የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የ2014/2015 በጀት ዓመት (ከመጋቢት 1 ቀን 2014 እስከ ጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም) ተቋማዊ ዕቅዱንና የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ሩብ አመት አፈጻጸሙን ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቀረበ፡፡
መ/ቤቱ ህዳር 7 ቀን 2015 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት ዕቅዱንና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸሙን ያቀረበው ቋሚ ኮሚቴው ቀደም ሲል በደረሰው የመ/ቤቱ ስትራቴጂካዊና ዓመታዊ ዕቅድ መሠረት የሩብ ዓመት አፈጻጸሙን ገምግሞ ግብረ መልስ እንዲሰጥበት ለማድረግ ነው፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ዕቅዱንና አፈጻጸሙን አስመልክቶ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡ በገለጻቸውም መ/ቤቱ የሩብ ዓመት ዕቅዱን ካስቀመጣቸው ግቦች አንጻር ለማሳካት ያከናወናቸውን ተግባራት፣ በአፈጻጸሙ ያስመዘገባቸውን ውጤቶችና በዕቅድ አፈጻጸም ወቅት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
የቀረበውን ሰፊ ገለጻ መሠረት በማድረግም የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ተጨማሪ ማብራሪያ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ ጥያቄዎችን አንስተው በክብርት ዋና ኦዲተር እና በም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ ተጨማሪ ማብራሪያዎችና ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና ም/ሰብሳቢዋ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው የቀረበው የዕቅድ አፈጻጸም አበረታችና ስኬታማ ሊባል የሚችል መሆኑን በመጥቀስ ተቋሙ የህዝብና የሀገርን ሀብት በአግባቡ በስራ ላይ ከማዋል አንጻር የመ/ቤቱ ሚና ጉልህ ስፍራ ያለውና ለሌሎች ተቋማትም ምሳሌ ሊሆን የሚገባው በመሆኑ በአሠራር ላይ የታዩ ክፍተቶችን በማሻሻል የበለጠ ጠንክሮ መስራትና ተጨማሪ ውጤቶችን ማስመዝገብ ይገባዋል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም መ/ቤቱ የሠራተኞች አቅምና ተቋማዊ አፈጻጸሙን የበለጠ በማጎልበት ቀዳሚ ትኩረቱን በክዋኔ ኦዲት ላይ አድርጎ ዋና ዋና በሚባሉ ሀገራዊ ጉዳዮች፣ የልማት ድርጅቶች እና ሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ በማድረግ የተቋማትን የፋይናንስና የአፈጻጸም ፍትሀዊነት፣ አዋጪነትና ተደራሽነት ላይ መሠረት ያደረገ የኦዲት ስራ እንዲሠራ አቅጣጫ ያስቀመጡት ሰብሳቢዎቹ ቋሚ ኮሚቴውም ሆነ ፓርላማው ለመ/ቤቱ የአፈጻጸም ሂደት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡
#_ቋሚ_ኮሚቴው በፌዋኦ መ/ቤት ላይ ያደረገውን መድረክ በተመለከተ የተላለፈውን ሙሉ ውይይት ከዚህ በታች አባሪ ያደረግናቸውን ማስፈንጠሪያዎች በመጫን መከታተል የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡