News

ሚኒስቴር መ/ቤቱ ያለበትን የመረጃ አያያዝና የመመሪያ ጥሰት ሊያሻሽል እንደሚገባ ተገለጸ

 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀድሞው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የ2012 በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ ይፋዊ የህዝብ ውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱ በ2012 በጀት ዓመት በርካታ የህግ ጥሰቶችን ከመመሪያ እና አሠራር ሥርዓት ውጪ ፈጽሞ መገኘቱ በኦዲት ሪፖርቱ ተመላክተዋል፡፡

ለአብነትም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለተለያዩ አገልግሎቶች በድምር ብር 1,932,275.90 ባላተሟላ ሰነድ ክፍያ ፈጽሞ መገኘቱ፣ ለደህንነት ካሜራ እና የጽህፈት መሣሪያ ግዢ በድምር ብር 744,042.10 በጀት ዓመቱን ያልጠበቀ ክፍያ መፈጸሙ እና ለመስተንግዶ አገልግሎት ግዥ ያለውድድር በቀጥታ ብር 189,436.28 ተፈጽሞ መገኘቱ ተጠቁሟል፡፡

ከስልክ አጠቃቀም ጋር ተያያዘም በስልክ ዝርዝር ውስጥ ላልተካተቱ ቁጥሮች በድምሩ ብር 68,062.32 ክፍያ ተፈጽሞ መገኘቱ፣ አገልግሎት ለማይሰጡ 47 የስልክና የፋስክ መስመሮች በድምሩ ብር 9,317.28 ክፍያ ተፈጽሞ መገኘቱ እንዲሁም በመ/ቤቱ የተለያዩ ኃላፊዎች የስልክ ፍጆታ ጣሪያ ካለመውጣቱም በተጨማሪ ለተወሰኑ ስልኮች ከፍተኛ የስልክ ፍጆታ ብር 2,674,450.04 ተከፍሎ መገኘቱ ተመላክቷል፡፡

ከበጀት አጠቃቀም አኳያም በመደበኛ እና በካቲታል በጀት በድምሩ ብር 123,634,679.62 ሥራ ላይ ያልዋለ መሆኑ፣ በበጀት አመቱ በድምሩ ብር 800,000.00 የበጀት ዝውውር ምዝገባ ያልተደረገ መሆኑ እና የሚኒስቴር መ/ቤቱ የሰነድ አያያዝ እና የምዝገባ ሥርዓት መረጃን በቀላሉ ለማግኘት ለማግኘት የማያስችል መሆኑ ተገልጾ የተቋሙ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቋል፡፡

የቀድሞ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የፋይናንስና ግዢ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አበራ ጎደቤ የኦዲት ግኝቱን ተከትሎ የመውጫ ስብሰባ መደረጉን አውስተው በሪፖርቱ ለቀረቡት ከህግና መመሪያ ውጪ ለተፈጸሙ የኦዲት ግኝቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አቶ አበራ በማብራሪያቸው ብዙዎቹ የኦዲት ግኝቶች ከኢፍሚስ /IFMIS/ ትግበራ ጋር በተያያዘ በተቋማቸው በቂ ግንዛቤ ያልጎለበተበት ሁኔታ የነበረ በመሆኑ እንደተፈጠሩ፣ከኦዲት ግኝቱ በኋላ በግኝቶቹ ላይ በተለያየ ደረጃ የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰዳቸውን እና ከኦዲት ሪፖርቱም ትምህርት በመውሰድ በቀጣይ በጀት ዓመት ሥራዎች ላይ እንዳይደገሙ የእርምት እርምጃዎችን እየወሰዱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለበጀት አጠቃቀማቸው ዝቅተኛ መሆንም በበጀት ዓመቱ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመከሰቱ ምክንያት በዕቅዳቸው መሠረት ለማከናወን በመቸገራቸው መሆኑን አቶ አበራ ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ከሚኒስቴር መ/ቤቱ የኦዲት ግኝት ሪፖርቱን ተከትሎ የድርጊት መርሃ ግብር አለመላኩን እና ተቋሙ በኦዲት ግኝቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃ ወስጃለው ብሎ ያቀረበበት መንገድ ትክክለኛ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከመመሪያ ውጪ የተፈጸሙ ግዢዎች አግባብነት የሌላቸው በመሆኑ በህጉ መሠረት ሊፈጸሙ፤ መመሪያን ተላልፈው በተገኙ አካላት ላይም ተቋሙ እርምጃ ወስዶ ሊያሳውቅ፣ የአሠራር ሥርዓትና መመሪያ ላልወጣላቸው አሠራሮች እንዲወጣላቸው ሊደረግ እንደሚገባ የሳሰቡት ም/ዋና ኦዲተሯ የበጀት ዝውውር፣ ሞዴል አለመቁረጥ፣ የበጀት አጠቃቀም፣ የሰነድ አያያዝ አሁንም በተቋሙ ያልተፈቱ ችግሮች በመሆናቸው ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራባቸው ይገባል ብለዋል፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱ አጠቃላይ ያሉበትን የአሰራር ግድፈቶች ለመቅረፍም የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓቱን ሊያጠናክር ይገባልም ብለዋል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ በሰጡት ያማጠቃለያ ሀሳብ የኦዲት ግኝቱ ላይ የተደረገው ይፋዊ ስብሰባ ለቀጣይ ሥራቸው መሻሻል እንደሚያግዛቸው፣ በኦዲት ግኝቱ የታዩ ችግሮችን ለመፍታት ሁለቱም ሚኒስቴር መ/ቤቶች /የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና የቱሪዝም ሚኒስቴር/ በጋራ ተቀናጅተው እንደሚሠሩ፣ በ2012 በጀት ዓመት የታዩ ችግሮች ድጋሚ እንዳይታዩ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ሚኒስቴር መ/ቤቱ የሰነድ አያያዝ ላይ ያሉ መዝረክረኮችን ለመቅረፍ እንደሚሠራ፣ የበጀትና የስልክ አጠቃቀም ላይ ያሉ ችግሮችን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚያይ እና የጎላ ጥፋት በፈጸሙ ሠራተኞች ላይ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራዎች እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ስብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ ባስተላለፉት የማጠቃለያ መልዕክት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር የጋራ ኮሚቴ በማዋቀር በኦዲት የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አያይዘውም ሚኒስቴር መ/ቤቱ እስከ ሰኔ 10/ 2014 ዓ.ም የኦዲት ማስተካከያ ሪፖርት እንዲያቀርብ፣ የሰነድ አያያዙን እንዲያዘምን እና ለኦዲት ግኝቶች ተገቢውን ክብደት በመስጠት እንዲሠራ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

በሌላ በኩል የገንዘብ ሚኒስቴር ለተቋሙ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግ፣ በሁሉም ተቋማት ላይ ተፈጻሚ የሚሆን የስልክ ወጪ ጣሪያ መመሪያ እንዲዘጋጅ እና በተቋሙ የፋይናንስ ኃላፊዎች ላይ ተገቢው አስተዳደራዊ እርምጃ ወስዶ እስከ ሰኔ 10/2014 ዓ.ም ሪፖርት እንዲያደርግ ሰብሳቢው አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *