በኢትዮጵያ መልካም አስተዳደርንና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና ያላቸው ተቋማትና አካላት የተሳተፉበት የአንድ ቀን የኮሙዩኒኬሽን ፎረም ተካሄደ፡፡
በአሜሪካ ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ልህቀት ማዕከል (CAE- Center of Audit Excellency) አዘጋጅነት ጥቅምት 14 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው ፎረም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን ጨምሮ ከዩ.ኤስ.አይ.ዲ (USAID)፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤት፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሰታዊ ካልሆኑ ተቋማት (NGO)፣ ከሲቪል ሶሳይቲ ተቋማት(CSO)፣ ከመንግስት ግዢና ንብረት ባለስልጣን፣ ከስነ-ምግባርና የፀረ- ሙስና ኮሚሽን እና ከግል የሚዲያ ተቋማት የመጡ አካላት ተሳትፈዋል።
በመድረኩ የተገኙት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ ስለኦዲት ምንነት፣ ዋናው ኦዲተር መ/ቤት ስለተመሰረተባቸው የህግ ማዕቀፎች እና መ/ቤቱ ስለሚያከናውናቸው የኦዲት አይነቶች፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ስላለው ቅንጅታዊ አሰራር፣ ከሚዲያ አካላት ጋር ስላለው ግንኙነት፣ ከክልልና ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ጋር ስላለው ግንኙነትና ቅንጅታዊ አሰራር እንዲሁም በአጠቃላይ በመ/ቤቱ አሠራር ላይ እያጋጠሙ ስላሉ ችግሮችና ችግሮቹን ለመቅረፍ እየተወሰዱ ስላሉ የመፍትሄ እርምጃዎች ሰፊ ገለፃ አድርገዋል።
በተለይም ዋና ኦዲተሯ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት የኦዲት ግኝት ሪፓርቶችን መሰረት በማድረግ እየወሰደው ስላለው እርምጃ ያብራሩ ሲሆን በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በትምህርት ሚኒስቴር፣ በፍትህ ሚኒስቴር እና በሌሎች ተቋማትና አካላት ላይ የተወሰዱ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ እርምጃዎች ይበል የሚያሰኙ እና ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በፎረሙ የተሳተፉ የተለያዩ ተቋማት ተወካዮችና አካላት መልካም አስተዳደርን እና ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አንጻር ያላቸውን ሚና እና በጉዳዩ ላይ እየሰሩ ስላሉዋቸው ሥራዎች ለመድረኩ ገለጻ አድርገዋል።
በመጨረሻም ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና ሀሳቦች ተነስተው በሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።