የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ዋነኛ ስራው ከሆነው የኦዲት ተግባር በተጓዳኝ በተደራጀ የስልጠና ማዕከሉና የአቅም ግንባታ ዕቅዱ መሰረት ስራውን ሊያግዙ የሚችሉ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
በዚህም መሰረት የራሱን አመራሮችና ሠራተኞች ሁለንተናዊ ሙያዊ አቅም ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ሲሆን ለሥራው ዋነኛ አጋር የሆኑ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች ዋና ኦዲተር መ/ቤቶችን አቅም ለመገንባትም ውጤታማ እገዛ እያደረገ ነው ፡፡
በቅርቡም ለክልልና ከተማ አስተዳደሮች ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ኦዲተሮች በፋይናንሽያል ኦዲት አስተዳደር (Financial Audit Manual-FAM) ምንነትና የተሻሻለ አተገባበር ዙሪያ ክልሎች ድረስ በመሄድ ተከታታይ ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል፡፡
ከታህሳስ 24-28/2015 ዓ.ም በነበሩት 5 ቀናትም የዚሁ አቅም ግንባታ መርሀ ግብር አካል የሆነውን በፋይናንሽያል ኦዲት አስተዳደር (Financial Audit Manual-FAM) ምንነትና የተሻሻለ አተገባበር ላይ ያተኮረ ስልጠና ለሶማሌ ክልላዊ መንግስት ዋና ኦዲተር መ/ቤት አመራሮችና ኦዲተሮች ሰጥቷል፡፡
በስልጠናው ማክፈቻ ላይ የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ዋና ኦዲተር አቶ መሐመድ የሱፍ፣ ምክትል ዋና ኦዲተር አብዱላሂ አብዲ እና የክልሉ ምክትል አፈጉባኤ አቶ ኢብራሒም ተገኝተው ለሰልጣን ኦዲተሮች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በጅግጅጋ ከተማ የተካሄደውን በተግባራዊ ልምምድ የታገዘ ስልጠና የሰጡት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አሰልጣኝ ባለሙያዎች አቶ ቴዎድሮስ ሽመልስና አቶ እዮብ ጉታ ሲሆኑ በስልጠናው የክልሉ ዋና ኦዲተርና ም/ዋና ኦዲተር እንዲሁም የማኔጅመንት አባላትን ጨምሮ 70 የሚሆኑ ሰልጣኞች ተሳትፈዋል፡፡
ሰልጣኞች ከስልጠናው በኋላ በሰጡት አስተያየትም ስልጠናው በተለይም በአዲሱ የፋይናንሽያል ኦዲት አስተዳደር (Financial Audit Manual-FAM) አተገባበር ዙሪያ ጠቃሚ ግንዛቤና ዕውቀት ያገኙበት መሆኑን ጠቅሰው የፋይናንሽያል ኦዲት ስራቸውን የበለጠ ቀልጣፋና ምቹ እንደሚያደርግላቸው እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተለያዩ አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ አዳዲስ የኦዲት አሠራሮችን ለራሱም ሆነ ለክልልና ለከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች በማስተዋወቅ ፍሬያማ የአቅም ግንባታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡