Uncategorized

የዲላ ዩኒቨርስቲ ለኦዲት ግኝቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ከተደጋጋሚ የኦዲት ግኝት ነጻ መሆን እንዳለበት ተገለጸ፡፡

የዲላ ዩኒቨርስቲ አመራር ለኦዲት ግኝቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ዩኒቨርስቲውን ከተደጋጋሚ የኦዲት ግኝት ነጻ ለማድረግ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡ ቋሚ ኮሚቴው በዩኒቨርስቲው የ2008 በጀት አመት ሂሳብ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ያደረገውን ኦዲት መሰረት አድርጎ ሚያዝያ 15/ 2010 ዓ.ም ይፋዊ ስብሰባ አካሂዷል፡፡

በስብሰባው ላይ በኦዲቱ የተገኙ በርካታ ግኝቶች በዝርዝር እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡

በዚህም በጥሬ ገንዘብ ቆጠራ ወቅት ብር 37,900 የተገኘ ቢሆንም ከወጪ ቀሪ ሆኖ የሚታይ የገንዘብ መጠን ባለመኖሩ የተቆጠረው ጥሬ ገንዘብ በመብለጥ የተገኘበት ምክንያት አለመታወቁ እንዲሁም ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች ከተሰበሰበውና ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሪፖርት መደረግ ከነበረበት ብር 18,070,155.47  ውስጥ ብር 2,833,280.20 በማሳነስ ብር 15፣236፣875.27 ብቻ ሪፖርት መደረጉ በኦዲቱ ተመልክቷል፡፡

ለኮንትራት ሰራተኞች ብር 888,454.00፣ በመደበኛ ሰዓት ሊሰሩ ለሚገቡ ስራዎች ብር 413,409.25 እንዲሁም የትርፍ ሰዓት፣ የማበረታቻና የአስተባባሪነት በሚል ምክንያት የሚመለከተው አካል ሳይፈቅድ በድምሩ ብር 5,846,079.25 መከፈሉም ተጠቅሷል፡፡

በህጉ መሰረት ኦሪጅናል ደረሰኝ ለሂሳብ ማወራረጃ ጥቅም ላይ መዋል ሲገባው በብር 5,413,691.14 የተፈፀሙ የተለያዩ ግዥዎችን በዱቤ ሽያጭ ደረሰኝ ማወራረዱ እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው ወጪ ተደርጎ ለጤና ሣይንስ ኮሌጅ በዝውውር የተላለፈ ብር 504,084.00 በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ በወጪ ተመዝግቦ ሳለ በድጋሚ ለጤና ሳይንስ ኮሌጅ በዝውውር ተመዝግቦ መገኘቱ በሪፖርቱ ታይተዋል፡፡

ዘጠኝ የሥራ ተቋራጮች ለዩኒቨርሲቲው ከሚያካሂዷቸው 11 የግንባታ ፕሮጀክቶች መዘግየት ጋር በተያያዘ በጉዳት ካሳነት መሰብሰብ የነበረበት ብር 9,494,646.02 እና በወቅቱ እቃ ካላቀረቡ አቅራቢዎች መሰብሰብ የነበረበት የጉዳት ካሳ ብር 206,919.90 በድምሩ ብር 9,701,565.92 አለመሰብሰቡም ተመልክቷል፡፡

ግዢ በጨረታና በተቀመጠው ጣሪያ መፈጸም ሲገባው በቀጥታ ግዥ ብር 2,857,465.85  እንዲሁም ከተቀመጠው ከጣሪያ በላይ በዋጋ ማወዳደሪያ ብቻ ብር 404,400.00 በድምሩ ብር 3,261,865.85 ወጪ ተደርጎ ግዥ መፈፀሙ እንዲሁም በድምሩ ብር 30,113,316.86 በ2007 ለተፈፀመ ግዥ የበጀት ዓመቱን ሳይጠብቅ በ2008 በጀት ዓመት ሊሠሩ ከታቀዱ ሥራዎች በጀት ላይ መከፈሉ በኦዲቱ ታውቋል፡፡

ለተጨማሪ እቃ ትዕዛዝ ወይም የግንባታ ዘርፍ ስራ የሚከፈለው ክፍያ ቀደም ሲል ውል ከተገባው የገንዘብ መጠን ከ25% በላይ መብለጥ እንደሌለበት በግዥ መመሪያው ቢገለጽም ለዩኒቨርሲቲው ስብሰባ አዳራሽ እድሳት አስቀድሞ ውል ከተገባው 1,098,785.96 ሚሊዮን ብር ላይ ለተጨማሪ የእድሳት ስራ ሊከፈል የሚገባው ብር 274,696.00 ሆኖ ሳለ ብር 4,720,701.03 ከውል በላይ መከፈሉም ታውቋል፡፡

በኦዲት ናሙና ከተመረጡ ሰነዶች ውስጥ ብር 6,873,851.63 የያዙ 16 የክፍያ ቫውቸሮችን ዩኒቨርስቲው ለኦዲት አለማቅረቡም ተገልጿል፡፡

ለግንባታ ዘርፍ ክፍያ የሚፈፀመው የሥራውን ደረጃ ተከትሎ ከአማካሪ መሐንዲስ በሚሰጥ የክፍያ ምስክርነት መሆን ሲገባው ለ21 ግንባታ ስራ ተቋራጮች በዩኒቨርሲቲው የግንባታ ጽ/ቤት በተዘጋጀ 27 የክፍያ የምስክር ወረቀት መሠረት ብር 30,856,433.06 መከፈሉ እንዲሁም GIZ ለተባለ ድርጅት ብር 13,180,000.00 ለትሪትመንት ፕላንት ስራ በሚል ከድርጅቱ በቀረበ የከፍያ ጥያቄ መሠረት ብቻ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የተደረገ ውል ሰነድ እንዲሁም የሚመለከታቸው የሥራ ተቋራጮችና አማካሪዎችን የሚያሳይ ዝርዝር ሁኔታ ሳይቀርብ በተጨማሪም የግንባታ የክፍያ ምስክር ወረቀት ሳይኖር ከመመሪያ ውጪ ክፍያ መፈፀሙ ተገልጿል፡፡ ከዚህም ሌላ ቀድሞ ትምህርት ሚኒስቴር ሲያሰራቸው ከነበሩና ወደ ዩኒቨርሲቲው ከተመለሱት ግንባታዎች ላይ ከኮንትራክተሮች ላይ ከሚፈለግ እዳ ውስጥ 16,501,754.63 የተሰበሰበ ቢሆንም ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በወቅቱ ፈሰስ አለመደረጉ በኦዲቱ ተጠቅሷል፡፡

ዩኒቨርስቲው በውጭ ሀገር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ያደረጋቸው መምህራን በውላቸው መሠረት ዩኒቨርሲቲውን የማገልገል ግዴታቸውን ሳይወጡ በመቅረታቸው ሊሰበሰብ የሚገባው ብር 142,740.00 ገቢ አለመደረጉና አንድ መምህርም ውል ሳይጽም ወደ ውጭ ሀገር ለትምህርት እንዲሄድ መደረጉ ተመልክቷል፡፡

በተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳብ በኩል በቅድሚ ክፍያ ተሰጥተው ሳይሰበሰቡ ከ1 እስከ 14 ዓመት የቆዩ  በድምሩ ብር 8,405,369.03 ተሰብሳቢ ውዝፍ በወቅቱ እንዲወራረድና እንዲሰበሰብ አለመደረጉ እንዲሁም በተለያዩ የሂሳብ መደቦች በድምሩ ብር 654,583.29 የሂሳብ ሪፖርቶች ላይ የሚታይ ቢሆንም ተቀጽላ ሌጀር ያልተሰራላቸው መሆኑና ለኮንትራት መያዣነት የተያዘ ግዴታ የተገባባቸው ሂሳቦች ብር 12,784,647.46 በወቅቱ አለመወራዱ ተገልጿል፡፡

በበጀት አጠቃቀም በኩል ከውስጥ ገቢ ከተፈቀደው ብር 15,934,900.00 ውስጥ ብር 1,391,767.43 (9%) ሥራ ላይ ያልዋለ መሆኑ፤ ለካፒታል ከተፈቀደው ብር 494,567,240.65 ውስጥ ብር 18,850,286.32 (4%) ሥራ ላይ ያልዋለ መሆኑ፤ እንዲሁም ከመደበኛ በጀት ብር 368,717,022.26 ውስጥ ብር 12,013,561.17 (3%) ከበጀት በላይ ጥቅም ላይ መዋሉ ተመልክቷል፡፡

በንብረት አስተዳደርና አወጋገድ በኩል በብር 1,720,500.00 የተለያዩ እቃዎች የተገዙ ቢሆንም ዕቃዎቹ በናሙናው መሠረት ለመገዛታቸው በጥራት (በቴክኒክ) ኮሚቴ ሳይረጋገጡ ገቢ መደረጋቸው እንዲሁም ለተማሪዎች የምግብ አገልግሎት የሚውል ጤፍና ማርማላት ግዥ በብር 3,184,000.00 ቢፈፀምም ዕቃዎቹ ወደ ንብረት ክፍል ለመግባታቸው የሚያረጋግጥ የንብረት ገቢ ደረሰኝ አለመቅረቡ ተጠቅሷል፡፡

እንደዚሁም በዋናው ግቢ የተለያዩ ህንፃዎች እንደ ቋሚ ንብረት በተለየ መዝገብ ላይ መመዝገብ ቢገባቸውም በ2008 በጀት ዓመት እና ከዚያ በፊት ባሉት ሁለት ዓመታት ርክክብ የተፈፀመባቸው አገልግሎት የሚሠጡ ህንፃዎች እንዲሁም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ያልተመዘገቡ መሆኑ፤ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ ያገለገሉ የአገልግሎት ዘመናቸው ያበቃ ለኬሚስትሪና ለባዮሎጂ ትምህርቶች ላብራቶሪ አገልግሎት የሚውሉ ኬሚካሎችና መድኃኒቶች ለረጅም ጊዜ ሳይወገዱ መቆየታቸው፤ ቁጥራቸው የማይታወቅ በርካታ ወንበሮች ከአገልግሎት ውጪ ሊሆኑ በሚችሉበት መልኩ ለረጅም ጊዜ ለዝናብና ለበፀሐይ መጋለጣቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ካሉት ተሽከርካሪዎች ውስጥ 25 ተሽከርካሪዎች በቀላልና ከባድ ብልሽት አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆኑ ወደ ሥራ እንዲገቡ ወይም አገልግሎት የማይሰጡትን እንዲወገዱ አለመደረጉ በኦዲቱ ተገኝቷል፡፡

ዩኒቨርስቲው የዕለት ተዕለት ተግባራቱን በማከናወን ሂደት የሚከሰቱ ችግሮችንና የተጋላጭነት ደረጃን ለመለየት በሚያስችል መልኩ የሥጋት ተጋላጭነት ዳሰሳ ጥናት አለማድረጉም ተጠቅሷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በነዚህ ግኝቶች ላይ የዩኒቨርስቲው አመራር ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡ በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር የ2006 እና የ2007 በጀት አመት የሂሳብ ኦዲት ግኝቶችንና የዋና ኦዲተር መ/ቤትን የማሻሻያ ሃሳቦችን መሰረት አድርጎ የእርምት እርምጃ ባለመውሰዱ በተደጋጋሚ የኦዲት ግኝት እንደሚገኝበትና በ2008 በጀት ዓመት ለተገኙ ግኝቶችም በአብዛኛው ምላሽ እንዳልሰጠ ተገልጾ የተቋሙ አመራር በባለቤትነትና በተጠያቂነት ኃላፊነትን የማይወጣበት፣ ችግሩን የማይፈታበትና ለመንግስት ደንብና መመሪያ ተገዥ ያልሆነበት መሠረታዊ ምክንያት ምን እንደሆነ እንዲገለጽለት ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡

በተነሱት ጥያቄዎች ላይ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ቃልኪዳን ነጋሽና ሌሎች የስራ ሀላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በመብለጥ ሪፖርት የተደረገው ብር 37,900 በሰኔ 30 2008 ዓ.ም ለሪፈራል ሆስፒታል ሰራተኞች ሊከፈል የተዘጋጀና በውስጥ ኦዲተሮች የጥሬ ገንዘብ ቆጠራ ወቅት የተገኘ እንደሆነና በእለቱ ለሰራተኞቹ በመክፈልና አስፈላጊ ማስረጃዎችን በማቅረብ ከውስጥ ኦዲት ጋር መተማመን ላይ የተደረሰበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በማነስ ሪፖርት ስለተደረገው ገንዘብ ሲገልጹም በወቅቱ በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና በሪፈራል ሆስፒታል ከመድሀኔትና የህክምና መሳሪያዎች ሽያጭ ከእቅድ በላይ የተሰበሰበ ገንዘብ እንደነበረና በበጀት ዓመቱ ከነበረው ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ጋር በተያያዘ የተጠቀሰው መጠን ፈሰስ ሳይደረግ በተቋሙ ላሉ ችግሮች ወጪ መደረጉና ይህ አሰራሩን የጠበቀ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

አላግባብ የተከፈሉ ክፍያዎችና ጥቅማ ጥቅሞችን በተመለከተ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የትርፍ ሰዓት ክፍያ እንደተቋረጠ፣ ከሥራ ባህሪ አንፃር የትርፍ ሰዓት ክፍያ የሚያስፈልጋቸው የሥራ ክፍሎች ተለይተው በ2009 እና በ2010 የበጀት ዓመት ከፐብሊክ ሰርቪስና ከሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር በተገኘ ፈቃድ የተወሰኑ መደቦች ላይ እየተከፈለ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በፕሮጀክት ገንዘብ ይካሄድ የነበረ ስራ ከተቋረጠ በኋላም ይከፈሉ የነበሩ ክፍያዎች ከ2009 በጀት ዓመት ጀምሮ እንዲቋረጡ መደረጉን ገልፃዋል፡፡ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች መጥተው በማማከርና በማስተባበር ስራ ለሚሰማሩ መምህራን በተለይ ከድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ጋር በተያያዘ የሚከፈሉ ክፍያዎችን ማቆም በትምህርት ስራው ላይ በቀጥታ ተፅዕኖ ስለሚኖረው ከዚህ በፊት በአስተዳደር ካውንስሉ ፀድቀው የነበሩ ክፍያዎችን ወዲያው ማቆም ባይቻልም ተጠንቶ ዝርዝር ፕሮፖዛል ተዘጋጅቶ ለቦርድ ቀርቦ እንደሚጸድቅ ተናግረዋል፡፡

ደጋፊ ማስረጃ ያልቀረበለትና በዱቤ ሽያጭ የተወራረደ ሂሳብን በተመለከተ እነዚህ ደጋፊ ማስረጃዎች በአሁኑ ወቅት እንደቀረቡ ገልፀዋል፡፡ በወቅቱ ያልቀረበውም የፋይናንስ የስራ ክፍል ውስጥ ባለው የሠነድ አያያዝ ችግር መሆኑንና አሁን የሠነድ አያያዙ ችግር ከሞላ ጎደል መፈታቱን ገልፀዋል፡፡

አላግባብ ስለተመዘገበው ሂሳብ ሲስረዱም ሂሳቡ ፋይናንሻል ስቴትመንት ላይ ያለ የተዘጋ ሂሳብ በመሆኑ በቀላሉ በዩኒቨርሲቲው የሚፈታ ባለመሆኑ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ድጋፍ እንዲደረግ ጥያቄ መቅረቡንና ባለሙያ እስኪላክላቸው እየተጠበቀ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በግንባታ ፕሮጀክት ያልተሰበሰበ የጉዳት ካሳን በተመለከተ አብዛኞቹ የግንባታ ፕሮጀክቶች ባለመጠናቀቃቸው ወደ ጉዳት ካሳ ጥያቃ ደረጃ አለመደረሱን በሌላ በኩልም ፕሮጀክቶቹ የሚዘገዩት በኮንትራክተሮቹ ችግር ብቻ ሳይሆን በዩኒቨርስቲውና በአማካሪ ድርጅቱ ባሉ ችግሮች ምክንያትም ጭምር በመሆኑ ኮንትራክተሩን ብቻ ለመጠየቅ  አመቺ ሆኖ እንዳልተገኘ ተናግረዋል፡፡

በቀጥታና በዋጋ ማወዳደሪያ የተፈፀመ ግዥን በተመለከተ ለተፈጠሩ አጣዳፊ ችግሮች ወዲያው ምላሽ ለመስጠት በሚል ምክንያት የተፈፀሙ ግዢዎች እንዳሉ እንደዚሁም እንደ ውሃ ፓምፕ ግዢ አይነት በተቋሙ ላይ ሊደርስ የሚችል የማይቀለበስ ጉዳትን ለመከላከል በሚል የግዥ ህጉን መሠረት በማድረግ በአስገዳጅ ሁኔታ የተፈጸሙ ግዥዎች እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡ በግዥ በኩል የነበሩ ችግሮች ከአሰራር ጋር የተያያዙም እንደነበሩ በመገምገም የግዥ ዳይሬክተሩን የመቀየር እርምጃ መወሰዱን ከ2009 አጋማሽ ወዲህ ያለው የግዥ ሥርዓት የተሻለ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ከውል በላይ በተፈጸመና በጀት ዓመቱን ባልጠበቀ ክፍያ ረገድ በ2007 ለምርምርና ለማስተማር ለሚያስፈልጉ በርካታ ግዥዎች ከአስቸኳይነታቸው አንፃር አንዳንድ ያልታቀዱ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡ በዚህም በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች የመፀዳጃና መታጠቢያ ቤቶች እጥረት ስለነበር በወቅቱ አዲሱ የዩኒቨርስቲው አመራር ችግሩን ለመቅረፍ ከእቅድ ውጪ እንዲከናወኑ ያደረጋቸው አነስተኛ ግንባታዎች እንደነበሩና ሌሎች አንገብጋቢ ችግሮችን ለመፍታት እንደ ጄኔሬተር ያሉ ግዥዎች እንደተፈፀሙና በነዚህ ግዥዎች ምክንያት የውሎቹ ክፍያ ከበጀት ዓመት የተሻገሩበት ሁኔታ እንደተፈጠረ አስረድተዋል፡፡

ለስብሰባ አዳራሽ ጥገና ከተከፈለው ተጨማሪ ክፍያ ጋር ተያይዞም አዳራሹ ያረጀና ደረጃውን ያልጠበቀ በመሆኑ ጥገና እየተደረገለት እያለ ዩኒቨርሲቲው የ29ኛውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉባኤ እንዲያስተናግድ  በመመረጡ ለዚህ የሚሆን ደረጃውን የጠበቀ አዳራሽ በዩኒቨርሲቲውም ሆነ በከተማው ባለመኖሩ በመጀመሪያ ህንፃውን ለማደስ በተደረገው ግዥ ላይ ሰፊ የለውጥ ስራ ተሰርቶ በመታደሱ በመመሪያው ከተፈቀደው ጣሪያ በላይ ክፍያው መውጣቱን ገልፀዋል፡፡ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ለመጀመሪያው የህንፃ እድሳት ግዥ ፈቃድ በመስጠቱ ተጨማሪ ስራውን ሳያስፈቅዱ ጥገናውን ማካሄዱ ስህተት እንደነበረና ይህን በፈጸመው የቀድሞው አመራር ላይ ግን እርምጃ እንዳልተወሰደ አስረድተዋል፡፡

ለኦዲት ስራ የተጠየቁ ማስረጃዎች ካለመቅረባቸው ጋር አያይዘው ሲናገሩም ከፋይናንስ ክፍሉ ሰነድ አያያዝ ችግር በመነጨ የተከሰተ እንደሆነና ከኦዲቱ በኋላ ግን በዘመቻ መረጃዎች እንደተፈለጉና መረጃዎቹ አሁን እንዳሉ ገልፀዋል፡፡

የ21 ግንባታዎች ክፍያ ዩኒቨርሲቲው ካለአማካሪ ከኮንትራክተሩ ጋር የሁለትዮሽ ውል በመግባት የፈፀማቸውን መሆኑን ገልፀው ይህም የዩኒቨርሲቲዎች የግንባታ ፕሮጀክት አስተዳደር ጽ/ቤቶች ከትምህርት ሚኒስቴር በወረደ መመሪያ ዩኒቨርስቲዎች በራስ አቅም መሰራ በሚችሉ መለስተኛ ፕሮጀክቶች ላይ የግድ አማካሪ መቅጠር ሳያስፈልጋቸው የማማከርና የሱፐርቪዥን ስራውን በራሳቸው መስራት እንደሚችሉ በተሠጣቸው ተግባርና ኃላፊነት መሰረት የዩኒቨርስቲው የግንባታ ጽ/ቤት የአማካሪ ድርጅትን ስራ ተክቶ እንደሰራ አስረድተዋል፡፡ አክለውም በወቅቱ ይህ በኦዲተሮች እንደግኝት መቅረቡን ምክንያት በማድረግ ለመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ጥያቄ ቀርቦ እንደነበረና ኤጀንሲው በሠጠው ምላሽ ዩኒቨርስቲው በመመሪያው መሠረት በአግባቡ መፈጸሙን ማረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

ከGIZ ክፍያ ጋር በተያያዘ ክፍያውን ለመፈፀም የሚያስችል በቂ ዝርዝር መረጃ የነበረ በመሆኑ የተፈፀመ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ተሰብሳቢ ሂሳብን በተመለከተ ለበርካታ አመታት የዩኒቨርሲቲው ችግር ሆኖ የቆየበት ሁኔታ እንዳለና የበርካታ አመታት ተሰብሳቢ ሂሳብ ተንከባሎ እንደመጣ ገልፀው ተሰብሳቢውን ሂሳብ በየመደቡ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ አንደኛው ተሰብሳቢ ከ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነው ለመምህራን ይሠጥ የነበረ ብድር መሆኑን ገልጸው አሰራሩ በ2009 አዲሱ አመራር ሥራውን ከጀመረ ወዲህ እንዲቆም መደረጉንና እየተሰበሰበ እንዳለም አስረድተዋል፡፡ ከሌሎች ተሰብሳቢ ሂሳቦች ጋር በተገናኙ ጉዳዮች ላይ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጋር ውይይት እየተደረገ እንዳለና በቀጣዩ አመት ከነዚህ ውስጥ በተወሰኑት ላይ እርምጃ መወሰድ እንደሚጀምር አስረድተዋል፡፡ በኃላፊዎች መቀያየር ምክንያት መፍትሄ ማግኘት ያልቻሉ ተሰብሳቢዎች እንደነበሩና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጤና ኮሌጅ ከዲላ ዩኒቨርስቲ ተገንጥሎ ሲሄድ ለሥራ ማስኬጃ የተወሰደውን ገንዘብ ዩኒቨርሲቲው በተሰብሳቢ ቢመዘግበውም ኮሌጁ ግን በተሰብሳቢነት እንዳልመዘገበውና ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት መቅረብ ያለበት ማስረጃ እየተፈለገ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ተቀጽላ ሌጀር ያልተከፈተላቸው ሂሳቦችም በሙሉ እንደተከፈተላቸውና በአግባቡ እድሜ ተስጥቷቸው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በተከፋይ ሂሳብ በኩል የግንባታ ፕሮጀክቶቹ ወደ ፊት ሲጠናቀቁ ተከፋይ ሂሳቦችም እእንደሚከፈሉ ገልጸዋል፡፡

ከበጀት በላይ አጠቃቀምን በተመለከተ ባብዛኛው ከተማሪዎች ምግብ አቅርቦት ጋር በተገናኘ የተፈጠረ እንደሆነና በዋጋ ንረት፣ ከጨረታ በኋላ በሚከሰቱ የዋጋ ጭማሪዎች እና ሌሎች ምክንያቶች ሳቢያ የሚፈጠር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የተገዙ እቃዎች በናሙና መሠረት ገቢ አለመደረጋቸውን በተመለከተ በፊት በነበረው አሰራር በቴክኒክ ኮሚቴዎች ሳይሆን እውቀቱ ባላቸው ሠዎች የሚረጋግጥበት ሁኔታ እንደነበረ በማስታወስ ሁኔታውን ሙሉ በሙሉ በመቀየር በየዘርፉ በአግባቡ ኮሚቴዎች ተዋቅረው በስፔስፊኬሽኑና በናሙና መሠረት እቃዎች መቅረባቸው እየተረጋገጠ ገቢ እየተደረገ እንዳለ ገልጸዋል፡፡

የህንፃ ምዝገባን በተመለከተ ችግሩ እንዳለ ገልጸው ነባርም ሆነ አዲሶቹ ህንፃዎች እንዳልተመዘገቡና ለመመዝገብ ሥራ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡

ንብረት ሳያስረክቡ የሚሄዱ ሠራተኞች ጉዳይ በውስጥ ድክመት የተፈጠረ እንደሆነና ንብረት በዚህ መልኩ የለቀቁትን ተከታትሎ የማስመለስ እና በህግ የማስጠየቅ በኩል ድክመቶች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ ንብረት የመለሱና ያልመለሱ ሰዎችንም የመለየት ስራ እየተሰራ እንዳለና እንዲመልሱ የተደረጉም እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

የሚወገዱ ኬሚካሎችን በተመለከተ ለማስወገድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ግንኙነት መደረጉንና ኬሚካሎቹን ለማስወገድ በሀገር ደረጃ ከባድ እንደሆነ በሚመለከተው አካል እንደተገለጸ አስረድተው ዩኒቨርሲቲው ግን በግሉ ከውጪ ካምፓኒ ጋር በመነጋር ኬሚካሎቹን ለማስወገድ ጥረት እንዳደረገና ጉዳዩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚፈታበት ሁኔታ እየተጠና በመሆኑ ሂደቱ መቋረጡን ተናግረዋል፡፡ በችግሩ ምክንያት የጤና ጉዳትም እየደረሰ መሆኑንና ሰው ሊደርስበትና ብዙ ንኪኪ ሊኖር በማይችል መጋዘን ውስጥ ኬሚካሎቹ ታሽገው በጥንቃቄ እንዲቀመጡ መደረጉን ገልፀዋል፡፡

ለብልሽት የተጋለጡ ወንበሮችን ጉዳይ በተመለከተ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ወንበር ለማስጠገን ጥረት መደረጉን፤  ሊጠገኑ የማይችሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ንብረቶችን የማስወገድ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡ በተበላሹ ተሽከርካሪዎች በኩል የተቋሙ ተሽከርካሪዎች ያረጁና ዩኒቨርሲቲው ባለበት አካባቢ ባለው የተበላሸ መንገድ ሳቢያ ተደጋጋሚ ብልሽት እንደሚደርስባቸው ጠቅሰው አሁን ተበላሽተው የቆሙ መኪኖች ቁጥር መቀነሱንና በጣም ከባድ ችግር ያለባቸውን መኪኖችን ለመለየት ጥናት እየተደረገ እንዳለና ለማስወገድ መታቀዱን ገልፀዋል፡፡

በዩኒቨርስቲው የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ላይ የቋሚ ኮሚቴው አባላትና በመድረኩ የተገኙ ባለድርሻ አካላት ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አቅርበዋል፡፡

በቋሚ ኮሚቴው አባላት በኩል የተጠያቂነትን ስርአት ከማስፈን አንጻር የውስጥ ቁጥጥር ስርአትን ከማጠናከር እንዲሁም የውስጥ ኦዲት የስራ ክፍልን በመደገፍና የሚያወጣቸውን የኦዲት ሪፖርቶች ተከትሎ እርምጃ በመውሰድ አኳያ ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል፣ ለGIZ ለተከፈለው ክፍያ መረጃ አለ ከተባለ በኦዲቱ ወቅት ለምን እንዳልቀረበ፣ ለዩኒቨርስቲው እድሳት ተጨማሪ ስራ ከመመሪያ ውጪ 4.4 ሚልየን ብር አላግባብ በከፈለው አካል ላይ እርምጃ ስለመወሰዱ፣ ዩኒቨርስቲውን ከተሰብሳቢ ሂሳብ ነጻ ለማድረግ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶ ለምን እንዳልተሰራ እንደዚሁም በቴክኖሎጂ በመታገዝ የተከማቹና የተበታተኑ ሰነዶችን አደራጅቶ ለመያዝ የታቀደ ጉዳይ ስለመኖሩ ጠይቀዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ዩኒቨርስቲው የዋና ኦዲተር መ/ቤት ግኝትን እንደግብአት እንደማያይና ደንብና መመሪያን ሳያከብር እንደሚሰራ፣ ከመንግስት ደንብና መመሪያ ውጪ የተከፈሉ ክፍዎች ሊመለሱና የተፈጸሙ ግዢዎችም ተጠያቂነት ሊኖርባቸው እንደሚገባ እንዲሁም አስቸኳይና አስገዳጅ በሚል ደንብና መመሪያዎችን መጣስ ተቀባይነት እንደሌለው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ባለድርሻ አካላት በሰጡት አስተያየት በፌዴራል ስነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን በኩል ዩኒቨርስቲው በኦዲቱና ከኦዲቱ ውጪ ያሉ ችግሮችንና ሊወሰዱ ከሚገቡ መፍትሄዎችን ጭምር በሚገባ በሚገልጽ አግባብ በዝርዝር የተዘጋጀ በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል የተቀናጀ የሙስና መከላከያ ስትራቴጂ በ2009 ቢያዘጋጅም ስራ ላይ እንዳላዋለውና ወደ ተግባር መለወጥ እንደሚጠበቅበት ተጠቅሷል፡፡

በፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ በኩል ችግሮችን ሰበብ አድርጎ ከመንግስት ህግ ውጪ መስራቱ አግባብነት እንደሌለው አስገንዝበው የውሀ ፓምፕ ለምን በመመሪያው መሰረት እንዳልተገዘና ለምንስ ችግሩን ታሳቢ አድርጎ ቀድሞ ዝግጅት እንዳልተደረገ፣ የዩኒቨርስቲው ህንጻዎችን ርክክብ ሲደረግ በውል መሰረት የተሟሉ መሆናቸው ተረጋጦ ለምን ርክክብ እንዳልተፈጸመ፣ ይህ ባለመደረጉ ለመጸዳጃ ቤትና ለመታጠቢያ ቤት ግንባታ ለወጣው ወጪ ተጠያቂው ማን እንደሆነ እንዲሁም በተፈጸሙት በርካታ ግድፈቶች ውስጥ እስካሁን ተጠያቂ የተደረገ አካል ስለመኖሩ ጠይቀዋል፡፡

በመንግስት ግዥና ንበረት ማስወገድ አገልግሎት በኩል ኬሚካል ማስወገድ ሀገራዊ ችግር እንደሆነና አወጋገዱ ጥናት እየተደረገበት እንደሆነ ነገር ግን እንደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በዩኒቨርስቲዎችም በኩል ባሏቸው ምሁራን አማካይነት በኬሚካል ማስወገድ ላይ ጥናት ቢያደርጉ መልካም እንደሆነ፣ ጠጋኝ ያልተገኘላቸውንና ቢጠገኑም አዋጭ ያልሆኑትን ወንበሮች ማስወገድ እንደሚያስፈልግ እንዲሁም ግንባታን ካለአማካሪ ድርጅት ማከናወን ከግዢ ህጉ አንጻር በደንብ መታየት እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡

በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በኩል የዩኒቨርስቲው አመራር የፋይናንስ ስርአቱን ተከትሎ ህጋዊ ስርአት መዘርጋት እንደሚጠበቅበት፣ ከ2006 በጀት አመት ጀምሮ ሲንከባለሉ የመጡ ግኝቶችን ወስዶ በአሰራር መፍታት ላይ ክፍተት እንደሚታይ፣ የውስጥ ኦዲት ክፍሉን በማገዝና በማጠናከር ላይ ጉልህ እጥረት እንዳለ፣ በ2007 እና 2008 በጀት አመቶች በውስጥ ኦዲት በተገኙ ጉልህ ግኝቶች ላይ የተሰራ ስራ እንደሌለና በመስክ ጉብኝት ወቅትም በአብዛኛው በዋና ኦዲተር ግኝቶች ላይ እርምጃ እንዳልተወሰደ መረጋገጡን፣ በዩኒቨርስቲው ውስጥ በሌሉ ሰዎች ስም ሀሰተኛ (artificial) የሆኑ ተሰብሳቢ ሂሳቦች እየተፈጠሩ እንደሆነና እነዚህን ሂሳቦች እንዲያስወግዱ ሀሳብ የተሰጠ ቢሆንም ምን እርምጃ እንደተወሰደባቸው አለመገለጹን ገልጸው ላልተሰበሰበው የግንባታ ፕሮጀክቶች የጉዳት ካሳ የተሰጠው ምክንያት አጥጋቢ ባለመሆኑ ሊሰበሰብ ይገባል ብለዋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ዩኒቨርስቲው የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ ያከናወናቸውን የእርምት ተግባራት መላክ እንዳለበት፣ ሰነዶችን በአግባቡ አደራጅቶ ለኦዲት ማቅረብ እንደሚተበቅበት አሳስበዋል፡፡ በተጨማሪም ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚያጋጥማቸው ሁሉ ዲላ ዩኒቨርሲቲም የፋይናንስና የውስጥ ኦዲት ባለሙያዎች እጥረት እንዳለበት ገልጸው በቅርብ ጊዜ ትምህርት ሚኒስቴር ከገንዘብና ኦኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በመመካከር ዩኒቨርሲቲዎች በፋይናንስ ስራ ላይ የሰው ሃይል እጥረት ካለባቸው በልዩ ሁኔታ ከፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር እንዲፈቀድ ተደርጎ ቅጥር እየተፈፀመ እንዳለ ገልጸው መሆኑ በዲላ ዩኒቨርሲቲም ይኸው ሂደት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

ከፕሮጀክት ጋር ተያይዞም የዩኒቨርሲቲው የግንባታ ጽ/ቤት በግንባታ ሥራዎች ማማከር ላይ ያለው ስልጣን ገደብ ያለው እንደሆነ ገልጸው በዚህ ዙርያ ያለው የግንዛቤ ችግር መፈታት አለበት ብለዋል፡፡ ከGTZ ጋር በተያያዘም  ከጨረታ ጀምሮ እስከ ክፍያ ያሉ ሠነዶች ለዩኒቨርሲቲዎች እንደተሰጡና ቀሪ ሰነዶች ብቻ ትምህርት ሚኒስቴርን ወክሎ GTZ ጋር እንዳሉ ገልጸው ያለው ችግር ሠነድን በትክክል መረከቡ ላይ ስለሆነ ዲላ ዩኒቨርስቲም ራሱን ማየት ይገባዋል ብለዋል፡፡ ያልተገኙ ሠነዶችን ካሉም GTZ ጋር ሊኖሩ ስለሚችሉ ችግሩን ለመፍታት ትምህርት ሚኒስቴር እገዛ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡፡

ፍቃድን የሚፈልጉ ግዥዎችን ከመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ማስፈቀዱ ከባድ ባለመሆኑ ይህን ማድረግ እንደሚገባና የህዝብና የመንግሥት ሀብትን በህግና መመሪያ ብቻ ማዋልን ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያሻ አስረድተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ቃልኪዳን በቋሚ ኮሚቴውና በባለድርሻ አካላት በተሰጡት ተጨማሪ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በመርህ ደረጃ የቀጥታ ግዥ መደረግ ባይኖርበትም በግዢ ህጉ በተቀመጠው መሠረት ዩኒቨርስቲው ግዥው ባስቸኳይ ካልተፈጸመ የማይቀለበስ ችግር ሊያጋጥም ይችላል ብሎ ካመነ በማኔጅመንት አስፈቅዶ ቀጥታ ግዥ መፈጸም የሚቻል በመሆኑ ከተማሪዎች መኝታ ክፍል መቃጠል፣ ከቦንብ ፍንዳታና ከውሃ አቅርቦት ችግር ጋር በተያያዘ እንደተከናወነና ከችግሩ አጣዳፊነት አንጻር ከመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ጠይቆ ማስፈቀድም ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ አሳውቀዋል፡፡

ማስረጃ ያልቀረበላቸው ክፍያዎች ቀደም ብሎ በተጠቀሰው መልኩ ከአሠራር መዝረክረክና ከባለሙያዎች አቅም ጋር የተገናኘ እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ አስረድተዋል፡፡

የውስጥ ኦዲትን አጠናክሮ በማደራጀት በኩል በባለሙያውም ሆነ በአመራር በኩል ክፍሉ መሳሳቱንና ይህም የቀድሞ የውስጥ ኦዲት ዳይሬክተር ከቦታው ለቀው ሌላ ሀላፊነት ላይ በመቀመጣቸው እንደሆነ፣ ለክፍሉ የሰው ሀይል በቅጥር ለማሟላት የተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ተደርጎ የተቀጠሩት ሁለት ባለሙያዎችም ከተቋሙ ጋር መላመድና የበለጠ አቅማቸው ማደግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ የክፍሉ ተወካይ ኃላፊም ጉልህ የአቅም ችግር ያለባቸው በመሆኑ የክፍሉን አመራር በመቀየርና በአዲስ መልክ በማደራጀት ለመስራት ታቅዷል ብለዋል፡፡

ለአዳራሽ ጥገና ተጨማሪ ሆኖ የተከፈለው ገንዘብም የተሰራው ስራ ተቀጥሮና ተረጋግጦ ለተሰራ ስራ በአግባቡ የተከፈለ እንጂ የባከነ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ብለው ከተፈቀደው የክፍያ ጣሪያ በላይ መከፈሉ ግን ጥፋት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህንንም በወቅቱ የነበረው አመራር በቅን ልቦና ያደረገው እንደሆነና ተጠያቂ ይሁን ከተባለም በምን አግባብ እንደሆነ እንዲገለጽ ጠይቀዋል፡፡

የኦዲት ግኝቶችን ለእርምት እርምጃ በመጠቀም በኩል አዲሱ አመራር ከ2009 በጀት ዓመት አጋማሽ በኋላና በ2010 በጀት አመት የኦዲት ግኝቶችን መሠረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ዶ/ር ቃልኪዳን ገልፀዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት አስተያየት ለመንግሥት ፈሰስ መደረግ ያለበትን ገቢ መሰወር ተገቢ እንዳልሆነ፣ የትርፍ ሰዓትና የማስተባበሪያ ክፍያ እዲቆም ተደርጓል ቢባልም በ2009 በጀት አመትም እንደነበረና ጥያቄው ክፍያው ይቁም ብቻ ሳይሆን አላግባብ የተከፈለው ይመለስ የሚልም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ግንባታዎችን ከማስጀመሩ በፊት አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች ማድረግ እንደሚያስፈልግና ያልተዘጋጀ የግንባታ ሳይት ይዞ ውል መግባት እንደሌለበት እንዲሁም በዚህ አግባብ የሰሩትን መቅጣት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ክቡር ዋና ኦዲተሩ የቀጥታ ግዥ መፈፀም ያለበት መመሪያን ተከትሎ በአስፈላጊው ሰነድ ተደግፎ መሆን እንደሚኖርበት ጠቅሰው ለቀጥታ ግዥ ጥቅም ላይ ከዋለው 2.8 ሚሊዮን ብር ውስጥ ለውሃ ፓምፐ ግዢ ከወጣው 455 ሺህ ብር ውጪ ሌሎቹ አስቸኳይ ተብለው ሊፈጸሙ የማይገቡ ግዥዎች እንደነበሩ ማስረጃዎቹን በዝርዝር አቅርበው አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ውጪ ክፍያዎችን በበጀት አመቱ ለታቀዱ ሥራዎች መክፈልና ክፍያዎችን ተከታትሎ በበጀት ዓመቱ መክፈል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው ለአዳራሽ ጥገና የተጠየቀው ገንዘብ መጠን ተገቢ ስለመሆኑ የገበያ ጥናት አድርጎ ሳያረጋገጥ ተቋራጩ በጠየቀው ዋጋ መሰረትነት ብቻ ስራውን ለተቋራጩ እንደሰጠ ገልጸው ይህን ያደረገው አካል መጠየቅ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

ለትምህርት ወደ ውጪ ሀገር ለሚሄዱ መምህራን የሚሠጥ ብድር ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ቢቆምም ዩኒቨርሲቲው ብድሩን በ2009 በጀት አመት ጭምር የሠጠበት ሁኔታ እንዳለና ይህም ህገ ወጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሀሰተኛ ተሰብሳቢ ሂሳብ ከተፈጠረም ይህንን ባደረጉት ላይ እርምጃ መወሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ክቡር አቶ ገመቹ የዩኒቨርስቲ ግንባታ ጽ/ቤቶች የተቋቋሙት የክፍያ ሰርተፍኬሽን ለማረጋገጥ ሳይሆን የፕሮጀክት አስተዳደር ክትትል ስራ እንዲሰሩ እንደሆነ፣ የዩኒቨርሲቲው የግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤትም ትምህርት ሚኒስቴር ባዘጋጀው መመሪያ መሠረት እንዳልተደራጀ፣ ከተረጋገጡ 27 የክፍያ ሠነዶች ውስጥ አስሩ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንደሆኑና ጽ/ቤቱ ይህን ለማረጋገጥ ስልጣን እንደሌለው ገልጸዋል፡፡ ይህን ስራ በሚገባ ያልተከታተሉ ኃላፊዎችም መጠየቅ አለባቸው ብለዋል፡፡

ከGIZ ጋር ለትሪትመንት ፕላንት ግንባታ ውል የተዋዋለው ከትምህርት ሚኒስቴር እንደሆነና ዩኒቨርሲቲው ስራው ስለመሰራቱ የሚያረጋግጡ ሠነዶች ሳይሟሉና መሠራት ያለባቸው ዝርዝር ጉዳዮች ሳይሰሩ ክፍያ መፈጸሙ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

በኬሚካል አወጋገድ ላይም የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆኖ ዩኒቨርሲቲዎችን ባሳተፈ መልኩ በቀጣይ በሀገር አቀር ደረጃ ችግሩ እንዴት ይፈታ የሚለውን ቢያጠና እንደሚሻል ዋና ኦዲተሩ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት ገለሶ በማጠቃለያ አስተያየታቸው የዩኒቨርስቲው አዲስ አመራር አሰራሮችን ለመዘርጋትና ችግሮችን ለመፍታት እያደረገ ያለው ሙከራ እንዲሁም፣ የተቀናጀ የሙስና መከላከያ ስትራቴጂ ማዘጋጀቱን በጥንካሬ ጠቅሰዋል፡፡

ሆኖም በተቋሙ ተወሰዱ የተባሉ እርምጃዎች ለዋና ኦዲተር መ/ቤትና ለሚመለከታቸው አካላት በየወቅቱ መገለጽ እንዳለባቸው፣ የተቀናጀ የሙስና መከላከያ ስትራቴጂውን ወደ ተግባር መቀየር እንደሚያስፈልግ፣ በኦዲት የተገኙ ግኝቶች ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ፣ ከደንብና ከመመሪያ ውጪ የተከፈሉ ክፍያዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲቆሙና እንዲመለሱ ማድረግ እንደሚያስፈልግና ተጠያቂነትን በማስፈን አስፈላጊነት ላይ አዲሱ አመራር ግንዛቤ መውሰድ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት  በግንባታ ፕሮጀክት አካባቢ ያለውን አሰራር ማጥራትና ለኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚከፍቱ ጉዳዮችን ማስቀረት ላይ የዩኒቨርሲቲው አዲሱ አመራር ትኩረት ማድረግና በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት፣ እገዛ በሚፈልግባቸው ጉዳዮች ላይም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት መስራት እንደሚኖርበት፣ ትምህርት ሚኒስቴርም ተገቢውን ድጋፍ ለዩኒቨርሲቲው መስጠት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡

የውስጥ ኦዲት ክፍሉን ማጠናከርና የበላይ አመራሩ ከኦዲት ግኝቶችም ነጻ ሆኖ ስራውን እንዲመራ የሚያስችል አቅም እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አክለዋል፡፡

እንደዚሁም ከበጀት አጠቃቀምና ከግዥ ጋር ተያይዘው በመድረኩ የተሰጡ አስተያየቶችን ተቀብሎ መተግበር እንደሚገባ፣ በእቅድ እንዲመሩ ማድረግም እንደሚያስፈልግ፣ ተሰብሳቢ ሂሳቦችን ለይቶ እንዲመለሱ ማድረግ እንደሚያሻ እንዲሁም ህጉንና አሰራሩን በመከተልና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የማያገለግሉ ንብረቶችን በህጉ መሠረት ማስወገድ እንደሚገባ፣ የኬሚካል አወጋገድ ጉዳይ በተማከለና በተደራጀ ሁኔታ ተጠንቶ ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚያሻ ለዚህም በኬሚካል ላይ ምርምር የሚያደርጉና ለዚህ ጉዳይ ቅርብ የሆኑ አካላትና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት ጉዳዩን ማጥናት እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *