News

ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከተከታታይ ነቀፌታ ያለበት የኦዲት አስተያየት ለመውጣት ህግና ደንብን ጠብቆ ሊሠራ እንደሚገባ ተገለፀ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2008 በጀት ዓመት የፋይናንሺያል ኦዲት ግኝት ላይ ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ ታህሳስ 11፣ 2010 ዓ.ም አካሄደ፡፡ ተቋሙ በተከታታይ ከሚታይበት ነቀፌታ ያለበት የኦዲት አስተያየት ለመውጣት ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡

በኦዲት ግኝቱ እንደተመለከተው በሚኒስቴር መ/ቤቱ ስለሚከፈል የተጨማሪ እሴት ታክስ አፈፃፀምን ለማጣራት በተደረገው ኦዲት ከቻይና ኢምባሲ በድጋፍ ላገኘው ተሸከርካሪ የቀረጥ ክፍያ በሚል ለያንጋፉን ሞተርስ የመኪና ዋጋ ብር 381,739.13 ላይ 15% ተጨማሪ እሴት ታክስ 57,260.87 ቀንሶ ለገቢዎችና ጉሙሩክ ባለሥልጣን መ/ቤት ማስተላለፍ ሲገባው ለድርጅቱ ከፍሎ የተገኘ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የወጪ ሒሳቦችን በተሟላ ማስረጃ ሳይደገፉ የተፈፀሙ ክፍያዎችን በተመለከተ ለሚኒስትር ዲኤታ በብር 21,485.39 የተገዛ አይፎን 6 የሞባይል ቀፎ ለወጪው የንብረት ገቢ ደረሰኝ ያልቀረበ መሆኑ፤ በ7 የተለያዩ የባንክ ወጪዎች በድምሩ ብር 33,651.60 የቤት ዕቃዎችና አምፑሎች የተገዙበት የንብረት ገቢ ደረሰኝ ሳይቆረጥላቸው በወጭ የተመዘገቡ መሆናቸው፤ ብር 317,003.60 ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት መዋጮ በሚል በወጪነት የተመዘገበ ሒሳብ ገንዘቡ ለባለጥቅሞቹ ስለመድረሱ ማስረጃ ያልቀረበ መሆኑ፤ በሒሳብ እንቅስቃሴ መዝገብ ላይ የድጋፍ ማስረጃ ሳይቀርብላቸው በተለያዩ የቫውቸር ቁጥሮች ብር 17,772.86 መመዝገቡን፤ ለቢሮ ኪራይ አገልግሎት በ9 የወጭ ማስመስከሪያዎች በድምሩ ብር 1,035,342.00 ደጋፊ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ የተመዘገቡ መሆናቸውን፤ በተለያዩ ቫውቸር ቁጥሮች በድምሩ ብር 12,619.30 ቁልፍ ለማስቀረፅ፣ አምፑሎች መግዣና ለመስተንግዶ በሚል የተከፈሉ ክፍያዎች ተከታታይ የደረሰኝ ቁጥርና ህጋዊ ማህተም የሌላቸው መሆኑንና የሒሳቦቹንም ትክክለኛነት ለማረጋገጥ አለመቻሉን፤ ለሚሲዮን አዲስ የቤት ኪራይ ብር 750,603.05 እንደዚሁም ለቢሮ ኪራዩ የሴኪዩሪቲ ዲፖሲት የተከፈለ ክፍያ ብር 1,538,625.00 ማስረጃ ማግኘት ያልተቻለ መሆኑ፤ ለወንበሮች ጥገና ብር 22,536.98 ማስረጃ ሳይቀርብ በወጭ ተመዝግቦ የተገኘ መሆኑ፤ በተለያዩ ቫውቸር ቁጥሮች በድምሩ ብር 131,950.87 የነዳጅ ክፍያ ወጭ የሆነ ሲሆን የቀረበው የክፍያ ማስረጃ ትክክለኛነቱን ማጣራት ያልተቻለ መሆኑ እና የክፍያ መጠየቂያን እንደ ክፍያ ማስረጃ በመቁጠር ብር 479,094.08 የሚሲዮን መሪ መኖሪያ ቤት /ንብረት/ ታክስ ክፍያ የተከፈለ መሆኑ በኦዲት ግኝቱ ተመልክቷል፡፡

የሚኒስቴር መ/ቤቱን የሒሳብ እንቅስቃሴ አመዘጋገብ የሒሳብ አያያዝ ሥርዓቱን የተከተለ ስለመሆኑ ለማጣራት ኦዲት ሲደረግ በ5 የተለያዩ የወጪ ማስመስከሪያዎች፣ የባንክ የወጪ ማስመስከሪያ እና የሒሳብ እንቅስቃሴ መዝገብ ተመሳሳይ ባልሆነ የሂሳብ መደቦች ብር 244,817.70 የተመዘገበ መሆኑ፤ በሒሳብ ማዘዣ ቁጥር 910692 ላይ በዴቢት ብር 7,275,185.25 እንዲሁም በክሬዲት ብር 7,275,185.25 የተመዘገቡትን ሒሳቦች ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የመጀመሪያው የምዝገባ ማጣቀሻ ቁጥር አለመጠቀሱ እና በሒሳብ መዝገብ ማዘዣዎች በዴቢት እና ክሬዲት ብር 5,803,559.00 ለተደረገው ሒሳብ ማስተካከያ በቂ የሆነ ማብራሪያና ማስረጃዎች እንዳላቀረቡ ተገልጿል፡፡

ተሰብሳቢ ሒሳብን በተመለከተም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከብር 74,563,073.14 ውስጥ ብር 36,196,716.29 ስለመሰብሰቡ ማስረጃ የቀረበ ሲሆን ለቀሪው ብር 38,366,356.85 ማስረጃ አለመቅረቡን፤ ተከፋይ ሒሳብን በተመለከተም በሰኔ 30/2008 ዓ.ም የተከፋይ ሒሳብ ብር 106,884,753.85 የነበረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ብር 93,108,134.81 ማስረጃ የቀረበለት ሲሆን ቀሪው ብር 13,776,319.04 ማስረጃ ባለመቅረቡ የሒሳቡን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ አለመቻሉን፤ በደብሊን ኢምባሲ በጄቢ ቁጥር 59762 በዴቢት 5002 እና በክሬዲት 4274 ብር 2,949.69 ተሰብሳቢና ተከፋይን በማጣፋት ምዝገባ ተደርጎ የተወራረደበት መንገድ ተገቢ አለመሆኑን  እና በ2008 ዓ.ም ለመ/ቤቱ ከተመደበው ብር 1,905,294,095.29 ሥራ ላይ ከዋለው ጋር ሲገናዘብ 10% በላይ ሳይሰራበት የተገኘ ጠቅላላ ከመደበኛ በጀት ብር 170,960,837.22 እንዲሁም ከካፒታል በጀት ብር 50,816,881.55 በጠቅላላ ብር 221,777,718.77 ወይም 11.6 % ሥራ ላይ ያልዋለ በጀት በኦዲት ግኝቱ መገኘቱ ተገልጿል፡፡

የክትትል ኦዲትን በተመለከተም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ ፕሪቶሪያ ለተከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ለ250 ሰው የምግብ አገልግሎት ላቀረበ ድርጅት አስቀድሞ የአገልግሎት ውል ሳይገባና ድርጅቱ የተመረጠበት አጥጋቢ ማስረጃና አገልግሎቱን ለማግኘት የፀደቀበት ማስታወሻ ሳይቀርብ ብር 35,200.00 ክፍያ ተፈፅሞ በወጪ ተመዝግቦ መገኘቱን፤ የወንድና የሴት ሙሉ ልብስ ስፌት ታክስን ጨምሮ ብር 334,000.00 ያለጨረታ በቀጥታ ግዢ መፈጸሙን፣ ለግዢውም መጠየቂያ አለመቅረቡን እና ክፍያው ሲፈፀም ታክስን ጨምሮ 334,000.00 መሆን ሲገባው ብር 348,398.55 በመከፈሉ  ብር 14,398.55 በብልጫ መክፈሉን የኦዲት ሪፖርቱ አመልክቶ ቋሚ ኮሚቴው በአጠቃላይ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በዋና መ/ቤቱና በኢንባሲዎቹ የሚያንቀሳቀሰውን በጀት ለሚፈለገው ዓላማ በአግባቡ ለመጠቀም፣ የፋይናንስ ህግና መመሪያዎች መሠረት በማድረግ ግዢዎችን ለመፈፀም፣ ህጋዊ የክፍያ ሰነዶችን ለማቅረብ፣ ክፍያዎችን በትክክለኛ ሰነድ መዝግቦ ለመያዝ እንደዚሁም የኦዲት ግኝቱን ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት፣ ለመከታተል  እና የውስጥ ኦዲት ቁጥጥርን አጠናክሮ ጤናማ የፋይናንስ አሠራር እንዲኖር ለማድረግና እና ተቋሙ ነፃ የሆነ የኦዲት አስተያየት እንዲኖረው ለማድረግ ምን እየሰራ እንደሚገኝ የተቋሙ ኃላፊዎች እንዲያብራሩ ጥያቄዎችን አቅርቧል፡፡

በሚኒስቴር መ/ቤቱ የፋይናንስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሸጋው አባተ በሰጡት ምላሽ ለገቢዎችና ጉሙሩክ ባለሥልጣን ያላስተላለፉትን የተጨማሪ እሴት ታክስ ለድርጅቱ እንዲከፈል ማድረጋቸውን፤ የወጪ ገቢ ደረሰኝ ያልተመዘገበለትን ሞባይል ሞዴል 19 ተቆርጦ ገቢ እንዲደረግ መደረጉን፤ ገቢ ደረሰኝ ያልተቆረጠላቸው የቤት ዕቃዎችና አምፑሎች የተገዙበት የንብረት ገቢ ደረሰኝ ክትትል በማድረግ እንዲቆረጥላቸው መደረጉን፤ በወጪ ተመዘገቦ ማስረጃ ያልቀረበለት የመዋጮ ክፍያ ማስረጃ እንዲያያዝለት መደረጉን፤ በተለያዩ የቫውቸር ቁጥሮች በስህተት የተመዘገቡ ሰነዶችን የማስተካካል ሥራ መሠራቱን፤ ለቁልፍ ማስቀረጫ፣ ለአምፑሎች መግዣና ለመስተንግዶ የተከፈሉ ክፍያዎች ትክክለኛ ማስረጃ እንዲቀርብላቸው መደረጉን፤ ለነዳጅ ክፍያ የቀረበውን ማስረጃ ትክክለኛነቱን የማረጋገጥ ሥራ መሠራቱን፤ የክፍያ መጠየቂያን እንደ ክፍያ ማስረጃ በመቁጠር ሰነድ የቀረበበትን እንዲስተካከል  መደረጉንና ማስረጃ መያያዙን እንዲሁም ማስረጃ ሳይቀርብባቸው ለወንበሮች ጥገና ተደረገዋል በሚል የወጡ ወጪዎችን ለወደፊት እንዲስተካከሉ እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡

ከአመዘጋገብ ጋር የተፈጠሩ ስህተቶችን በተመለከተም ስህተት መሆናቸው ተምኖ የተወሰኑት እንዲስተካከሉ መደረጋቸውንና ቀሪዎቹም በቀጣይ ተስተካክለው እንዲመዘገቡ እንደሚደረግ፤ ተሰብሳቢ ሒሳብን በተመለከተም ከ74 ሚሊዮን ብር ተሰብሳቢ ሒሳብ ወደ 44 ሚሊዮን የሚሆነውን ሒሳብ በተሰራው ሥራ ማወራረድ መቻላቸውን እና ቀሪ ሒሳቦችንም ለመሰብሰብ እራሱን የቻለ ዳይሬክቶሬት በማቋቋም ችግሩን ለመፍታት መታቀዱን፤ በተከፋይ ሒሳብ በኩልም በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውንና ቀሪ ከነበረው 13 ሚሊዮን ሒሳብ 4 ሚሊዮን ቀሪ ተከፋይ ሒሳብ መቅረቱን፤ ከበጀት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ካፒታል በጀት አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለና ችግሩም አብዛኛውን ጊዜ ጨረታ ሲወጣ የሚወዳደር አካል የማይገኝና በአገር ውስጥ ያለ አሠራርና በውጭ አገር ያለ አሠራር የተለያዩ በመሆናቸው እንደሆነ፤ በክትትል ኦዲት በኩል በፕሪቶሪያ ኤምባሲ ለተፈፀመ የምግብ አገልግሎት የክፍያ ማስረጃ ማቅረብ ያልተቻለው ለበዓሉ ዝግጅት የሐበሻ ምግብ እንዲሆን በመታሰቡ እና በዓሉ የተከበረበት አከባቢ የአበሻ ምግብ አወዳድሮ ለማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ የተፈጠረ ችግር እንደሆነ፤ የውስጥ ኦዲትም ከዚህ ቀደም ከነበረው በተጠናከረ ሁኔታ ሥራቸውን እየደገፈ እንደሚገኝና በሌሎችም በመድረኩ በተነሱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አቶ ሸጋው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡፡፡

በሚኒስቴር መ/ቤቱ ሚኒስቴር ዲኤታ የሆኑት ክቡር አቶ ዮናስ ዮሴፍ በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ የሚታዩትን የፋይናንስ ችግሮች ለመቅረፍ አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱን ለማስተካከል እየሰሩ እንደሚገኙ፣ በግዢና በተለያዩ የሰነድ አያያዝ ጉዳዮች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን እንደግብዓት እንደሚወስዱ፣ መድረኩንም በአስተማሪነት እንዳገኙትና አሠራራቸውን እንደሚያስተካክሉ ገልፀዋል፡፡

በተለይም በአቅም ግንባታ ሠራተኛውን የማብቃትና ከአሠራር ጋር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላቸው ዘንድ መዋቅር በማስጠናት ላይ እንደሚገኙ፣ በውጭ አገር ያሉ ሚሲዮኖችን የሂሳብ አያያዝ ችግሮች ለመቅረፍ የሚረዳ መመሪያ እንደሚያዘጋጁ፤ የኦዲት ግኝትን መሠረት አድርጎ የሚከታተል ቋሚ ግብረ-ኃይል እንደተደራጀ፤ በ56ቱም ሚሲዮን መ/ቤቶቻቸው የሚገኙ ባለሙያዎችም ትክክለኛ መረጃ እንዲያመነጩ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርጉ፤ በበጀት አጠቃቀም በኩል በ2008 ዓ.ም የተሟላ አፈጻጸም እንዳልነበራቸው በመገምገም በ2009 ዓ.ም የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖር መሠራቱን፤ ተሰብሳቢ ሒሳብን በተመለከተም አሁንም የተቋሙ ችግር ሆኖ እንደሚቀጥልና የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትም ሆነ የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ችግሩን ለመቅረፍ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ሚኒስቴር ዲኤታው ጠይቀዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው በሰጡት ሃሳብ በተሰብሳቢ ሒሳብ በኩል መልካም የተባለ ሥራ መሥራታቸው ቢገለጽም በተባለው ልክ ስለመሰብሰቡ ማስረጃ ሊቀርብበት እንደሚገባ፤ በውስጥ ኦዲት አንፃር ከውይይቱ ለመረዳት እንደተቻለው የውስጥ ኦዲቱ ተቋሙ እየታየበት ያለውን ችግር ገለልተኛ ሆኖ ለመፍታት ጥረት ከማድረግ ይልቅ የተፈጠሩ ጥፋቶችን በመሸፋፈን ላይ እንደሚገኝ፤ ከአመዘጋገብ ስህተት ጋር በተያያዘ ተቋሙ የሰጠው ምላሽ አጥጋቢ እንዳልሆነና ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ፤ ተቋሙ የበጀት አጠቃቀም ልምዱ ለተከታታይ አመታት ደካማ መሆኑን ከአመት አመት መሻሻል አለማሳየቱን፤ ከሦስተኛ ወገን ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ችግሩን የራስ አድርጎና የአሠራር ሥርዓት ዘርግቶ ሊሰራ እንደሚገባ፤ በግዢ ኤጀንሲ የተቀመጡ ደንብና መመሪያዎች ተፈፃሚነት ሊኖራቸው እንደሚገባ እና ከዓመት ዓመት ተመሳሳይ ግድፍት ከሚያሳይበት አሰራር ተቋሙ እራሱን ሊያርም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት የተጨማሪ እሴት ታክስ ለድርጅት የተከፈለው ክፍያ አግባብ ባለመሆኑ ተመላሽ ሊሆን እንደሚገባ፤ ማንኛውም ግኝት ሳይንሳዊ መርሆችን ተከትሎ የሚሠራ እና ማስረጃ ሳይኖር በግኝት ሊመዘገብ እንደማይችል አስረድተው ተቋሙ ማስረጃ ካለው በወቅቱ የተጠየቀውን ማስረጃ ማቅረብ እንደነበረበት፤ ዓለም አቀፍ ግዢዎችንም በተመለከተ ተገቢውን ደረሰኝ ማግኘት ባይቻል እንኳ ገንዘቡ ወደባንክ መግባቱን የሚያስረዳ ማረጋገጫ ሰነድ ሊቀርብ እንደሚገባ፤ በሒሳብ አመዘጋገብ ላይም በአግባቡ ያልተመዘገበ ሒሳብ ውጤቱም ትክክለኛ ስለማይሆን በጥንቃቄ ሊመዘገቡና ከበቂ ማስረጃ ጋር ሊቀርቡ እንደሚገባ፤ በውጭ አገር ያሉ የሂሳብ አያያዝ ችግሮች ጋር በመነሳት መ/ቤቱ መመሪያ እያዘጋጀ እንደሚገኝ የተገለፀውም አግባብ አለመሆኑንና መመሪያ ማዘጋጀት ካለበትም የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መ/ቤት እንደሆነ፤ ተሰብሳቢ ሒሳቦችንም በተመለከተ የቆዩ እና አሁንም እየተፈጠሩ ያሉ እንዳሉ ገልፀው በጥንቃቄ መፍትሔ መፈለግ እንደሚያስፈልግ፤ ተመላሽ ሒሳብ በማይከፍሉ አካላት ላይም በቀጣይ አገልግሎቱን እንዳያገኙ ማድረግ እንደሚያስፈልግ እና በጥቅማጥቅም ህግ ውስጥ ያልተቀመጠና ላልተፈቀደ ክፍያ የተከፈለ 280 ሺህ ብር ተመላሽ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት ገለሶ በመጨረሻ ባስተላለፉት መልዕክት ሚኒስቴር መ/ቤቱ የኦዲት ግኝቶችን መሠረት አድርጎ ችግሮችን ለመቅረፍ እራሱን የቻለ ኮሚቴ አቋቁሞ መስራቱ በጥንካሬ እንደሚወሰድ ገልፀው ነገር ግን የተቋቋመው ኮሚቴ የሥራ ውጤትም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊታይ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም ተቋሙ ከተከታታይ ነቀፌታ ካለበት የኦዲት ግኝት ለመውጣት አሠራሮቹን በአግባቡ ሊፈትሽ፤ ደንብ፣ መመሪያና ህጎችን ተከትሎ ሊሠራ እንደሚገባ፤ የንብረት አያያዝ፣ የሒሳብ አሰራርና የተሰብሳቢ ሒሳብ አሰባሰብ ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለበት፤ የአሰራር ክፍተት ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ህጎች እንዲወጡ ከሚመለከተው አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ፤ በተቋሙም ይሁን በሚሲዮኖች ያሉትን የፋይናንስ ባለሙያዎች አቅም መገንባት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ፤ የውስጥ ኦዲት ገለልተኛ ሆኖ መ/ቤቱን ከአሰራር ችግር ሊጠብቅ በሚያስችል አግባብ መደረጀት እንዳለበት፤ ተቋሙ ያሉበትን ችግሮች መቅረፍ ያስችለው ዘንድ ከባለድርሻ አካላት ጋር መሥራት እንደሚያስፈልገው፤ እርምጃ ተወስዶባቸዋል የተባሉ ጉዳዮችም ትክክለኛ ማረጋገጫ ለዋና ኦዲተር መ/ቤት ሊቀርብባቸው እንደሚገባ እና በአጠቃላይ ተቋሙ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት በዋና መ/ቤትም ሆነ በተለያዩ አገርት በሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች ላይ የአመለካከት ሥራ መሥራት እንዳለበት ወ/ት ወይንሸት አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *