የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤት ኦዲተሮች በተለያዩ የኦዲት አሠራሮች ዙሪያ ስልጠና ሰጠ፡፡
ከጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ.ም አስከ ጥቅምት 16 ቀን 2016 ዓ.ም በቆየው ስልጠና 40 የሚሆኑ የአስተዳደሩ ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡
ስልጠናው በዋናነት በአዲሱ የፋይናንሽያል ኦዲት ማንዋል ላይ ያተኮረ ሲሆን ሰልጣኞች በስልጠናው ወቅት ያደረጉት ተሳትፎም አበረታች መሆኑን ከመ/ቤቱ የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
መ/ቤቱ ለእራሱ ኦዲተሮች እያደረገ ካለው ተከታታይ የአቅም ግንባታ ስራ በተጓዳኝ የተለያዩ የክልል መንግስታትና የከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች አመራሮችንና ባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ በርካታ ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል፡፡