የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከኦድዋስ (Organization for Development of Women and Children in Ethiopia: ODWaCE) ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የአካታችነት ትግበራን የተመለከተ ሥልጠና ለመ/ቤቱ የኦዲት ማኔጅመንት አባላት ተሰጥቷል፡፡
በስልጠናው መክፈቻ ላይ የተገኙት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ ባስተላለፉት መልዕክት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የአካታችነት ትግበራን በሚመለከት ለሌሎች አርአያ በመሆን ጉዳዩን ከኦዲት አንጻር መምራት የሚጠበቅበት በመሆኑ የአካታችነት ጉዳይ በመ/ቤቱ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል፡፡
አያይዘውም የአካታችነት ሥልጠና ለኦዲተሮች በተለይም ኦዲቱን ለሚመሩ አመራሮች መሰጠቱ በኦዲት ሥራ ውስጥ የተለያዩ የአካታችነት አመለካከቶች እንዲካተቱ፣ በአካታችነት ጉዳይ ላይ ያለው የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንዲጎለብት፣ የአካታችነትን መርህ በሁሉም የመንግስት ፕሮግራሞች፣ ፕሮጀክቶችና የተለያዩ አሠራሮች ውስጥ በአግባቡ መተግበራቸውን መ/ቤቱ በሚያካሂደው ኦዲት መከታተል የሚያስችል አቅም ለመፍጠር እንዲሁም የኦዲቱ ሥራ ከህብረተሰቡ ግብ ጋር እንዲጣመር ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኦድዋስ (ODWaCE) ኤክስኪየቲቭ ዳይሬክተር አቶ አያሌው እጅጉ በበኩላቸው ሥልጠናው ከዚህ ቀደም ለመ/ቤቱ ከተሰጠው የአካታችነት ሥልጠና ቀጣይ አካል የሆነና ይበልጥ ወደትግበራ ለመግባት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከየካቲት 17-18 2017 ዓ.ም ለ2 ቀናት በተሰጠው ስልጠና ስርዓተ ጾታ ተኮር በጀት አመዳደብ፣ የአካቶነት አሰራርና የተጠያቂነት መንገድ እና በፋይናሽያልና ህጋዊነት ኦዲት እንዲሁም በክዋኔ ኦዲት ውስጥ አካቶነትን በተመለከተ በትግበራው የሚካተቱ ጉዳዮችና ጉዳዮቹም እንዴት እንደሚካተቱ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ፍሬ ሀሳቦች እንደተሸፈኑ ከትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ቀደም ካሉት ጊዜት ጀምሮ በአካታችነትና በትግበራው ዙሪያ ተመሳሳይ ስልጠናዎችን አዘጋጅቶ ለመ/ቤቱ አመራርና ሠራተኞች እየሰጠ ይገኛል፡፡