የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለፋይናሽያል ኦዲተሮች በፋይናሽያል ኦዲት ማንዋል ላይ ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡
በሥልጠና ማስጀመሪያ መርሃግብሩ ላይ የተገኙት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ለሰልጣኝ ኦዲተሮች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በመልዕክታቸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በየጊዜው ወቅቱን ታሳቢ ያደረገ ሥልጠና ለኦዲተሮች መስጠት አንዱ የሥራው መሠረታዊ አካል መሆኑን አውስተው ይህ ሥልጠናም የኦዲተሩን ሙያዊ ክህሎት ለማሳደግ እና የኦዲት ጥራት ደረጃን ይበልጥ ከፍ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ሠልጣኞች በሥልጠና ቆይታቸው ወቅት ሥልጠናውን በአግባቡ በመከታተል ለተቋሙ ተልዕኮ መሳካት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
የመ/ቤቱ የትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክተር አቶ አበራ ታደሰ በበኩላቸው ሥልጠናው ከእቅድ እስከ ሪፖርት ያሉ ማለትም የዕቅድ ዝግጅት፣ የኦዲት ክንውን፣ ሪፖርት ዝግጅት እና ክትትል ሥራዎች ላይ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሥልጠናው ዓላማም በመ/ቤቱ የኦዲት ጥራት ዳይሬክቶሬት እና በአፍሮሳይ-ኢ /AFROSAI-E/ የተለዩ ችግሮች ላይ የእርምት እርምጃዎችን ለመውሰድ፣ በፋይናሽያል የኦዲት ማንዋል ላይ ከዚህ ቀደም ሥልጠና ላልወሰዱ ሠራተኞች ግንዛቤ ለመፍጠር፣ በሒሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን ያሉ ልምዶችን ለመለዋወጥ እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን /IT Tools/ በኦዲት ሥራው በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል አቅም ለመፍጠር መሆኑን አቶ አበራ አስረድተዋል፡፡
ሥልጠናው በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የኦዲት አሰልጣኞች እና ከሒሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን በመጡ ባለሙያዎች አማካኝነት በሦስት ዙር ለ5 ቀናት ከጀማሪ ኦዲተር እስከ ዳይሬክተር ደረጃ ላሉ ከ350 በላይ ኦዲተሮችና የስራ ኃላፊዎች እንደሚሠጥ ታውቋል፡፡