የኦዲት አገልግሎቶች
የሂሳብ እና ህጋዊነት ኦዲት
የሂሳብ ወይም የፋይናንሽያል ኦዲት መንግስት የፌዴራል ተቋማት የተቋቋሙበትን ተልዕኮ በአግባቡ እንዲያሳኩ የሚመድበውን ዓመታዊ መደበኛ በጀት እና ለክልል መስተዳድሮች የሚደለደሉ የድጎማ በጀቶች እንዲሁም ከለጋሽና አበዳሪ የተለያዩ ተቋማት የሚገኝ ገንዘብ በትክክል በገቢና በወጪ መዝገብ የተመዘገቡና የሚቀርቡ የሂሳብ መግለጫዎችም የመንግስት የሂሳብ አያያዝ ስርዓትን የተከተሉ መሆናቸውን እንዲሁም ከሚያስፈልጉ ሌሎች መረጃዎችና ማስረጃዎች ጋር የተገናዘቡ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚካሄድ የኦዲት ዓይነት ነው፡፡ አስከአሁን ድረስ ከዚሁ ከሂሳብ ኦዲት ጋር ተጣምሮ የሚሰራው የህጋዊነት ኦዲትም የመንግስትና የህዝብ ሀብቶች በየተቋማቱ በስራ ላይ ሲውሉ አግባብነት ያላቸውን ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች የተከተሉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚካሄድ ነው፡፡
የክዋኔ ኦዲት
የክዋኔ ኦዲት መ/ቤቱ ኦዲት የሚያደርጋቸው ተቋማት የስራ አካሄድ እና ሌሎች ሀገራዊ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች የተልዕኮ አፈጻጸም ውጤታማ፣ ኢኮኖሚያዊ አሠራርን የተከተለና የታለመለትን ግብና ውጤት ያስገኘ እንዲሁም በተነደፈው ዕቅድ፣ የሰው ኃይል፣ ንብረትና የገንዘብ አቅም መከናወኑን ለማረጋገጥ የሚካሄድ የኦዲት ዓይነት ነው፡፡
የአካባቢ ሁኔታ ኦዲት
የአካባቢ ኦዲት አንዳንዴ ከክዋኔ ኦዲት ጋር በጥምረት የሚከናወን ሲሆን ዓላማውም ለአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ተግባራት አስፈላጊውን ትኩረት በመስጠት አንድ አካባቢ በዓለም አቀፍ መስፈርቶች የተወሰነውን የልቀትና የአካባቢ ብክነት ስታንዳርድና ደረጃ የጠበቀ ስለመሆኑ የሚካሄድ የኦዲት ዓይነት ነው፡፡
የመረጃ ስርዓት (IT) ኦዲት
የመረጃ ስርዓት (IT) ኦዲት ከፍተኛ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎትን የሚጠይቅ ሲሆን ተቋማት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የዘረጉት የመረጃ ስርዓት ተገቢውንና ትክክለኛውን መረጃ የሚያመነጭ ወይም የሚሰጥ መሆኑን እንዲሁም ለመረጃ ስርዓቱ በቂ የጥበቃ ስርዓት የተዘረጋና መረጃዎቹም ከአደጋ የተጠበቁ ስለመሆናቸው ለማረጋገጥ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የኦዲት ባለሙያዎች የሚካሄድ የኦዲት ዓይነት ነው፡፡
ልዩ ኦዲት
ልዩ ኦዲት መንግስት የአንድን የመንግስት ተቋም የተለየ የፋይናንሻልና ሌሎች አሰራሮች፣ የሀብትና ንብረት አጠባበቅ ሁኔታ እንዲሁም ሌሎች የሀገራዊ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በልዩ ሁኔታ ለመረዳትና ለማወቅ በሚፈልግበት እና ተገቢ በሆኑ የመንግስት አካላት ኦዲቱ እንዲደረግ በልዩ ሁኔታ ጥያቄ በሚቀርብበት ወቅት በመ/ቤቱ አማካይነት ከመደበኛ የኦዲት መርሀ ግብር በተለየ መልኩ የሚከናወን ሲሆን በአብዛኛው በትላልቅ ተቋማዊና ሀገራዊ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ተመስርቶ የሚካሄድ የኦዲት ዓይነት ነው፡፡
የስርዓተ ጾታ አካታችነት ኦዲት
አሁን ባለው የመ/ቤቱ ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት ይህ ኦዲት ከክዋኔ ኦዲት ጋር በመካተትና የራሱ የሆኑ መስፈርቶች ወጥተውለት የሚካሄድ ሲሆን የመንግስት ተቋማት በተለያዩ መዋቅራዊ ሁኔታቸው፣ አሠራራቸውና ተሳትፏቸው ውስጥ የስራአተ ጾታን ጉዳይ ትኩረት ሰጥተውና በእቅዶቻቸው አካተው ማከናወናቸውንና የሚገባውን የተሳትፎ ደረጃ መስጠታቸውን ለማረጋገጥ የሚካሄድ የኦዲት አይነት ነው፡፡
ሌሎች አገልግሎቶች
የበይነ መረብ አገልግሎት
ፖርታል መዳረሻ
ለኦዲት ነክ ጉዳዮችን ለመከታተልና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማግኘት የተለያዩ መተግበሪያዎቻችንን ከፖርታላችን በመግባት ይመልከቱ፡፡
የአገልግሎት መመሪያዎች
የኦዲት ደረጃዎች (Audit Standards)
በአለምአቀፍ ደረጃዎች መሰረት ኦዲቶችን ለማካሄድ የሚያስችሉ ትክክለኛና አግባብነት ያላቸውን መመሪያዎች /Audit Standards/ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
በተደጋጋሚ የሚጠየቁ ጥያቄዎች
የኦዲት ሂደት ምንድን ነው?
የኦዲት ሂደቱ ሁሉን አቀፍ ግምገማን ለማረጋገጥ እቅድ ማውጣትን፣ የመስክ ስራን፣ ሪፖርት ማቅረብን እና ክትትልን ያካትታል።
ኦዲት ለማጠናቀቅ ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?
የኦዲት ቆይታ በስፋት እና ውስብስብነት ይለያያል፣ በአብዛኛው ከሳምንታት እስከ ብዙ ወራት ሊወስድ ይችላል።
ምን ዓይነት ሰነዶች ያስፈልጋሉ?
በኦዲት ሥራ ወቅት ከኦዲት ተደራጊው አካል የፋይናንስ መግለጫዎች፣ ፖሊሲዎች፣ የአሰራር ሂደቶች እና ተያያዥ ደጋፊ ሰነዶችን ያፈልጋሉ።