News

ሴቶች እድሉን ካገኙ አሁን ያላቸውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ የበለጠ ማሳደግ እንደሚችሉ ተገለጸ

በአለም አቀፍ ደረጃ ለ111ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል መሪ ቃል ለ46ኛ ጊዜ የተከበረው አለም አቀፍ የሴቶች ቀን (March-8) የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አመራርና ሠራተኞች በተገኙበት የካቲት 29 ቀን 2014 ዓ.ም  በድምቀት ተከበረ፡፡

በመ/ቤቱ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት በተዘጋጀው  የአከባበር ስነስርዓት ላይ  የተለያዩ ዝግጅቶች የቀረቡ ሲሆን በስፍራው የተገኙት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ም/ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ዕለቱን በማስመልከት ንግግር አድርገዋል፡፡

ሴቶች ቀደም ባሉት ጊዚያት ይደርስባቸው የነበረውን ጫናና ዘርፈ ብዙ ተጽዕኖ በመቋቋምና በመታገል ሀገርን እስከ መምራት የደረሱበትን ደረጃ የአለም አቀፍና የሀገር አቀፍ ተሞክሮዎችን በመጥቀስ ያስታወሱት ም/ዋና ኦዲተሯ ሴቶች እድሉን ካገኙና ሁኔታዎች ከተመቻቹላቸው አሁን እያሳዩ ያሉትን ሁለንተናዊ ተሳትፎ የበለጠ ማሳደግ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ በገጠር አካባቢ ያሉ ሴቶችን በሁለንተናዊ መልኩ የማብቃትና ህይወታቸውን የመለወጥ ሂደቱ ገና ብዙ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን አመላክተው ቀደም ካሉት ጊዜያት ጀምሮ በሀገራችን የሴቶችን መብቶች ለማሻሻል በሂደት የተወሰዱትን እርምጃዎች አስታውሰዋል፡፡ መንግስት በአሁን ሰዓት ከምንግዜውም በላይ ለሴቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎዎች ማደግ የበለጠ ትኩረት መስጠቱንና በዚህ ዕድል ተጠቃሚ በመሆንም በተለያዩ ሀገራዊና ተቋማዊ የአመራር ደረጃዎች ጭምር ሀገርንና ህዝብን እያገለገሉ የሚገኙ ስኬታማ ሴቶች መኖራቸውንም ጨምረው አስታውሰዋል፡፡ አክለውም ሴቶች በተሻለ ደረጃ ላይ ለመገኘትና የበለጠ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት እራስን ማብቃትና መብትና ግዴታን በማወቅ በተሰማሩበት የስራ መስክ ተልዕኮን ለመወጣት ዝግጁ ሆኖ በመገኘት ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በመ/ቤቱ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት ሴቶችን ለመደገፍ እየተደረጉ ያሉ አበረታች እንቅስቃሴዎችን ያነሱት ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ  በተለያዩ ገቢ ማስገኛ እንቅስቃሴዎች በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የመ/ቤቱን ሴት ሰራተኞች ኑሮ ለመደጎም እና የትምህርት ዕድሎችን በማመቻቸት የትምህርት ደረጃቸውን ለማሻሻል እየተደረገ ያለውን ጥረት በንግግራቸው አስታውሰዋል፡፡

የመ/ቤቱ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሙሉ ጥሩነህ በበኩላቸው ዕለቱን በማስመልከት ገለጻ ያቀረቡ ሲሆን በዓሉ ሴቶችና መላው የአለም ህዝቦች ድንበር፣ ዘር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ የኢኮኖሚ  ደረጃና የፖለቲካ  ልዩነቶች ሳይወስኗቸው ለፆታ እኩልነት፣ ለፍትህ ፣ ለሰላምና ለልማት በጋራ በመቆም የሚያከብሩት ነው  ብለዋል፡፡ አለም አቀፍ የሴቶች ቀን የሴቶችን ሁለንተናዊ እኩልነትንና ሰላምን ለማምጣት ትግል  ያደረጉ ሴቶችን በማሰብ  ለእኩልነት ያደረጉትን ታሪካዊ ትግል እና የከፈሉትን  መስዋዕትነት እንዲሁም በትግሉ የተገኙ ድሎችን ዕውቅና ለመስጠት የሚከበር ታላቅ አለም አቀፋዊ በዓል መሆኑንም በገለጻቸው ጠቅሰዋል፡፡

በሀገራችን የሴቶችን እኩልነት ለማስፈንና ተሳትፎአቸውን ለማሳደግ ህገ መንግስታዊ ዋስትና ከመስጠት ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን የጠቆሙት ወ/ሮ ሙሉ ሴቶች በቀዳሚነት በራሳቸው ጥረትና ቀጥሎም በሚደረግላቸው ድጋፍ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የበለጠ ለማረጋገጥ፣ ከጎጂ ባህላዊ ድርጊቶች ለመላቀቅ እና ራስን በማብቃትና ወሳኝ የአመራር ቦታዎችን በመያዝ ለሀገር እና ለህዝብ እድገት በሚደረገው ሀገራዊ ተሳትፎ የበለጠ አስተዋጽኦ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

በአከባበር ስነ ስርዓቱ ላይ የሻማ ማብራት ስነስርዓት የተካሄደ ሲሆን ዕለቱን የሚመለከቱ የጥያቄና መልስ ውድድር፣ ግጥምና  በሴቶች የተዘጋጁ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ የቤት ዕቃዎች ለዕይታ ቀርበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *