News

የመ/ቤቱ የእቅድ አፈጻጸም ግምገማና የእቅድ ዝግጅት መድረክ ተካሄደ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አመታዊ የእቅድ አፈጻጸም ግምገማና የእቅድ ዝግጅት መድረኩን ሁሉንም የመ/ቤቱን ሰራተኞች ባሳተፈ መልኩ ከየካቲት 23-27፤2012 ዓ.ም በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ አከናወነ፡፡ በመድረኩ መ/ቤቱ የ2011/2012 የኦዲት ዘመን ማለትም ከመጋቢት 01/2011 ዓ.ም እስከ ጥር 30/2012 ዓ.ም ድረስ የተከናወነውን የኦዲት ስራና የ2012 በጀት አመት የ7 ወራት የድጋፍ ዘርፍ ስራዎች እቅድ አፈጻጸምን የገመገመ ሲሆን በ2012/2013 የኦዲት ዘመን የሚሰሩ የኦዲት ስራዎችንና በ2013 በጀት አመት የሚተገበሩ የድጋፍ ዘርፍ ስራዎችን እቅድ አዘጋጅቷል፡፡

በመድረኩ መክፈቻ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በ2011/2012 የኦዲት ዘመን ካለፉት አመታት በበለጠ መጠን የኦዲት ስራዎች ላይ መዘግየት መታየቱን ገልጸዋል፡፡ ለመዘግየቱ አስተዋጽኦ ያደረጉ ከመ/ቤቱ አቅም በላይ የሆኑ ውጫዊ ምክንያቶች እንደነበሩ የጠቀሱት ክቡር ዋና ኦዲተሩ ከክትትል ማነስ እንዲሁም በተወሰነ ደረጃ ከሎጅስቲክስ ጋር የተያያዙ ውስጣዊ ምክንያቶችም አንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

ክቡር ዋና ኦዲተሩ በአሁኑ ወቅት ገና በመስክ ላይ ካሉ የኦዲት ስራዎች አንስቶ የመውጫ ስብሰባ እየተጠበቀባቸው እስካሉ ኦዲቶች ድረስ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ ያሉ አንዳንድ የዘገዩ ኦዲቶች ቢኖሩም  በአጠቃላይ ሲታይ የመ/ቤቱ የኦዲት እቅድ አፈጻጸም ጥሩ እንደነበረ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም በቀጣይ የእቅድ አፈጻጸም ወቅት ከታዩት ውስጣዊ ክፍተቶች ትምህርት በመውሰድ የበለጠ አፈጻጸም ማስመዝገብ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የመንግስትና የህዝብ ሀብት አጠቃቀም ግልጽነት የተላበሰ እንዲሆንና ተጠያቂነትና ፍትሀዊነት እንዲኖር የበለጠ መስራት ይጠበቅብናል ያሉት ክቡር አቶ ገመቹ የመ/ቤቱ የ2012/2013 የኦዲትና የድጋፍ ዘርፍ ስራዎች እቅድ እንዲሳካ ሁሉም ሰራተኛ በተሰጠው ኃላፊነት ልክ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል በማለት አስገንዝበዋል፡፡ የነበረውን አፈጻጸምም ከስራ ክፍል እስከፈጻሚ ሰራተኛ ድረስ በጥልቀት መገምገም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ለአምስት ቀናት በየቆው በመድረክ ላይ በሁሉም የመ/ቤቱ የኦዲትና የድጋፍ ዘርፍ የስራ ክፍሎች ሊሰሩ ታቅደው የነበሩ ተግባራት አፈጻጸም ሪፖርት ቀርበው ውይይት ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የነረበውን የእቅድ አፈጻጸም፣ የመ/ቤቱን ስትራቴጂክ እቅድ እንዲሁም በኦዲቱ ዘርፍ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አቅጣጫ የተሰጠባቸው ርዕሰ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ ሰራተኞችን ባሳተፈ መልኩ በኦዲቱና በድጋፍ ዘርፉ በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎች ታቅደው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *