በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አዲስ ለተቀጠሩ ሠራተኞች የ5 ቀናት የተቋማዊ ትውውቅ /Induction/ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡
በስልጠናው የማጠናቀቂያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ባስተላለፉት መልዕክት የኦዲት ሙያ በቂ እውቀትን፣ ልምድን፣ የቡድን ሥራን እንዲሁም ስነ-ምግባር የተላበሰ ስብዕናን የሚጠይቅ ዘርፍ በመሆኑ ወደ መ/ቤቱ የተቀላቀሉ አዲስ ሠራተኞችም ከስልጠና ያገኙትን እውቀት ቀጣይነት ባለው ንባብ ማጎልበት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አለም አቀፍ የኦዲት ስታንዳርዶችን ተከትሎ የኦዲት ስራውን የሚያከናውን እና ዘርፈ ብዙ እውቀት ያለበት ተቋም መሆኑን ጨምረው የገለጹት ክብርት ዋና ኦዲተሯ ሰልጣኝ ኦዲተሮች ወደስራ ሲሰማሩ በስልጠና ወቅት ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር መቀየር እና የኦዲት ስነ-ምግባር ጠብቀው መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
ሰልጣኞች በበኩላቸው ግንዛቤ ማስጨበጫው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ዓለም አቀፍ የኦዲት አሠራር ስታንዳርዶችን ተከትሎ የኦዲት ሥራውን የሚሠራ ተቋም መሆኑን የተረዱበት እንዲሁም በቀጣይም ስራቸውን በአግባቡ ለማከናወን የሚያስችል በቂ እውቀትና ግንዛቤ ያገኙበት እንደነበረ ገልፀዋል፡፡
የተቋማዊ ትውውቅ ግንዛቤ ስልጠና መርሀ ግብሩ ከግንቦት 25 – ሰኔ 2/2017 ዓ.ም ለ5 ተከታታይ የሥራ ቀናት በመ/ቤቱ የስልጠና ማዕከል የተሰጠ ሲሆን በጥቅሉ 43 አዲስ የተቀጠሩ ሠራተኞች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በየጊዜው መ/ቤቱን ለሚቀላቀሉ አዳዲስ ሠራተኞች ከስራ በፊት የትውውቅና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በቋማኒት ይሰጣል፡፡