቶች በተመዘገቡባቸው የኦዲት ተደራጊ ተቋማት ላይ በመስራትና ውጤቱን ለህዝብ ይፋ በማድረግ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *