በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሰላም ሚኒስቴር የአርብቶ አደርና የከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ድጋፍ ኣሳጣጥን አስመልክቶ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2013 በጀት ዓመት ያካሄደውን የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት መነሻ በማድረግ ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይቱም በሚኒስቴር መ/ቤቱ በዕቅድ የተያዙ የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ማህበረሰብ ልማት ፕሮጀክቶች በአግባቡ ሲመራ አለመቆየቱን በኦዲት ሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
በዚህ የተነሳም በተለይም በአፋርና በሶማሌ ክልል ከፕሮጀክቶቹ ተጠቃሚ ከመሆን ይልቅ ነዋሪዎች በጎርፍ አደጋ ህይወታቸውን ያጡበትና እንስሳት ያለቁበት ወቅቶች እንደነበሩ ቋሚ ኮሚቴው ጠቅሶ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች በዕቅድ የተያዙ ፕሮጀክቶች በአግባቡ ያልተመሩበትን ምክንያት እንዲያብራሩ ጠይቋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙ የሰላም ሚኒስቴር አመራሮች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ለፕሮጀክቶቹ ውጤታማ አለመሆን በዋናነት የሰላም ሚኒስቴር ኃላፊነት የማስተባበር ተግባር ብቻ መሆኑንና የውሃ ሃብት ሚኒስቴር እንዲሁም የስኳር ኮርፖሬሽን ተገቢውን ኃላፊነት ባለመወጣታቸው በተጨማሪም የመብራት አገልግሎት እና የበጀት ችግሮች በማጋጠማቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ኦዲቱ የተከናወነው ለተቋሙ በተሰጡ ስልጣንና ኃላፊነቶች መሠረት መሆኑን ጠቁመው የተቋሙ አመራሮችም በኦዲቱ ለተመላከቱ ግኝቶች ተገቢውን ምላሽና ማብራሪያ መስጠት አለመቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከኦዲት ግኝቶቹም ሆነ ከተቋሙ አመራሮች ምላሽ መረዳት የሚቻለውም ፕሮጀክቶቹ ተገቢው የአዋጭነት ጥናት ተደርጎባቸው በኃላፊነት ሲመሩ እንዳልነበር መሆኑን የገለጹት ዋና ኦዲተሯ በቀጣይ ተቋሙ የኦዲት ግኝቶቹን የዕቅዱ አካል አድረጎ በመስራት ማስተካከል ይገባል ብለዋል፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት እና ባለድርሻ አካላት ተቋሙ ለኦዲት ግኝት ትኩረት ሰጥቶ አለመሥራቱን እና ተገቢ ምላሽና ማብራሪያ በተቋሙ አመራሮች አለመቅረቡን ገልጸዋል፡፡
የመስኖ እና ቆላማ አከባቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር እንድርያስ ጌታ በበኩላቸው በኦዲት ሪፖርቱ የተመላከቱ ግኝቶች ተገቢነት ያላቸው መሆናቸውን እና በቀጣይ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት ችግሮቹን ለመፍታት እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ የኦዲት ግኝቱ በአርብቶ አደሩ ስም በእርዳታ እና በተለያየ ሁኔታ የሚገኝ ሀብት ባልተገባ መንገድ እየባከነ ከመሆኑም ባለፈ ህብረተሰቡንም ለሌላ ተጨማሪ ጉዳት እየዳረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
አክለውም በኦዲት ግኝቶቹ መሠረት በአፈጻጸም ብልሹ አሠራር ምክንያት ችግሮቹ የተከሰቱባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከተጠቃሚነት አንጻር ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በእኩል እይታ ማየት ያላስቻለ ኢፍትሀዊ ተግባር መፈጸሙን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የመስኖ እና ቆላማ አከባቢ ሚኒስቴር መ/ቤት አስከ ሰኔ 25 ቀን 2014 ዓ.ም የኦዲት ማሻሻያ መርሃግብር አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ፣ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባቸው የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎችም ተለይተው አስተዳደራዊ እርምጃ ተወሰዶ ሪፖርት እንዲደረግ እና በሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚሠሩ ፕሮጀክቶች የአከባቢውን ማህበረሰብ ያማከሉ መሆናቸው እየተረጋገጠ እንዲሠራ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
በተያያዘም የፍትህ ሚኒስቴር በወንጀል የሚያስጠይቅ ድርጊት ካለ መርምሮ ክስ እንዲመሰርት፣ የስነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽንም ድርጊቱን አጥንቶ እንዲያሳውቅ እና የገንዘብ ሚኒስቴርም የበጀት አመዳደቡ ፍትሐዊ ስለመሆኑ እንዲያረጋግጥ እንዲሁም ቀደም ብለው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በልዩ ትኩረት ማጠናቀቀቅ የሚያስችል አሠራር ዘርግቶ በበጀት እንዲደግፍ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን አሳስበዋል፡፡