ኦዲት ለዜጎች ተጠቃሚነት

ፌዋኦ: ጥቅምት 11/2018:- የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች የተበጀተላቸውን የህዝብ ሃብት በአግባቡ መጠቀማቸውን ለማረጋገጥ የኦዲት ባለድርሻ ተቋማት በባለቤትነትና በሃላፊነት ተልዕኳቸውን እንዲፈጽሙ የሚያስችላቸውን የጋራ እቅድ ላይ ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወያይተዋል::

የጋራ እቅዱን ያቀረቡት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር) በ2017 በጀት አመት ከቀደሙት አመታት የተሻለ ቅንጅታዊ የክትትል፣ የቁጥጥርና የድጋፍ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀው በ2018 በጀት አመት እቅድም ሊሰሩ የታሰቡ ቁልፍ ተግባራትን ለኦዲት ባለድርሻ አካላት የትብብር ፎረም አቅርበዋል::

በመድረኩ የተገኙት የኦዲት ባለድርሻ አካላት የሥራ ኃላፊዎች ባነሱት ሀሳብ ባለፈው በጀት አመት ፎረሙ በቅንጅት ውጤታማ የሆኑ ሥራዎችን መስራቱን አስታውሰው በ2018 በጀት አመትም የተሻለ ለመሥራት የክትትልና የቁጥጥር ሥራቸውን ይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እና በአቅም ግንባታና በአሠራር ሊፈቱ የሚገቡ ጉዳዮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ፎረሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ በክትትልና ቁጥጥር ሥራው ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ መምጣቱን ገልጸው በቀደሙት አመታት በተሰሩት የኦዲት የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች ለመንግስት የፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ በርካታ ጠቃሚ ጉዳዮች አስተዋጽኦ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል፡፡

ዋና ኦዲተሯ አክለውም በቀጣይ የኦዲት ሥራ ይበልጥ ውጤት እንዲያስመዘግብ ሥራን ቆጥሮ ከመስራት፣ ከአቅም ግንባታ፣ ተጠያቂነት ከማረጋገጥ እና ሊሰበሰቡ የሚገቡ ተሰብሳቢ ሂሳቦች ላይ የተጠናከረ ሥራ ከመስራት አንጻር የተጠናከረ ሥራ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር የሺመቤት እንደተናገሩት የፎረሙ ዓላማ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተሠሩ የኦዲት ሪፖርቶች መሰረት ተቋማት የተበጀተላውን የህዝብ ሃብት ለታለመለት ዓላማ መንግስት ባወጣላቸው ህጎችን ተከትለው ስራ ላይ ማዋለቸውን የክትትልና የቁጥጥር ስራ በጋራ በመስራት ተጠያቂነትን ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል::

ሰብሳቢዋ አክለውም ባለፈው በጀት ዓመት በፌዴራል መ/ቤቶች ውስጥ በተገኙ የኦዲት ግኝቶች ላይ በዋና ኦዲተሮችና በቋሚ ኮሚቴ አባላት ምክረ ሃሳብ መሰረት ተገቢውን የእርምት እርምጃዎች መወሰዳቸውን አስታውሰው በዚህም በርካታ የህዝብ ሃብትን ማስመለስና ብልሹ አሰራሮችን ማስወገድ እንደተቻለም አብራርተዋል:: በተጨማሪም ባለፈው በጀት ዓመት የተስተዋሉ ችግሮች ስጋቶችና የመፍትሄ ሃሳቦችን አቅርበዋል:: የኦዲት ባለድርሻ አካላትም ለእቅዱ ተጨማሪ ግብዓት የሚሆኑ ዝርዝር ሃሳቦችን በማንሳት የተወያዩ ሲሆን በመድረኩ የቀረበውን የ2018 የጋራ እቅድን በማፅደቅ ፎረሙ ተጠናቋል::

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው