በጤና ሚኒስቴር ስር በሚገኘው በፌዴራል የኤች.አይ.ቪ. ኤድስ መቆጣጠሪያና መከላከያ ጽ/ቤት አማካይነት ለኤች.አይ.ቪ. ኤድስ መቆጣጠሪያና መከላከያ የሚውለው ፈንድ አጠቃቀምና አፈጻጸም በርካታ ጉድለቶች ያሉበት በመሆኑ ተገቢ የአጠቃቀምና አፈጻጸም ሥርዓት ሊኖረው እንደሚገባ ተጠየቀ፡፡
ይህ የተጠየቀው የኢ.ፌ.ዴ ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ጽ/ቤቱ ከ2011 እስከ 2013 በጀት ዓመታት ለኤች.አይ. ቪ. ኤድስ መቆጣጠሪያና መከላከያ ያዋለውን ፈንድ አጠቃቀምና አፈጻጸም በተመለከተ በ2013/2014 በጀት ዓመት ያካሄደውን የክዋኔ ኦዲት መሰረት በማድረግ በግኝቶቹ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ህዝባዊ ይፋዊ ውይይት ባካሄደበት መድረክ ነው፡፡
ለኤች.አይ.ቪ. ኤድስ መቆጣጠሪያና መከላከያ የዋለውን ፈንድ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመጠቀም የሚያስችል የአሠራር ስርዓት ያልነበረ መሆኑና በወቅቱ አገልግሎት ላይ መዋል የሚገባው ገንዘብ ያለአግባብ ለረጅም ጊዜ በባንክ መቀመጡ፣ የአፈጻጸም ክትትልና ቁጥጥር አሠራሩም ዝቅተኛ መሆኑ፣ ለኤች.አይ.ቪ. ኤድስ መቆጣጠሪያና መከላከያ ለክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ከተሰጠው ፈንድ በድምሩ ከብር 3.3 ሚሊዮን በላይ የሆነ ገንዘብ በስድስት ክልሎችና በአንድ የከተማ መስተዳደር ያልተወራረደና ተመላሽ ያልተደረገ መሆኑ እና ወቅታዊና ችግር ፈቺ ጥናቶችን በማድረግ የስራውን ውጤታማነት ማረጋገጥ ያለመቻሉ በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡
በተጨማሪም ዘርፉን በተመለከተ ከውጭ ድጋፍ ፈንድ ለመላቀቅ የሚያስችል ዘላቂ ሀገራዊ ሀብት ለማሰባሰብ ውጤታማ አሠራር ያለመዘርጋቱና ጉዳዩ ለባለድርሻ አካላት ተደራሽ ያለመደረጉ፣ የኤች.አይ.ቪ. ኤድስ ስርጭትን ለመግታት የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ መምጣታቸው፣ ተገቢና ወቅታዊ የሆኑ የአሠራር ደንብና መመሪያዎች ያለመተግበራቸው፣ የመድሃኒት ግዥና አቅርቦት ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ መከታተልና ማረጋገጥ የሚያስችል በቂ አሠራር ያለመኖሩ እና ሌሎችም በኦዲቱ ወቅት የታዩ ክፍተቶች በመሆናቸው ግኝቶቹን ለማስተካከል የተወሰዱ እርምጃዎች እንዲብራሩ ተጠይቋል፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የጤና ሚኒስትር ክብርት ዶ.ር ሊያ ታደሰ በመድረኩ በተነሱት የኦዲት ግኝቶች ላይ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ጽ/ቤቱ በአዲስ አደረጃጀት የሚኒስቴር መ/ቤቱ አንድ የስራ ክፍል ሆኖ የተደራጀ እንደመሆኑ የኦዲት ሂደቱ ስራቸውን ለማጠናከር ከፍተኛ ድጋፍ የሰጣቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ የኤች.አይ.ቪ. ኤድስ መቆጣጠሪያና መከላከያ ስትራቴጂ ተነድፎ እየተተገበረ መሆኑንና አዲሱንና የተከለሰውን አጠቃላይ የሀገሪቱ ጤና ፖሊሲ ለማጸደቅ እና ይህንኑ ተከትሎም የኤች.አይ. ቪ. ኤድስ ሀገራዊ ፖሊሲ ነድፎና አጸድቆ ለመተግበር በሂደት ላይ መሆናቸውን ዶ/ር ሊያ ታደሰ ጠቅሰዋል፡፡
ለኤች.አይ. ቪ. ኤድስ መቆጣጠሪያና መከላከያ ፕሮግራም ከአለም አቀፍ ግሎባል ፈንድ እና ከሌሎች ደጋፊ አካላት የሚመጣው ፈንድ ለተለያዩ ግብአቶች እና ለመድሀኒት ግዥ እንዲሁም ለምርመራ ሂደቶች የሚውለው ፈንድ በማዕከል ደረጃ የሚተገበር ቢሆንም ወደ ክልሎች የሚወርደውን ገንዘብ በትክክል በስራ ላይ ስለመዋሉ የማረጋገጥ ስራ ክፍተት ያለበት እንደሆነ ጠቁመው ይህን ክፍተት ለመቅረፍ ተጠያቂነትን የማስፈንና የክትትልና ቁጥጥር ስርዓቱን ከማጠናከር ጀምሮ ሌሎች የመፍትሔ እርምጃዎችን ለመውሰድ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በተለያዩ ዓለም አቀፋዊና የሀገር ውስጥ ሲሚናሮችና ወርክሾፖች ላይ ተሳትፎ መኖሩን ጨምረው የጠቆሙት ክብርት ሚኒስትሯ በመድረኮቹ የተገኙ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን ለሚመለከታቸው አካላት በማድረስ ሂደት ክፍተቶች መኖራቸውን ገልጸው የኤች.አይ.ቪ. ኤድስ ስርጭትን ለመግታት የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጥ ጥረት ቢኖርም ይህንኑ ስራ የተለያዩ ሚዲያዎችን አሳትፎ ለማጠናከር ም/ቤቱ የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡
በጤና ሚኒስቴር አመራሮች በተሰጡ ምላሾች ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ባለድርሻ አካላት አፈጻጸሞችን በወቅታዊ ሪፖርት ከማሳወቅ ጀምሮ በፈንድ አጠቃቀምና ቁጥጥር እንዲሁም በግንዛቤ ማስጨበጥ ሂደት ያሉትን ክፍተቶች በአፋጣኝ በመፍታት ስራውን በአግባቡ መምራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው የማስተካከያ እርምጃ የተወሰደባቸውን ግኝቶች በክትትል ኦዲት የማረጋገጡ ስራ በቀጣይ እንደሚካሄድ ጠቁመው በተለይ ለፕሮግራሙ የሚውለው ፈንድ ተገቢ የሆነ የአጠቃቀም፣ የአፈጻጸም፣ የክትትልና የቁጥጥር ሰንሰለት ያልተዘረጋለት በመሆኑ መፍትሔ እንዲበጅለት ጠይቀዋል፡፡
የኤች.አይ. ቪ ቫይረስ ስርጭት እየጨመረ ስለመምጣቱ መረጃዎች የሚያሳዩ በመሆናቸው በመከላከሉና በመቆጣጠሩ ሂደት ልዩ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አክለው የገለጹት ክብርት ዋና ኦዲተሯ በዕቅድ አፈጻጸም፣ በግንዛቤ ማስጨበጥ፣ ከክልሎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ሊኖር በሚገባው ወጥ የሆነ የቅንጅት አሠራር፣ በአዋጅ እና በመመሪያ ትግበራ፣ በመረጃ አሰባሰብና ስርጭት እንዲሁም በአደረጃጀት ረገድ ያሉትን ችግሮች ሚኒስቴር መ/ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እንዲያስተካክል አሳስበዋል፡፡
የኦዲት ግኝቶቹ የኦዲት ናሙና እንደመሆናቸው በዘርፉ ያሉ ሌሎች ተቋማዊ ችግሮችንም ጭምር በዝርዝር በማየት መቅረፍ እንደሚገባ በማጠቃለያ አስተያየታቸው የጠቆሙት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ ፍትሀዊና ተገቢ የሆነ የፈንድ አስተዳደርና አጠቃቀም እንዲኖር እና በግንዛቤ ማስጨበጥ፣ በኤች.አይ.ቪ. ኤድስ መከላከል፣ በክትትልና ቁጥጥር፣ በፈንድ አሰባሰብ ስትራቴጂ ዝግጅትና ትግበራ ሂደት እንዲሁም በሌሎች ችግሮች ላይ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱና ለትግበራውም ተከታታይ ሪፖርቶች እንዲቀርቡ በማሳሰብ የማስተካከያ እርምጃ አወሳሰድ የድርጊት መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ በ10 ቀናት ውስጥ እንዲቀርብ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡