News

ሚኒስቴር መ/ቤቱ ህግን ካልተከተለ የሒሳብ አሠራር በመውጣት ህግና መመሪያን ተከትሎ ሊሰራ እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ህግን ካልተከተለ የሒሳብ አሠራር በመውጣት ህግና መመሪያን ተከትሎ ሊሰራ እንደሚገባም አሳሰበ፡፡ ቋሚ ኮሚቴው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2009 በጀት አመት የሒሳብ ኦዲት ግኝቶች ላይ መጋቢት 11፣ 2011 ዓ.ም ይፋዊ ስብሳባ አካሄዷል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ባደረገው የፋይናንሺያል ኦዲት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከመንግስት የግዥ መመሪያ ውጭ ያለ ውድድር ከአንድ አቅራቢ የ5.9 ሚሊዮን ብር የተለያዩ ግዥዎችን፤ ለ28ኛ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ የ14.9 ሚሊዮን ብር ማስረጃ ያልቀረበበት ክፍያ እንዲሁም በተለያዩ ኢንባሲዎች ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ ለተደረገ ጉዞ ያለአግባብ ክፍያ ብር 183,899.00 ክፍያ መፈፀሙን አመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል የሴኪዩሪቲና የኪራይ አገልግሎት ግዥ በሚል ብር 73,920.00፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች በሚል ብር 90,519.92 እንዲሁም የአገልግሎት ግዥ በሚል ብር 370,636.10 ማስረጃ ሳይቀርብ የተወራረደ መሆኑ፤ በጀት ሳይኖር ለአፍሪካ ህብረት የአባል አገራት መዋጮ ክፍያ በሚል ብር 183,813,986.04 ወጭ ሆኖ መከፈሉን፤ በ2009 ተወራርዷል ከተባለው ብር 43,408,881.64 ውስጥ ብር 7,563,380.78 ማስረጃ የሌለው መሆኑን እና በበጀት አጠቃቀምም መ/ቤቱ በ2009 ከተፈቀደለት በጀት ውስጥ ብር 444,892,606.80 (20%) በሥራ ላይ አለማዋሉን እና ከበጀት በላይ ደግሞ ብር 330,099,679.28 ሥራ ላይ ማዋሉ በኦዲት ግኝቱ ተረጋግጧል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከተቀመጡ ህግና መመሪያዎች ውጪ የተፈፀሙ ተግባራትና የሒሳብ አሰራሮች ለማስተካከል ስለወሰዳቸው የማስተካከያ እርምጃ እንዲያስረዳ ጠይቋል፡፡

በሚኒስቴር መ/ቤቱ ሚንስትር ዴኤት አምባሳደር ብርትኳን አያኖ በሰጡት ምላሽ መ/ቤታቸው 46 ሚሲዮንና 14 ቆንስላ ጽ/ቤቶች በመላው ዓለም የሚያስተዳድር መሆኑንና እያንዳንዱ ሚሲዮንና ቆንስላ ጽ/ቤትም እንደሉበት አገር የተለያየ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት የሚመሩ በመሆኑ በአገር ውስጥ ያለውን የፋይናንስ አሠራር በተገቢ ሁኔታ ለመተግበር እንዳስቸገራቸው አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም ብዙ ችግሮች እየተፈጠሩ ያሉት ተቋሙ ለሦስተኛ ወገን ከሚፈፅማቸው ክፍያዎች ጋር በተያያዘ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በሚኒስቴር መ/ቤቱ የግዥ፣ ፋይናንስና አስተዳደር ዳይሬክተር ጄኔራል የሆኑት አቶ ሽብሩ ማሞ በሰጡት ምላሽ መ/ቤታቸው ያለበት የአሠራር፣ የአደረጃጀት እና የአቅም ችግር እንደሆነ በመገንዘብ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰራ እንደቆየና በተለይም በመ/ቤቱ የሚታየውን ጉልህ የተከፋይና ተሰብሳቢ ሒሳብ ችግር የሚከታተልና መፍትሔ የሚሰጥ እራሱን የቻለ የሥራ ክፍል ማቋቋማቸውን፤ ለ120 ለሚሆኑ በአገር ውስጥና በውጭ ለሚሰሩ የተቋሙ የፋይናንስ ባለሙያዎች በፋይናንስ አስተዳደርና አያያዝ ዙሪያ ሥልጠና መስጠቱን እና የሚሲዮኖች መተዳደሪያ መመሪያ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ተዘጋጅቶ ወደተግባር መገባቱን አስረድተዋል፡፡

ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር በሰጡት አስተያየት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ያሉበትን ችግሮች በአሠራር፣ በአደረጃጀት፣ በሥልጠና ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልፀው በተቋሙ የሚፈፀሙ ክፍያዎች ተገቢው ማስረጃ ሊቀርብባቸው እንደሚገባ፤ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የማዕቀፍ ግዢ ስምምነት በመፈፀም ቢሰሩ የተሸለ እንደሆነ እና ከዚህ በፊት በነበሩ የኦዲት ግኝቶች ላይ በሚፈለገው ልክ እየተሰራባቸው ባለመሆኑ ትኩረት በመስጠት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በሰጡት ሀሳብ የመቤቱ ኃፊዎች ብዙ የሂሳብ ችግሮች የሦስተኛ ወገን ችግር ነው በማለት ሊዘናጉ እንደማይገባና ይልቁንም ችግሮቹ በውጭም ሆነ በዋናው መ/ቤት በስፋት የሉ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ፤ በ2009 አወራርደናል ካሉት ገንዘብ ውስጥ 7.5 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ማረጋገጫ ሰነድ ያልቀረበበት በመሆኑ ተመልሶ ካልተወራረደ ሒሳብ ውስጥ ሊካተት እንደሚገባ፤ በአንድ አገር ውስጥ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ ለተደረገ ጉዞ የተፈፀመው ክፍያ ህጉን ያልተከተለ በመሆኑ የተከፈለው ክፍያ ተመላሽ መሆን እንዳለበት እና የበጀት አጠቃቀም ጋር በተያያዘም በዚህ ደረጃ በጀት በአግባቡ አለመጠቀም ተጠያቂ የሚያደረግ እንደሆነ ገልፀው ማስረጃ አልቀረበባቸውም የተባሉ ጉዳዮች በሙሉ ማስረጃ ሊቀርብባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መሐመድ የሱፍ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በአገሪቱ በወጡ የፋይናንስ ደንብና መመሪያ ሊመራ፤ የመንግስት ሃብትና ንብረት በአግባቡ ሊያስተዳድር፣ የክትትል እና ቁጥጥር ሥርዓቱን ሊያጠናክር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *