Uncategorized

21ኛው የዋና ኦዲተሮች እና የባለድርሻ አካላት የምክክር ጉባኤ በሐረር ከተማ ተካሄደ

የምክክር ጉባኤው ከነሐሴ 23-25/2014 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን በመክፈቻው ላይ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦድሪን በድሪ እና የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብረት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

በጉባኤው የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባኤዎች፣ የየምክር ቤቶቹ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና አባላት፣ ዋና እና ምክትል ዋና ኦዲተሮች፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የፋይናንስ ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

ተሳታፊዎቹ በውይይታቸው ያለፉትን ተሞክሮዎች የዳሰሱበት እና ለቀጣይ የጋራ ሥራዎች አቅጣጫ ያስቀመጡበት ነበር፡፡

በመድረኩ በክብር እንግድነት የተገኙት የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ በክልሉ የህዝብና የመንግስት ሀብት ያለአግባብ እንዳይባክን እንዲሁም ሙስና እና ብልሹ አሰራሮችን ለማስቀረት በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

አያይዘውም የኦዲት ተቋማትን አቅም ለመገንባት እና የሙያ ነጻነት ኖሯቸው እንዲሰሩ ለማስቻል የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርገም ተናግረዋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው የዋና ኦዲተር መ/ቤቶች በተሰጣቸው ስልጣንና ኃላፊነት መሠረት የህዝብና የመንግስት ሀብት በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል መንግስታዊና ሌሎች ተቋማት ብልሹና ህገወጥ አሠራሮች እንዲያስወግዱ የዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ቀዳሚ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።

የኦዲት ሥራ በየጊዜው መሻሻልና ከዓለም አቀፍ ወቅታዊ አሠራር ጋር መራመድ ያለበት ነው ያሉት ዋና ኦዲተሯ፣ የዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ከአዳዲስ አሰራሮችና ዓለም አቀፋዊ የኦዲት ስታንዳርዶች ጋር አሰራራቸውን ማዘመን ይገባቸዋል ብለዋል።

ለኦዲት ስራ ውጤታማነት የባለድርሻ አካለት ቅንጅታዊ አሰራር ልዩ ትኩረት የሚሰጠው በመሆኑም በየደረጃው የሚገኙ የፌዴራልና የክልል ምክርቤቶች፣ የፍትህ ተቋማት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካለት ከዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ አስገንዝበዋል።

ቀደም በነበሩ የምክክር ጉባኤዎች በኦዲት ቴክኒካዊ አሠራሮች፣ በህግና መመሪያ፣ በኦዲት ስታንዳርድ አተገባበር፣ በአቅም ግንባታ፣ በግብዓት ድጋፍ እና በቅንጅታዊ ተልዕኮ አፈጻጸም ዙሪያ በርካታ ውጤቶች እንደተገኙ በጉባኤው ላይ ተነስቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *