የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እና የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አመራርና ሠራተኞች በጋራ በመሆን ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ “ዐሻራችን ለትውልዳችን” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ያለውን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃግብር ምክንያት በማድረግ ዛሬ ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም በአይሲቲ ፓርክ አካሂደዋል፡፡
በችግኝ ተከላዉ ላይ ተሳታፊ የሆኑት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ ባስተላለፉት መልዕክት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጤናማ አየር፣ የከርሰ-ምድር ውሃ እና አፈር ለትውልድ ተጠብቆ እንዲተላለፍ የዜግነት ግዴታችንን የምንወጣበት ነው ብለዋል፡፡
አያይዘውም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የመንግስትን ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ተፈጥሮን የመንከባከብ ኃላፊነትን የመወጣት እና ለተቋሙ ከተሰጠው ተልዕኮ አንጻርም በየዓመቱ የሚተከሉት ችግኞች ጸድቀው ለትውልድ መተላለፋቸውን በአከባቢ ኦዲት የመከታተል ሥራውን አጠናክሮ የሚቀጥልበት እንደሚሆን ም/ዋና ኦዲተሩ አስረድተዋል፡፡
በሀገራችን ከ2.2 ሚሊዮን በላይ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች መኖራቸውን ያወሱት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጽ/ቤት ኃላፊ የተከበሩ አቶ አልማው መንግስት ይህ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛ ከሌላው ማህበረሰብ በበለጠ አከባቢን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ በባለቤትነት ስሜት እንዲንከባከብ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በዛሬው ዕለት በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ከሁለቱ ተቋማት 600 የሚሆኑ አመራርና ሠራተኞች የተሳተፉ ሲሆን በመርሃ ግብሩ 2000 የሚሆኑ ችግኞች ተተክለዋል፡፡
ችግኞቹም 40 በመቶ የጥላ ዛፍ (ወይራ፣ ዝግባ፣ ግራር የሀበሻ፣ ዋርካ እና ብርብራ)፣ 40 በመቶ የውበት (ቱያ ጽድ፣ ተረሚናሊያ እና ኦሜድላ) እና 20 በመቶ የፍራፍሬ (ማንጎ ሀይብሪድ፣ አቮካዶ ሀይብሪድ እና ዘይቶን ሀይብሪድ) መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡