ኦዲት ለዜጎች ተጠቃሚነት

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት (ፌዋኦ) በአዲስ መልክ ተሻሽሎ የተዘጋጀውን የህጋዊነት ኦዲት ማኑዋል (Compliance Audit Manual and Working Papers, First Edition 2025) ለማስተዋወቅ የሚረዳ የሁለት ሳምንት ሥልጠና ከየካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ ነው፡፡

የፌደራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከአውሮፓ ሕብረት የሕዝብ ፋይናንስ አስተዳደር ማሻሻያ ድጋፍ (EUSPRE) እና ከቴክኒካል ፋሲሊቲ ዩኒት (TFU) ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይህ ሥልጠና የኦዲት አሰራርን ለማዘመንና ከዓለም አቀፍ ስታንዳርዶች ጋር ለማጣጣም የሚደረገው ጥረት አካል ነው። ይህም ቀደም ሲል የተከናወኑትን የፋይናንሻል እና የክዋኔ ኦዲት ማንዋሎች ማሻሻያ ተከትሎ የተከናወነ ስትራቴጂካዊ ተግባር መሆኑ ተገልጿል።

በሥልጠናው መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ የሕግ ተገዥነት ኦዲት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ወሳኝ መሣሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

ክብርት ዋና ኦዲተሯ አክለውም የሕግ ተገዥነት ኦዲት የመንግሥት ተቋማት የሚመሩባቸውን ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ተከትለው እየሰሩ መሆኑን የሚያረጋግጥና በተጠያቂነት ሥርዓት ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያለው ነው ብለዋል።

አዲሱ የ2025 ማንዋል የኦዲት ዕቅድ ዝግጅት፣ የስጋት ትንተና፣ የማስረጃ አሰባሰብ እና የጥራት ቁጥጥር ሥራዎችን በተቀናጀ መልኩ ለመምራት የሚያስችል መሆኑን ጨምረው የጠቀሱት ክብርት ወ/ሮ መሰረት ሥልጠናው በተግባራዊ ልምምድ (Case Study) ላይ የተመሰረተ መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል። ይህም ኦዲተሮች ዝርዝር መመሪያዎችን ከመከተል ባለፈ የነገሮችን አመክንዮ የመተንተንና ሙያዊ ፍርድ የመስጠት አቅማቸውን እንደሚያሳድገው ገልጸዋል።

በመጨረሻም ለማንዋሉ ዝግጅትና ለሥልጠናው መሳካት ድጋፍ ላደረጉት የአውሮፓ ሕብረት እና የቴክኒክ ቡድን አባላት ምስጋናቸውን አቅርበው ሰልጣኞች የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ የጥራት አምባሳደርና ለሥራ ባልደረቦቻቸው መሪ እንዲሆኑ አሳስበዋል።

በሁለት ዙሮች እየተሰጠ ባለው ስልጠና የመሥሪያ ቤቱ  የኦዲት ዳይሬክተሮች እና ሥራ አስኪያጆች እንዲሁም ከፍተኛ ኦዲተሮች በመሳተፍ ላይ የሚገኙ ሲሆን ከሥልጠናው በኋላም ስለ ሕግ ተገዥነት ኦዲት ወጥ የሆነ ግንዛቤ መያዝ፣ በስጋት ላይ የተመሰረተ የኦዲት ዕቅድን ማሻሻል፣ በኦዲት መስፈርቶችና ግኝቶች መካከል ጠንካራ ትስስር መፍጠር፣ የሥራ መዝገቦችን (Working Papers) በመጠቀም የሰነድ አያያዝን ማዘመን እና ወጥና ሙያዊ ጥራቱን የጠበቀ የኦዲት ሪፖርት ማቅረብን በተመለከተ ለሠልጣኞቹ የተሻለ ግንዛቤ እንደሚፈጠር ተገልጿል፡፡

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው