የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተለያዩ ይዘቶች ያሏቸው ለትምህርት ድጋፍ የሚሆኑና ለጠቅላላ እውቀት የሚረዱ በቁጥር 1,589 የሚሆኑ መጻህፍትን ለአብርሆት የህዝብ ቤተ መጻህፍት በስጦታ አበረከተ፡፡
መ/ቤቱ ያደረገውን የመጻህፍት ስጦታ በአብርሆት የህዝብ መጻህፍት ቤት በመገኘት ያበረከቱት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ሲሆኑ የቤተ መጻህፍቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ታሪኩ መጻህፍቱን ተረከብዋል፡፡
መንግስት የሀገሪቱን የተማረ የሰው ኃይል ከማጠናከር አንጻር የህረተሰቡን የንባብ ባህል ለማሳደግ እያደረገ ያለውን ጥረት በማድነቅ አጭር ንግግር ያደረጉት ክብርት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ የመጻህፍት ስጦታው በተለይም ቤተ መጻህፍቱ በርካታ አንባብያን ያሉት በመሆኑ ይህንኑ ጥረት ለማገዝ የተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ቤተ መጻህፍት የሠራተኞቹን ሙያዊ ክህሎትንና እውቀት ሊያግዙ የሚችሉ በርካታ መጻህፍት ያሉት መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ጨምረው የጠቀሱት ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ወደፊትም የህዝብ ቤተ መጻህፍቱን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የመጻህፍት ስጦታውን የተረከቡት የቤተ መጻህፍቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ታሪኩ በበኩላቸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለቤተ መጻህፍቱ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው ከመ/ቤቱ የተበረከቱት መጻህፍት በተለይም ቤተ መጻህፍቱ በአካውንቲንግና በመሰል የትምህርት ዘርፎች ያሉበትን የመጻህፍት እጥረት ከማቃለል አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመጻሀፍት ርክክብ ስነስርዓቱ ላይ ቤተ መጻህፍቱ ለመ/ቤቱ የድጋፍ እውቅና የምስክር ወረቀት አበርክቷል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከዋነኛው የኦዲት ተግባር በተጓዳኝ በተለያዩ ህብረተሰብ አቀፍ ማህበራዊና ልማታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በመሳተፍ የተለያዩ ጠንካራ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ይታወቃል፡፡