News

የኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ (EGP) ሥርዓትን የሚመለከት ስልጠና ተጀመረ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ኦዲተሮች በመንግስት ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት ላይ ያላቸውን እውቀት የበለጠ አጎልብተው ውጤታማና ወቅቱን የሚመጥን የኦዲት ስራ እንዲያከናውኑ ሊያደርጋቸው የሚችል ስልጠና መሰጠት ተጀምሯል፡፡

የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም በተጀመረውና ከመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በመጡ ባለሙያዎች በሚሰጠው ስልጠና ከተለያዩ የኦዲት የስራ ክፍሎች የተውጣጡ የፋይናንሽያል ኦዲተሮች  በስድስት ዙሮች የሚሳተፉ ሲሆን  ስልጠናውን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሠ በንግግር ከፍተዋል፡፡

ስልጠናው የመ/ቤቱ ኦዲተሮች በተቋማት የግዥ ስርዓት አተገባበር ላይ በሚያደርጓቸው ኦዲቶች ላይ ጠቃሚ ግንዛቤ የሚያገኙበት መሆኑን በንግግራቸው የጠቀሱት ክቡር ም/ዋና ኦዲተሩ በተለይም የመንግስት ግዥ ስርዓትን አስመልክቶ  በአዲስ መልክ እየወጣ ባለው የተሻሻለ አዋጅና ወደፊት አዋጁን ተከትለው በሚወጡ የተለያዩ ማስፈጸሚያ መመሪያዎች መሠረት ኦዲቶችን  ለማከናወን ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

አክለውም በተለይም በተቋማት የግዥ ስርዓት አተገባበር ላይ በሚካሄዱ  የህጋዊነት ኦዲቶች ግዥዎች በወቅታዊው የግዥ ስርዓት መሠረት እየተከናወኑ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ስልጠናው ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑን ጠቅሰው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ወደፊት ለመተግበር ላቀደው ዲጂታላይዝድ የኦዲቲንግ ስርዓት አተገባበር ጠቃሚ በመሆኑ ሠልጣልኞች ስልጠናውን በትኩረት እንዲከታተሉ አሳስበዋል፡፡

ይህንና ቀደም ሲልም ተመሳሳይ ስልጠናዎችን በመስጠት ትብብር እያደረገ ላለው የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን እንዲሁም ስልጠናውን በማመቻቸት ላዘጋጀው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት ምስጋናቸውን ያቀረቡት ክቡር አቶ አበራ ታደሠ ስልጠናው የተሳካና ውጤታማ እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

በስድስት ዙሮች በሚሰጠው ስልጠና በጥቅሉ 400 ያህል የመ/ቤቱ የፋይናንሽያል ኦዲተሮች የሚሳተፉ መሆኑና በዚህ የመጀመሪያ ዙር ስልጠናም 72 ኦዲተሮች ለሶስት ቀናት ስልጠናውን የሚከታተሉ መሆኑን ከመ/ቤቱ የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *