የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2014 በጀት ዓመት እና ከዚያ በፊት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ላይ ባደረገው የሂሳብ ኦዲት መሠረት እስካሁን ማስተካከያ ባልተደረገባቸው የኦዲት ግኝቶቹ ላይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባው ተገለጸ፡፡
ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በተካሄደው ህዝባዊ ይፋዊ መድረክ እንደተገለጸው ቀደም ሲል የነበሩ ግኝቶችን ጨምሮ በ2014 በጀት ዓመት በሚኒስቴር መ/ቤቱ ላይ በተደረገው የሂሳብ ኦዲት መሠረት በውሎ አበል አከፋፈል፣ በበጀት አጠቃቀም፣ በሂሳብ አመዘጋገብ፣ በመስተንግዶ ወጪ አከፋፈል፣ በተሰብሳቢ፣ በተከፋይ፣ በግዥ እና በሂሳብ ሰነድ አያያዝ እንዲሁም በንብረት አያያዝ፣ አጠቃቀምና አመዘጋገብ አሠራሩ ላይ በርካታ ክፍተቶች ታይተዋል፡፡
የሚኒስቴር መ/ቤቱን ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ በመድረኩ የተገኙ የስራ ኃላፊዎች በመድረኩ የቀረቡ የኦዲት ግኝቶች ትክክለኛ መሆናቸውን እና ከኦዲቱ በኋላ በአጥፊዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድን ጨምሮ በወቅቱ የተሰጡ የኦዲት ግኝት ማስተካከያ አስተያየቶችን መሰረት ያደረጉ በርካታ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቅሰው ከአቅም በላይ የሆኑና ቀሪ ያልተፈቱ ችግሮችን ለማስወገድ ቋሚ ኮሚቴውና ሌሎች አካላት እገዛ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሠ የሚኒስቴር መ/ቤቱን የስራ ኃላፊዎች ምላሽ መሰረት አድርገው በሰጡት አስተያየት በ2013 በጀት ዓመት በተደረገ ኦዲት የታዩና ማስተካከያ ሳይደረግባቸው በ2014 በጀት ዓመት በተደረገው ኦዲት ደግመው የታዩ ግኝቶች መኖራቸውን አስታውሰው ማስተካከያ ተደርጎባቸውል ተብለው የቀረቡ ግኝቶች በቀጣይ የክትትል ኦዲት የሚረጋገጡ ናቸው ብለዋል፡፡
በተለይም በግዥ ፣በተሰብሳቢና ተከፋይ፣ በሂሳብ አመዘጋገብ እና በሌሎች ግኝቶች ላይ ትኩረት በመስጠት አሠራርን ማስተካከል እንደሚገባ ያሳሰቡት ክቡር አቶ አበራ በንብረት አያያያዝ፣ አጠቃቀምና አመዘጋገብ ረገድ የነበሩ ክፍተቶችን ለማስተካከል ተወስዷል የተባሉ እርምጃዎችንም ማጠናከርና ቀሪ ችግሮችን ለማስወገድ ቀጣይ ጥረት መደረግ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙ የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ግኝቶችን ለማስተካከል ቀሪ የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ ያሳሰቡ ሲሆን በተለይም በመድረኩ የተገኙ የገንዘብ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ተሰብሳቢ ሂሳብ ከመሻሻል ይልቅ መጠኑ እየጨመረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በኦዲት ግኝቶቹና ከሚኒስቴር መ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች በግኝቶቹ ላይ የተሰጡ ምላሾችን አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን ከ2014 በጀት ዓመት በፊት በተደረጉ ኦዲቶች የታዩ ግኝቶች ማስተካከያ ሳይደረግባቸው መቆየታቸው ተገቢ ያለመሆኑን ጠቅሰው በተለይም በአበል አከፋፈል ላይ የታዩ ችግሮች ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ይገባል ብለዋል፡፡
ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚከፈሉ ክፍያዎች በተያዘላቸው በጀት አመት ሊፈጸሙ እንደሚገባ እንዲሁም በአመራር መለዋወጥ ሊገታ የማይገባ ቋሚ ተቋማዊ አሠራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ እና ተቋማት ሲዋሀዱና ሲለያዩ የነበሩበትን ተቋማዊ አሠራር መሰረት ያደረገ ኦዲት መደረግ እንዳለበት ጨምረው የገለጹት ክብርት ወ/ሮ መሠረት አግባብ ያልሆኑ የቀጥታ ግዥ አማራጮች መንግስት ሊያገኝ የሚችለውን ገቢ የሚያሳጡ በመሆናቸው አስገዳጅ ሁኔታ ካላገጠመ በስተቀር ግዥዎች በግልጽ ጨረታ መከናወን አለባቸው ብለዋል፡፡
በሚኒስቴር መ/ቤቱ የታየው የተሰብሳቢ ሂሳብ አሠራር ከፍተኛ ክፍተት ያለበት መሆኑንና ተከፋይ ሂሳቦችም መንገድ ተፈልጎላቸው እንዲወራረዱ አክለው የጠቆሙት ክብርት ዋና ኦዲተሯ የተቋሙ የበላይ አመራሮች ጥረትና ቁርጠኝነት ካለ ችግሩ ሊፈታ እንደሚችል የሌሎች ተቋማትን ልምድ በማንሳት አሳስበው በንብረት አስተዳደር ረገድ ሰፊ ችግር ያለ በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ ማስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የተስተካከሉና ያልተስተካከሉ የኦዲት ግኝቶች ተለይተው መቅረባቸው የሚኒስቴር መ/ቤቱ ጠንካራ ጎን መሆኑን በመጥቀስ አስተያየታቸውን የሰጡት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው የተቋሙ አመራር በተለይም በፋይናንስ አሠራሩ ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል በተደረጉ ኦዲቶች ማስተካከያ ተደርጎባቸዋል ተብለው የቀረቡ ግኝቶች ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው ምልከታ ሳይስተካከሉ መገኘታቸውን ጨምረው ያስታወሱት ም/ሰብሳቢዋ በአጥፊዎች ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች ከጥፋቱ ጋር ተመጣጣኝ እና አስተማሪ መሆን የሚገባቸው መሆኑን በመጥቀስ በመድረኩ የተሰጡ አስተያየቶችን መሰረት ያደረገ የድርጊት መርሀ ግብር እስከ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡