News

መ/ቤቱ በንብረት አያያዝና በጀት አጠቃቀም ላይ ያለበትን ችግር ለመፍታት ተኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

በኢ.ፊ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ጆሎጂካል ሰርቬይ መ/ቤት በንብረት አያያዝና በጀት አጠቃቀም ላይ ያለበትን ችግር ለመፍታት ተኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ የመ/ቤቱን የ2009 በጀት ዓመት የሒሳብ የኦዲት ግኝት ሚያዚያ 30፣ 2011 ዓ.ም በገመገመበት ይፋዊ ስብሰባ ላይ ተገለፀ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተሰራውን የኦዲት ግኝት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ጆሎጂካል ሰርቬይ መ/ቤት ምላሽ ሊሰጥባቸው ይገባል ያላቸውን ጥያቄዎችን ለተቋሙ ኃላፊዎች አቅርቧል፡፡
መ/ቤቱ በደንብና መመሪያ መሠረት ሊያወራረድ የሚገባው በድምሩ ብር 5,648,757.94 አለመወራረዱን፤ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት ድረስ የቆየ ብር 50,897.12 ተከፋይ ሒሳብ መኖሩን፤ በተለያዩ የሂሳብ መደቦች ትክክለኛ ባልሆነ አግባብ ተመዝግበው መገኘታቸው፤ ከመ/ቤቱ ለለቀቁ ሠራተኞች ላልሠሩበት ደመወዝ ብር 9,133.67 ተከፍሎ መገኘቱ እና በበጀት አጠቃቀም ከ10% በላይ ከመደበኛ በጀት ብር 12,616,587.16፣ ከውስጥ ገቢ በጀት ብር 29,760,195.15 እና ከካፒታል በጀት ብር 511,011.64 በድምሩ ብር 42,887,793.95 ሥራ ላይ አለመዋሉ ኦዲቱ በኦዲት ግኙቱ ተገልጿል፡፡
ከንብረት አያያዝና አወጋገድ ጋር በተያያዘ በመ/ቤቱ አገልግሎት የሚሰጡና የማይሰጡ ንብረቶች ተደበላልቀው የሚገኙ መሆናቸው፣ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት የሚሰጡ 16 የውሃ ማሞቂያዎች፣ 1 የኮንፈረንስ ጠረጴዛ እና 2 ፋን ቬንትሌተሮች ተቀምጠው የሚገኙ መሆኑ፤ ከ10 ያላነሱ አገልግሎት ላይ መዋል የሚችሉና ሊወገዱ የሚገቡ ተሸከርካሪዎች መገኘታቸውን እና መ/ቤቱ የሥጋት ምንጮች ዳሰሳ ፍተሻ ያላካሔደ መሆኑን የኦዲት ግኝቱ የሚያሳይ በመሆኑ ለእነዚህና ለሌሎችም ጥያቄዎች መ/ቤቱ በኦዲት ግኝቶቹን መሠረት በማድረግ የወሰዳቸውን የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲያስረዳ ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ ጆሎጂካል ሰርቬይ የግዢና ፋይናንስ ተወካይ አቶ ዘውዱ ንጉሴ በሰጡት ምላሽ የ5.6 ሚሊዮን በላይ ያልተወራረደ ሒሳብን በተመለከተ ወደ 5 ሚሊዮን የሚሆነው ተሰብሳቢ ሒሳብ እንዲወራረድ ማድረጋቸውንና ቀሪ 5 መቶ ሺህ የሚሆነው ሒሳብ ያልተሰበሰበ ሲሆን ይህም በህግ ተይዘው እየታዩ መሆናቸውን፤ የቆዩ ለረጅም ዓመታት ተንጠልጥለው የነበሩ ተከፋይ ሒሳቦች ሙሉ ለሙሉ መዘጋታቸውን፤ ከሒሳብ አመዘጋገብ ጋር በተያያዘ የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገርና የሙያ ድግፍ በመጠየቅ የተለያዩ የማስተካከያ እርምጃዎች መወሰዳቸውንና እስከ ሰኔ 2011 መጨረሻ እልባት ለመስጠት እየሰሩ እንደሚገኙ፤ ስራ ለቀው ደመወዝ ከተከፈላቸው ሠራተኞች ውስጥም ክትትል በማድረግ ለሁለት ሠራተኞች ተከፍሎ የነበረ ብር 2119.37 እንዲመልሱ መደረጉንና የቀሪ 3 ሠራተኞች ብር 6614.30 በህግ ሒደት ላይ መሆኑን እና የበጀት አጠቃቀም በተመለከተም መ/ቤቱ ለረጅም ዓመታት ያለበትን የበጀት አጠቃቀም ችግር ለመፍታት በ2011 ዓ.ም ማሻሻያ አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጆሎጂካል ሰርቬይ ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ሁንዴ መልካ በሰጡት ምላሽ ንብረቶችን ለማስወገድ የሚወስደው እርምጃ በሚፈለገው ልክ ፈጥኖ ማከናወን ባይቻልም ኮሚቴ በማቋቋም አብዛኞቹን የሚወገዱ ንብረቶች ማስወገድ መቻላቸውን፤ በኦዲት ግኝቱ የተመላከቱትን የውሃ ማሞቂያና የኮንፍረንስ ጠረንጴዛ መስወገዳቸውን፣ ቬንትለተሮችን ለማስወገድ እየተሠራ እንደሚገኝና ተሸከርካሪዎችንም ከመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር በመነጋገር እያስወገዱ እንደሚገኙ፤ የስጋት ምንጮችን ዳሰሳ ስትራቴጂ ማዘጋጀታቸውንና በየሥራ ክፍሉ ተግባራዊ በሚሆንበት ሁኔታ ላይ እየሠሩ እንደሚገኙ ገልፀው በአጠቃላይ በኦዲት ግኝት የተመላከቱትን ችግሮች ለማስተካከል በትኩረት እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው በህግ አግባብ ሊፈቱ የሚገቡ ጉዳዮች በህግ ተይዘው እየታዩ እንደሚገኙና በተቋሙ በተለይም ከንብረት አያያዝ ጋር በተያያዘ የአቅም ክፍተት በመኖሩ ክፍተቱን ለመሙላት የተለያዩ የማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድ ለውጥ ለማምጣት እየሠሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰጡት አስተያየት መ/ቤቱ የኦዲት ግኝትን መሠረት አድርጎ የሰራቸው ሥራዎች የሚያስመሰግነውና ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው እንደሆነ በመግለፅ ተቋሙ ሠራተኞች ተቋሙን ሲለቁ ለፋይናንስ የሥራ ክፍል በወቅቱ ባላሳወቁ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ፤ ማስተካከያ ተደርጎባቸዋል የተባሉ ጉዳዮች በድርጊት መርሃ ግብር ተደግፈው መፈፀማቸውን ሊረጋገጥ እንደሚገባ፤ የንብረት አወጋገድና አያያዝ ላይ እየታዩ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እና በጀቱንም በአግባቡ ሊያቅድና ተፈፃሚነቱን ሊያረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በሰጡት አስተያየት ተቋሙ ለኦዲት ግኝት የሰጠውን ትኩረት አበረታች መሆኑን ጠቅሰው በኦዲቱ በታዩ ግኝቶች ላይ የድርጊት መርሃ ግብር አዘጋጅተው የማስተካከያ እርምጃዎች መውሰዳቸውን ነገር ግን በተሰብሳቢ ሒሳብ በኩል ተቋሙ ቀሪ ያልተሰበሰበ ሒሳብ 5 መቶ ሺህ ብር እንደቀረ ቢገልፅም በክትትል ኦዲት ማረጋገጫ እስከሚቀርብ ጊዜ ድረስ ቀሪ ያልተሰበሰበ ወደ 1.5 ሚሊዮን ብር እንደሚቀር፤ ከሒሳብ አመዘጋገብ ጋር በተያያዘ ለማስተካከል ቢሞከርም በአዲስ መልክ ችግሩ ተመልሶ እየታየ በመሆኑ በዘላቂነት ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ፤ ከንብረት አኳያም ማስተካከያ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ያሉ ቢሆንም መንግስት ባወጣው የንብረት አስተዳደር፣ አያያዝና አጠቃቀም መመሪያ መሰረት ማስተካከያዎች ማድረግ እንዲሁም መ/ቤቱ ስራውን በቂ በሆነ አግባብ መፈፀም የሚያስችለውን እቅድ በማቀድ የበጀት አጠቃቀሙን ሊያሻሽሉ እንደሚገባ ተናረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ የሱፍ መሐመድ በመጨረሻ በሰጡት አስተያየት ተቋሙ የኦዲት ግኝትን መሠረት በማድረግ የወሰዳቸውን የማስተካከያ እርምጃዎች አድንቀው በቀጣይ ይበልጥ በንብረት አያያዝ በበጀት አጠቃቀምና በሌሎች በኦዲቱ የተመላከቱ ችግሮችን ለመፍታት ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *