የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒሰቴር የፕሮጀክት ውልና የሰው ሀብት አስተዳደር አፈፃፀም ውጤታማነትን በተመለከተ በ2015/16 ኦዲት ዓመት ያካሄደውን የክዋኔ ኦዲት መሠረት በማድረግ የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ በም/ቤቱ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒሰቴር በ2015/16 ኦዲት ዓመት የፕሮጀክት ውል እና የሰው ሃብት አስተዳደር አፈጻጸሙ ደካማ እንደነበር ተገልጿል፡፡
መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም በምክር ቤቱ በተካሄደው የውይይት መድረክ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በሚያካሂዳቸው ፕሮጀክቶች ላይ በኦዲት ግኝት እንደተመላከተው ፕሮጀክቶች ከመተግበራቸው በፊት የዳሰሳና የቅደመ አዋጭነት ጥናት አለመደረጉ፣ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ግዢበ መመሪያ መሠረት የማይፈጽም መሆኑን፣ የፕሮጅክቶች ውል በሚፈጸምበት ጊዜ ከህግ አንጻር በፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስተያየትና ምክር እንዲሰጥባቸው አለማድረጉን እና የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ክትትልና ቁጥጥር የሚደረግበት ስርዓት አለመዘርጋቱ ተገልጻል፡፡
ፕሮጀክቶች በተገባላቸው ውል፣ በተያዘላቸው እቅድና በጀት እንዲጠናቀቁ ከማድረግ አንጻርም በተያዘላቸው ጊዜና በጀት እንደማይጠናቀቁ፣ ለአብነትም ሞዴል የሳይንስና የቴክኖሎጂ ቤተ-መጻህፍት በተያዘለት ጊዜና በጀት ባለመጠናቀቁ ብር 43,044,953.22 የሚሆን ተጨማሪ ወጪ ማስከተሉ ፣ ነባሩን የዳታ ማዕከል ለማሻሻል የተጀመረው ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜና በጀት ባለመጠናቀቁ ለብር 277,071,644.36 ተጨማሪ ወጪ ያስከተለ እና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክት አፈጻጸም ከ2009 እስከ 2015 በጀት አመት መጨረሻ ድረስ ለፕሮጀክቱ ጠቅላላ ወጪ ብር 299,610,994.84 ቢወጣም ኦዲቱ እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ ግንባታው አለመጀመሩ ተጠቁሟል፡፡
ከሰው ሃብት አስተዳደር ጋር በተያያዘም ሚኒስቴር መ/ቤቱ በድጋፍና ብድር የሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች ላይ የሚቀጠሩ ሠራተኞች በሚኒስቴር መ/ቤቱ የሰው ሃብት አስተዳደር በኩል ቅጥር እንዲፈጸም እና ከቅጥር እስከ ስንብት ያሉ የሰራተኞችን መረጃ አደራጅቶ የማይዝ መሆኑን፣ ውል ለሌላቸውና ውላቸው ለተቋረጠ ሠራተኞች መመሪያው ከሚያዘው የደመወዝ ጭማሪ በላይ ክፍያ በመፈጸም በድምሩ ብር 3.6 ሚሊየን በላይ ያለአግባብ ክፍያ ተፈጽሞ መገኘቱ እና ጊዚያዊ ሰራተኞች የቋሚ ንብረቶችን ለሚመለከተው አካል ርክክብ እንዲያደርጉ ባለመደረጉ በድምሩ ብር 8,609,114.31 የሚያወጡ ንብረቶች ገቢ አለመደረጋቸውን እና ከኦዲት ግኝቱ በኋላ የድርጊት መርሃግብር በማዘጋጀት የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ጥረት አአለመደረጉ ተገልጾ በመድረኩ የተገኙ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቀዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒሰቴር ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እና ሌሎች የሚኒስቴር መ/ቤቱ የሥራ ሀላፊዎች የኦዲት ግኝቶችን ትክክለኛነት በማረጋገጥ በግኝቶቹ ላይ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ግኝቶቹን መሠረት በማድረግ በቀጣይ የድርጊት መርሃ ግብር በማዘጋጀት የማስተካከያ እርምጃዎች እንደሚወስዱ ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ በሚኒሰቴር መ/ቤቱ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እየተጠናቀቁ አለመሆናቸውን፣ በተደጋጋሚ እንዲቋረጡ መደረጉን፣ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር እንደማያደርግባቸው፣ ወጪዎች ሲወጡ የፕሮጀክቶቹን አፈጻጸም ለመመዘን በማያስችል መንገድ ይሰራ እንደነበር፣ የሰው ሃብት አስተዳደር በኩል የቅጥር ሂደት ሳይከተሉ በሪኮማንዴሽን ብቻ የሰራተኞች ቅጥር ይፈጸሙ እንደነበር እና ሌሎች በርካታ የአሠራር ሥርዓት ጥሰቶች በኦዲቱ መታየታቸውን ገልጸው ሚኒስቴር መ/ቤቱ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ በሰራቸው ሥራዎች ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ኦዲቱ የተሰራው ከምክር ቤቱ በቀረበ ጥያቄ መሠረት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል አግባብ መሆኑን አስታውሰው ኦዲቱም ሦስት የትኩረት አቅጣጫዎችን መሰረት አድርጎ መሰራቱንና ሪፖርቱም ለፍትህ ሚኒስቴር፣ ለስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ከሚሽን እንዲሁም ለገንዘብ ሚኒስቴር መላኩን ገልጸዋል፡፡
ክብርት ዋና ኦዲተሯ አክለውም የሚኒስቴር መ/ቤቱ አጠቃላይ የፕሮጅክቶች አፈጻጸም ደካማና ዓላማዎቻቸውን በአግባቡ ያላሳኩ እንደነበሩ፣ ፕሮጀክቶቹ ከመተግበራው በፊት የቅድመ አዋጭት ጥናት አለመካሄዱን፣ ፕሮጀክቶች ላይ የሚቀጠሩ ሠራተኞች ተወዳድረው ስለመቀጠራቸው ማስረጃ አለመቅረቡን፣ ለፕሮጀክት ሠራተኞች ያለአግባብ የተለያዩ ክፍያዎች መፈጸሙን፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት አለመስራቱን እና ከመረጃ አያያዝ ጋር በተያያዘ ሚኒስቴር መ/ቤቱ እንደሀገር ብዙ የሚጠበቅበት ቢሆንም በሚጠበቅበት ልክ መረጃዎቹን አለማደራጀቱን አንስተዋል፡፡
የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና ሚኒስቴር መ/ቤቱ ሊወስዳቸው ከሚገቡ እርምጃዎች ጋር በተያያዘም ዋና ኦዲተሯ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የፕሮጀክቶችን ፊዚካል አፈጻጸም ሳይመለከቱ ገንዘብ መልቀቅ እንደሌለባቸው እና ሚኒስቴር መ/ቤቱም በናሙና የተገኙትን የኦዲት ክፍተቶች መሠረት በማድረግ አጠቃላይ አሠራሩን ሊፈትሽና ተጠያቂነትን በየደረጃው ማረጋገጥ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
የሚኒሰቴር መ/ቤቱ አመራሮች ቀጣይ የኦዲት ግኝት ማስተካከያ እርምጃዎች ተወስደው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለተገቢው አካላት የአፈፃፀም ሪፖርት እንዲቀርብ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የማጠቃለያ አስተያት የሰጡት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር) ለትክክለኛና ህጋዊ አሰራር ኦዲት ያለውን ጠቀሜታ በማንሳት ሚኒሰቴር መ/ቤቱ ግኝቶችን እንደ መማሪያ በመውሰድ ተጠያቂነት የሰፈነበት የአሰራር ስዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢዋ አክለውም በመድረኩ የተሰጡ አስተያየቶችን መሰረት ያደረጉ እርምጃዎች ተወስደው እስከ መጋቢት 28 ቀን 2017 ድረስ የድርጊት መርሀ ግብር ለቋሚ ኮሚቴውና ለሚመለከታቸው የኦዲት ባለድርሻ አካላት እንዲቀርብ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡