News

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ጥቅምት 9 ቀን 2008 ዓ.ም ለኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ጥቅምት 9 ቀን 2008 ዓ.ም ለኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የእቅድ ትውውቅ አደረገ፡፡
የተከበሩ ወ/ሮ አልማዝ መሰለ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የእለቱ ስብሰባ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌደራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን እቅድ ትውውቅ በማድረግ እና የጋራ ግንዛቤ በመያዝ የክትትልና ድጋፍ ስራውን በአግባቡ ለመፈጸም መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ አዲስ ለተቋቋመው ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን ታሪካዊ ዳራ፤ ዓላማዎች፤ ስልጣንና ትግባር፣ አደረጃጀት፣ አሰራርና አጠቃላይ ተልዕኮን ለግንዛቤ ካቀረቡ በኋላ መ/ቤቱ በ2007/2008 በጀት ዓመት ለማከናወን ያቀደውን እና ያለፉት ሰባት ወራት አፈጻጸምን አቅርበዋል፡፡
በዚህም የፋይናንሺያል ኦዲት ሽፋን 153 የፌዴራል ባለበጀት ተቋማትን ኦዲት በማድረግ የእቅዱን መቶ ፐርሰንት ለመፈጸም እና የክዋኔ ኦዲት 20 ኦዲቶችን ለማከናወን የታቀደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እስካሁን ባለው አፈጻጸም በታቀደው መሰረት ለመፈጸም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ዋና ኦዲተሩ በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የሰው ኃይል ፍልሰት በእቅድ አፈጻጸም ላይ ያለው ትልቁ የመ/ቤቱ ማነቆ መሆኑን ጠቅሰው የምክር ቤቱ ሚና ወሳኝ በመሆኑ ቋሚ ኮሚቴው በትኩረት እንዲከታተለው ጠይቀዋል፡፡
ክብርት የድጋፍ ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ ባዩሽ ተስፋዬ በበኩላቸው የሰው ኃይል ፍልሰቱን ተከታታይ ቅጥር በመፈጸም ለማሟላት ጥረት ቢደረግም የሚፈለገውን ብቃት ያለው የሰው ኃይል ማግኘት አለመቻሉን ጠቅሰው በዋናነት የሰራተኛ መልቀቅ ምክንያት ጥቅማጥቅም አለመሟላት ስለሆነ ቋሚ ኮሚቴው ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት መ/ቤቱ ባለው ውስን የሰው ኃይል የፋይናንሺያል ኦዲት ሽፋንን 100% ለመፈጸም እያከናወነ ያለው ተግባር በጥንካሬ የሚወሰድ መሆኑን ገልጸው በእቅዱ ትኩረት ቢሰጠው ያሏቸውን ነጥቦች ጠቁመዋል፡፡ በዚህም መሰረት የለውጥ ስራ አተገባበር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ፣ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ በእቅድ ተካትቶ መሰራት እንዳለበትና የባለዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡
የተከበሩ ወ/ሮ አልማዝ መሰለ በማጠቃለያቸው የቀረበው እቅድ ስለ መ/ቤቱ በቂ ግንዛቤ ያስጨበጠ መሆኑን ገልጸው በእቅዱ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን በመ/ቤት ደረጃ በመለየት የጋራ መግባባት መፍጠርና ለመፍታት የሚያስችል እቅድ በማዘጋጀት መፈጸም ያስፈልጋል፤ በተመሳሳይም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየትና ለዚህም እቅድ በማዘጋጀት ከባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ በማድረግ ችግሩን ለመፍታት መስራት አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል፡፡እንዲሁም መ/ቤቱ የሚያከናውናቸውን ስራዎች ከሜዲያ ጋር ጥብቅ ግንኙነት በመመስረት በአግባቡ ኮሙኒኬት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡ቋሚ ኮሚቴውም የመስሪያ ቤቱን እቅድ ለማሳካት በሚያደርገው ጥረት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
በመጨረሻም በቋሚ ኮሚቴው በያዝነው ዓመት ለክትትልና ድጋፍ የተዘጋጀው እቅድ ቀርቦ አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡

Office of the Federal Auditor General, Ethiopia's photo.
Office of the Federal Auditor General, Ethiopia's photo.
Office of the Federal Auditor General, Ethiopia's photo.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *