News

የእናቶችን የጤና ችግሮች ለመከላከል የመ/ቤቱ ሴት ሰራተኞች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ

Posted

በእናቶች ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን ለመከላከል የመ/ቤቱ ሴት ሰራተኞች የበኩላቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የሴቶችና ወጣቶች ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት በእናቶች ጤንነት ላይ ያተኮረ የግማሽ ቀን ስልጠና ለመ/ቤቱ ሴት ሰራተኞች ሚያዝያ 30፣ 2011 ዓ.ም በመ/ቤቱ አዳራሽ ተሰጥቷል፡፡

የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናውን የሰጡት የመ/ቤቱ የስራ አካባቢ ደህንነትና ጤንነት ባለሙያ አቶ ታመነ ጌታሁን የእናቶችን ጤንትና ህይወት አደጋ ላይ በሚጥሉ የጤና ቸግሮች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡ አቶ ታመነ እርግዝናና ወሊድ፣ የማህጸን ጫፍና የጡት ካንሰር፣ እንደ ኤች አይ ቪ ያሉ የአባላዘር በሽታዎች፣ ጾታዊ ጥቃትና ውርጃ   ያሉ ሁኔታዎች ሴቶች በእርግዝናና በወሊድ ወቅት ወይም ከወሊድ በኋላ የተለያዩ የጤና ችግሮች እንዲደርሱባቸው ከዛም አልፎ እንዲሞቱ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል፡፡

በሀገራችን በየአመቱ ከ11ሺህ እስከ 13ሺህ ሴቶች ከወሊድ ጋር በተያዙ የጤና ችግሮች ምክንያት በወሊድ ወቅት ህይወታቸው እንደሚያልፍ ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር ተያይዞ ሴቶችን የሚያጋጥሙ የጤና ችግሮች በጽንሱ ጤንትና ደህንነት ላይም አደጋ ያስከትላሉ ብለዋል፡፡

አቶ ታመነ፣ ካንሰር በተለይም የማህጸን ጫፍ ካንሰር፣ ኤች አይ ቪን ጨምሮ የተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች እንዲሁም ህገወጥ ውርጃ በእናቶች ጤናና ህይወት ላይ የሚያስከትሉትን አደጋም በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የእናቶችን ጤንትና ህይወት አደጋ ላይ የሚጥሉት እነዚህ የጤና ችግሮች የሚያስከትሉትን ጉዳት፣ ሲከሰቱ የሚያሳዩትን ምልክት፣ መከላከያ ዘዴያቸውን እንዲሁም በአጠቃላይ ሴቶችን በተለይም የእናቶችን ጤንነት በእርግዝናና በወሊድ ወቅት ጠብቆ ለማቆየት መወሰድ ያለባቸውን ጥንቃቄዎችና እርምጃዎች አስመልከቶ በሰፊው አስረድተዋል፡፡

የጤና ችግሮቹ እንዳይከሰቱ አስቀድሞ ጥንቃቄ ማድረግና ከተከሰቱም በኋላ ተገቢውን ህክምና መከታተል እንዲሁም በህክምና ተቋማት ውስጥ መውለድ እንደሚያስፈልግ ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ በማያያዝም የመ/ቤቱ ሴት ሰራተኞች የተጠቀሱትን ጤና ችግሮች በመከላከል በራሳቸው ከሚወስዱት ጥንቃቄና በሀገር አቀፍ ደረጃ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ በማህበረሰቡ ውስጥ ስለጤና ችግሮቹ ግንዛቤ በመፍጠር ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የሴቶችና ወጣቶች ጉዳዮች ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ሙሉ ጥሩነህ የመ/ቤቱን ሴት ሰራተኞች ጤንነት ከማስጠበቅ አኳያ ቀደም ባሉት ጊዜያት በዳይሬክቶሬቱ አስተባባሪነት ፈቃደኛ ሴት ሰራተኞች የማህጸን ጫፍ ካንሰር ምርመራ ማድረጋቸውን አስታውሰው በእናቶች ጤንነት ላይ የተሰጠውን ስልጠና ጠቃሚ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በእናቶች ጤና ላይ ከተሰጠው ስልጠና በተጨማሪ በመድረኩ ላይ በመ/ቤቱ የሴቶች ፎረም የብድር አሰጣጥ መመሪያ ላይ በተደረጉ ማሻሻያዎች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ በወቅቱ የብድር አሰጣጡን የተመለከተ ውሳኔ የተላላፈ ሲሆን የብድር ኮሚቴው አባላት ምርጫም ተካሂዷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *