የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ሚኒስቴር እና ለሚኒስቴሩ ተጠሪ በሆኑት በብሔራዊ እንስሳት ጤና ምርምርና ጥናት ማዕከል እና በብሔራዊ ሰው ሰራሽ እንስሳት ማራቢያ ዘዴ ማዕከል የ2008 በጀት ዓመት የፋይናንሺያል ኦዲት ግኝት ላይ ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ ህዳር 20፣ 2010 ዓ.ም አካሄደ፡፡
በኦዲት ግኝቱ እንደተመለከተው የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ሚኒስቴር ከሁለት ድርጅቶች ጋር በገባው የውል ስምምነት መሠረት የከፈለውን የቅድሚያ ክፍያ ሂሳብ ብር 153,832.21 ያልሰበሰበ መሆኑ፤ ለተለያዩ ወጪዎች የተፈጸመ ክፍያ ብር 1,733,134.31 በተገቢው የሂሳብ መደብ ያልመዘገበ መሆኑ፤ በእንስሳት ሀብት ልማት ላይ ለሦስት ቀን ስልጠና ለተሳተፉ 59 የክልል ባለሙያዎች የጉዟቸውን ሳይጨምር ብር 29,616.00 መከፈል ሲገባው ብር 163,514.00 የተከፈለ መሆኑ፤ የሚመለከተውን የመንግሰት አካል ሳያስፈቅድ ብር 80,541.76 የትርፍ ሰዓት ክፍያ የፈፀመ መሆኑ፤ ከደንብ ልብስ አስፈላጊነትና ዓላማ ውጪ ለሠራተኞች 247,405.94 በጥሬ ገንዘብ ክፍያ መፈፀሙ፤ ሥራ ላይ ያልዋለ ከመደበኛ በጀትና ከካፒታል በጀት በድምሩ ብር 30,621,908.60 የተገኘበት መሆኑ፤ ለየሂሳብ መደቦቹ ከተደለደለው በጀት በላይ ከመደበኛና ካፒታል በጀት በድምሩ ብር 1,786,817.56 ወጪ መሆኑ እና ሚኒስቴር መ/ቤቱ የሰኔ ወር 2008 ዓ.ም የቋሚ ሠራተኞች ደመወዝ ክፍያን ብር 1,736,915.40 በወጪ የመዘገበ ቢሆንም ለክፍያው የደመወዝ ፔይሮል ማቅረብ ያልቻለ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በብሔራዊ እንስሳት ጤና ምርምርና ጥናት ማዕከል በኩል ከ2006 በጀት ዓመት ጀምሮ በተለያዩ የሒሳብ መደቦች የተመዘገበ ብር 954,392.57 በደንቡና በመመሪያው መሠረት ያልተወራረደ መሆኑ፤ በማዕከሉ የቤትና የልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ አበል ለተፈቀደላቸው አካላት ክፍያ ሲፈፀም በጠቅላላው ብር 49,107.2 ግብር ያልተቀነሰ መሆኑ፤ በንብረት አስተዳደር በኩል በማዕከሉ ስቶክ ካርድና ቢን ካርድ ያልተዘጋጀላቸው ንብረቶች መኖራቸው፤ አንዳንድ ንብረቶች ያለ አገልግሎት ለረጅም ጊዜ በግምጃ ቤት ውስጥ ተከማችተው መገኘታቸው፤ የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸውና የተበላሹ ኬሚካሎች በግምጃ ቤት ውስጥ ተከማችተው መገኘታቸውና በሞዴል 19 ገቢ የሆነ ነዳጅ ወጪ ሲደረግ በሞዴል 22 የማይወጣ መሆኑ በኦዲት ግኝትነት የተገለፀ ሲሆን በሌላ በኩል ከመደበኛ በጀት ብር 6,995,297.70 እና ከካፒታል በጀት ብር 655,812.80 በድምሩ ብር 7,651,110.50 ሥራ ላይ ያልዋለ መሆኑ እንዲሁም ማዕከሉ የሥጋት ምንጮች ዳሰሳ፣ የተጋላጭነት ደረጃ መለየት እና የሥጋት ተጋላጭነት ፍተሻ ማድረግ ቢኖርበትም ያላደረገ መሆኑ በኦዲት ግኝቱ ተጠቅሷል፡፡
በብሔራዊ ሰው ሰራሽ እንስሳት ማራቢያ ዘዴ ማዕከል በኩል ማዕከሉ በ2008 በጀት ዓመት ብር 7,397,200.00 ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ ብር 4,257,161.98 ቢሰበስብም ብር 3,140,038.02 (42%) ያልተሰበሰበ መሆኑ፤ በንብረት አያያዝ በኩልም ነዳጅና በቀላሉ ሊቃጠሉ የሚችሉ ንብረቶች እንዲሁም የሚያገለግሉና የማያገለግሉ ንብረቶች በአንድ መጋዘን ውስጥ መኖራቸው፣ በግምጃ ቤቱ በሚገኙ አላቂ ንብረቶች ላይ ቢን ካርድ የማይንጠለጠልባቸው መሆኑ፤ በማዕከሉ የባለቤትነት መታወቂያ (ሊብሬ) ያልቀረበላቸው ተሽከርካሪዎች መኖራቸው፤ 8 ሞተር ሳይክሎች የሰሌዳ ቁጥር እና የባለቤትነት መታወቂያ (ሊብሬ) የሌላቸው መሆኑ እና ከመደበኛ ብር 2,403,837.25፣ ከውስጥ ገቢ በጀት ብር 742,383.20 በድምሩ ብር 3,146,220.45 ሥራ ላይ አለመዋሉ እንዲሁም ከመደበኛ በጀት ብር 12,109.92 ለየሒሳብ መደቦቹ ከተደለደለው በጀት በላይ ሥራ ላይ መዋኑ በኦዲት ግኝቱ ተገልጿል፡፡
ቋሚ ኮሚቴውም በእነዚህና ከህግና መመሪያ ውጪ በተፈፀሙ ሌሎች ተግባራት የሚኒስቴር መ/ቤቱ እና የየማዕከላቱ የበላይ አመራሮች ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱን አስመልክቶ የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ሚኒስቴር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነና ሌሎች የበላይ አመራሮች በሰጡት ምላሽ የተነሳውን ክፍተት ትኩረት ሰጥተው እንደሚያስተካክሉ ገልፀው የችግሩ ምንጭ በወቅቱ ተቋሙ አዲስ በመሆኑና የሰው ኃይል ባለመሟላቱ እንደሆነ፤ ያለፔይሮል የተከፈለ ደመወዝን በተመለከተም ክፍያ የተፈፀመው በፔሮል ቢሆንም ሰነዱ ጠፍቶ እስከአሁንም ሊገኝ አለመቻሉንና መከፈሉን የሚያረጋግጥ ሰነድ ከባንክ ጋር በመነጋገር ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን፤ ሥልጠና ላይ ለተካፈሉ የክልል ባለሙያዎች በብልጫ የተከፈለ የትራንስፖርት አበልም የደርሶ መልስ ወጪያቸውን በማስላት የተሰራመሆኑን፤ የደንብ ልብስ በመስጠት ምትክ በጥሬ ገንዘብ የተከፈለውም መ/ቤቱ አዲስ ሆኖ ከመቋቋሙ ጋር በተያያዘ የነበረን ጫና ለማስወገድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የብሔራዊ እንስሳት ጤና ምርምርና ጥናት ማዕከል አመራሮች በሰጡት ምላሽ ያልተወራረደ ሒሳብ እንዲወራረድ ለማድረግ ሒሳባቸውን ያላወራረዱ ክልሎች ድረስ በመሔድ እንዲያወራርዱ ጥረት ቢሆንም አለመሳካቱን፤ በንብረት አያያዝ በኩል የነበሩ ችግሮችን ለማስተካከል የተለያዩ ሥራዎች መሠራታቸውን እና በጀት በአግባቡ ያልተጠቀሙትም ለእንስሳት መኖ ተይዞ የነበረው በጀት ብዛት ያላቸው እንስሳት በበጀት ዓመቱ በመሞታቸው ሳቢያ ሥራ ላይ ባለመዋሉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የብሔራዊ ሰው ሰራሽ እንስሳት ማራቢያ ዘዴ ማዕከል ኃላፊዎች በበኩላቸው ነዳጅና ሌሎች በቀላሉ ሊቃጠሉ የሚችሉ ንብረቶች በአንድ ቦታ ይገኙ የነበረበትን ሁኔታ በማስተካከል እንዲለዩ መደረጉን፤ ሊብሬ ለሌላቸው መኪኖች ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር እንደተገኘላቸው ሞተር ሳይክሎቹ ግን እስካሁን ድረስ ሊብሬያቸው ስላልተገኘሰነድ አልባ ንብረቶች በመባል እንዲወገዱ ለንብረት ማስወገድ አገልግሎት እንዲተላለፉ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የመጡ የሥራ ሃላፊ በሰጡት አስተያየት ከፌዴራል ዋናው ኦዲተር በደረሳቸው የ2009 ዓ.ም የ4 ሩብ ዓመት ሪፖርት አሁንም በብልጫ ክፍያ እየተፈፀመ መሆኑን እና የተቋማቱ አንዱ ችግር የውስጥ ኦዲት ቢሮዎቻቸው አለመጠናከር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር አበል አከፋፈል በመመሪያው መሰረት ብቻ ሊከፈል እንደሚገባ፤ የደንብ ልብስ በጥሬ ገንዘብ መክፈል ከዓላማው ውጭ እንደሆነ፣ የተመደበ በጀት ጥቅም ላይ እንደማይውል ሲታወቅ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መ/ቤት ማሳወቅ ይገባ እንደነበር እንዲሁም የንብረት አያያዝ ሰፊ ችግር ያለበት በመሆኑ የንብረት አስተዳደሩ ከገንዘብ እኩል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚየሻ ገልጸዋል፡፡
ክቡር የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ሚኒስቴር የኦዲት ግኝቱ ከደረሰው በኋላ በተቀመጠው ቀነ ገደብ ውስጥ የድርጊት መርሃ ግብር አዘጋጅቶ ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አለመላኩ ትክክል አለመሆኑን ጠቅሰው ሁለቱ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ተጠሪ ማዕከላትም መርሃ ግብር የላኩ ቢሆንም የወሰዷቸውን የማስተካከያ እርምጃዎች ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አለማሳወቃቸው ተገቢ ባለመሆኑ ሊታረም እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በብልጫ የተከፈለው ውሎ አበል አንድም ብር ቢሆን ተመላሽ ሊደረግ እንደሚገባና ይህንን ስህተት የፈጸሙ አካላትንም ተጠያቂ ማደረግ እንደሚያስፈልግ፤ ለደንብ ልብስ የተከፈለው ጥሬ ገንዘብ ዓላማውን የሳተ ስለሆነ ተገቢ አለመሆኑን፤ ያልተወራረደው ሂሳብ ላይ የቀረበው ምክንያትም አሳማኝ ባለመሆኑ በአስቸኳይ ሊወራረድ እንደሚገባና ከተደለደለው በጀት በላይ መጠቀም የበጀት አዋጁን የጣሰና የሚያስጠይቅ በመሆኑ ሊታረም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ት ወይንሸት ገለሶ በሰጡት ማጠቃለያ የኦዲት ግኝቱን መሠረት በማድረግ በተቋማቱ በኩል የተሰጠው ምላሽ አጥጋቢ አለመሆኑን ገልፀው ሚኒስቴር መ/ቤቱም ሆነ የሁለቱ ተጠሪ ማዕከላት የፋይናንስ አደረጃጀታቸውን እንዲሁም የንብረት አያያዝና አወጋገድ ሥርዓታቸውን ማሻሻል እንደሚጠበቅባቸው፤ ጠፋ የተባለው ፔይሮልም ትኩረት ተሰጥቶት ሊሟላ እንደሚገባ፤ ብዙዎቹ ችግሮች የሚፈጠሩት የውስጥ ኦዲተር ለሚሰጠው ሃሳብ ትኩረት ባለመስጠት የሚፈጠር በመሆኑ የውስጥ ቁጥጥርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ፤ ተመላሽ ገንዘብ ገቢ ባላደረጉ ተቋራጮች ላይ ክስ ሊመሰረት እንደሚገባ እና ተቋማቱ መንግስት ያወጣቸውን ህግና መመሪያዎች በአግባቡ ተግባራዊ ሊያደረጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡