ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በህገ መንግሥቱና በማቋቋሚያ አዋጁ የተሰጡትን ተልዕኮዎች ለመወጣት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ የመንግሥት ገንዘብና ንብረት በአግባቡ ሥራ ላይ አንዲውልና የታለመውን ውጤት እንዲያስገኝ የመንግሥት መ/ቤቶች አፈፀፃም … እንዲጎለብትና ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲጠናከር እንደዚሁም መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል:: በዚህ ረገድ በተለይ ባለፉት አምስት የስትራቴጅክ ዕቅድ አመታት የፋይናንስና ህጋዊነት ኦዲቱን ሽፋን ወደ 100% ማሳደግ ከመቻሉም በላይ በየዓመቱ የሚወጡ የክዋኔ ኦዲት ሪፖረቶችንም ቢሆን ወደ 18 ገደማ ማሳደግ ተችሏል፡፡ የኦዲት ሸፋንን በተመለከተ በፋይናንስና ህጋዊነት ኦዲትም ሆነ በክዋኔ ኦዲት ረገድ የተገኘው ውጤት መልካም ሊባል የሚቻል ቢሆንም በኦዲት ጥራት ረገድ ግን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ ይገባል፡፡ በሌላም በኩል የተሰጡ የኦደት ማሻሻያ ሀሳቦች በትክክል ለመተግበራቸው ወይም እርምጃ ለመወሰዱ ክትትል የሚደረግ ቢሆንም እርምጃዎች በመወሰዳቸው ምክንያት የመጣው ውጤት ወይም ፋይደ በሚገባ ተገምግሞ እየተለካ አይደለም፡፡

በመሆኑም ከየካቲት 2008 እስከ ታህሣሥ 2013 የተዘጋጀው ስትራቴጅክ ዕቅድ አስከአሁን የተገኘውን ውጤት ማስጠበቅ ዋንኛው ጉዳይ ሆኖ የሠራተናውን ብቃትና ክህሎት ማሳደግ፤ የኦዲት ጥራትን ማሻሻል፤ የኦዲት ማሻሻያ አስተያየቶች በመተግበራቸው የተገኘውን ፋይደ ለክቶ ማወቅ፤ የክዋኔ ኦዲትን ሽፋን ማሳደግ፤ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና አስተዳደር ማሻሻልና የመረጃ ሥርዓት ብቃትና ጥራት ማሻሻል ትኩረት የተሰጠቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለመ/ቤታችን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለሠራተኞች ያደረገው የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ማሻሻያና መ/ቤቱ ምቹ የሥራ አካባቢ ተፈጥሮለት ተልዕኮውን እንዲወጣ ለማስቻል ያስገነባለት ደረጀውን የጠበቀ ህንፃና ዕርዳታ ሰጪ አካላት ለመ/ቤቱ የአቅም ግንባታ ሥራ  እያደረጉ ያለው ድጋፍ የሠራተኛውን ተነሳሽነትና ስትራቴጀው ያተኮረባቸውን ጉዳዮች ለማሳካት ዓይነተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ በተለይ ሠራተኛው ሊገነዘብ የሚገባው ጉዳይ መንግሥት ለዚህ መ/ቤት በዚህ ልክ ትኩረት የሰጠበት ምክንያት ነው፡፡

እንደሚታወቀው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሀገሪቱ በ2017 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ ግዙፍ የልማት ሥራዎች ለማከናወን ያቀደችበትና ከዚሁ የልማት ሥራ በተጓዳኝ ተጠያቂነትና ግልጽነት እንደዚሁም መልካም አስተዳደርን ለማስፍን ትንቅንቅ የሚደረግባት ወቅት ነው፡፡ በሌላ በኩል ለሁለተኘው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማስፈጸሚያ የተመደበው ሀብት እጅግ ግዙፍ እንደሆነም ይታወቀል፡፡ ይህ ለልማት የተመደበው ሀብት በቁጠባና በአግባቡ ለታለመለት ዓለማ መዋሉን መንግሥት ማረጋገጥ ይፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው ትኩረት ሰጥቶ ጠንካራ የመንግሥት ኦዲት ሥርዓት መገንባት የወሰነው፡፡

ስለሆነም በየደረጀው የሚገኝ ሠራተኛና ሀላፊ የመንግሥትን የትኩረት መነሻ በሚገባ ተረድቶ በዚህ ስትረቴጅክ ዕቅድ ውስጥ የተቀመጡትን ዓለማዎችና ግቦች ለማስካት በቁርጠኝነት፤ በመተባበርና በመደጋገፍ ከምን ጊዜውም በላቀ ተነሳሽነት የስትረቴጅክ ዕቅዱ ባለቤት በመሆን የተሰጠንን ተልዕኮ ለማሳካት እንዲንረባረብ በአፅንኦት አስገነዝባለሁ፡፡

አመሰግናለሁ፡፡