News

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተመደበለትን ከፍተኛ በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲያውል ተጠየቀ

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በአገሪቱ ከፍተኛ በጀት ከሚመደብላቸው የመንግስት መ/ቤቶች አንዱ  እንደመሆኑ መጠን በጀቱን በአግባቡ ሥራ ላይ ሊያውል እንደሚገባ በኢ.ፊ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ታህሳስ 26፣ 2009 ዓ.ም በሚኒስቴር መ/ቤቱ የ2007 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝት ላይ የፋዊ ስብሰባ ባደረጋበት ወቅት ጠየቀ፡፡

በዕለቱ በቋሚ ኮሚቴውና በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን የሚኒስቴር መ/ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ለተነሱት ጥያቄዎችና ከኦዲት ግኝቱ በኋላ ባከናወኗቸው የማስተካከያ ሥራዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በኦዲት ግኝቱ እንደተገለፀው በሚኒስቴር መ/ቤቱ የተቀፅላ ሌጀር ሚዛን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ በተደረገው ምርመራ ብር 11 ሺህ የሒሳብ ሚዛን እንደሚያሳይ የተለያዩ ግለሰቦች የቅድሚያ ክፍያ የወሰዱ መሆኑ፤ ከ2007 በጀት ዓመት የዞረ ተከፋይ ሒሳብ መነሻ ብር 163,942,074.98 ክሬዲት ሚዛን ማሳየት ሲገባው ዴቢት ሚዛን ማሳየቱን፤ ለተለያየ ሆቴሎች በጥቅሉ ብር 2,972,685.64 ጨረታ ሳይወጣ የመስተንግዶ አገልግሎት ግዢ መፈፀሙና ለግዢው ውል አለመቅረቡን፤ ከ221 ሺህ ብር በላይ ለተፈፀሙት የዕቃና የአገልግሎት ግዢዎች በመመሪያው መሠረት ቢያንስ ከሦስት ድርጅቶች የዋጋ መወዳደሪያ መሰብሰብ ወይም የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲን ማስፈቀድ ሲገባ የዋጋ ማወዳደሪያ ሳይሰበሰብ ወይም ሳያስፈቅድ ግዢ የፈፀመ መሆኑና መ/ቤቱ ጫማ ግዢ ፈፅሞ ለሠራተኞቹ መስጠት ሲገባው ከብር 22ሺህ በላይ በጥሬ ገንዘብ ክፍያ መፈፀሙ በኦዲት ሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

news-16-2009-6በሌላ በኩል ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከአራት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ከአንድ ድርጅት ጋር በገባው የውል ስምምነት መሠረት በ2007 በጀት ዓመት ብር 14,519,235.75፣ በ2006 በጀት ዓመት ብር 8,907,336.46 የተጨማሪ ዕሴት ታክስን ጨምሮ ለዩኒቨርስቲዎች ክፍያ የተፈፀመ ቢሆንም ዩኒቨርስቲዎቹ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ ስለመሆናቸው የምዝገባ ሰርተፍኬት እና ደረሰኝ አለመቅረቡ፤ ለመ/ቤቱ የበላይ ኃላፊዎች ለህክምና ወጪ ለተፈፀመው ክፍያ ብር 272,956.87 በመመሪያው መሠረት ማስረጃው ሳይቀርብ በወጪ ተመዝግቦ የተገኘ መሆኑ፤ በሁሉም የወጪ ማስመስከሪያዎች (Payment Voucher) ላይ ክፍያ ከመፈፀሙ በፊት በጀት አለመፈቀዱ እንዲሁም በአብዛኛው የወጪ ማስተካከያዎች ላይ የሒሳቡ ትክክለኛነት በሚመለከተው ሠራተኛ በፊርማ አለመረጋገጡ፤ በመ/ቤቱ ለ2007 በጀት ዓመት የተፈቀደው የወጪ በጀት አጠቃቀም በየሒሳብ ኮዶቹ ሲታይ ከመደበኛ ወጪ በጀት ከ10% በላይ ብር 7,063,084.39 ሥራ ላይ ያልዋለ ሲሆን ብር 1,853,811.93 ደግሞ ለየሒሳብ ኮዱ ከተደለደለው በጀት በላይ የወጣ መሆኑ በኦዲት ግኝቱ ተመላክቷል፡፡

ከቋሚ ኮሚቴው አባላት በተጨማሪ ሌሎች የሚመለከታቸው የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ የመንግሰት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ እንዲሁም የመንግስት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጥያቄዎችንና አስተያቶችን የሰጡ ሲሆን ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከኦዲት ግኝቱ በኋላ ከመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ጋር በመነጋገር ግዢዎችን እየፈፀመ እንደሚገኝ ቢገለፅም በሚፈለገው መጠን ተፈፃሚ አለመሆኑን፣ አሁንም ከተመደበ በጀት በላይ ከሒሳብ መደብ የመጠቀም ሁኔታ እንዳለ፤ የተከፋይና የተሰብሳቢ ሒሳብ እልባት ሊሠጣቸው እንደሚገባ፣ የፋይናንስ ሥርዓትንን እና የውስጥ ኦዲት ቁጥጥርን ማሻሻል እንደሚያሻ እና መ/ቤቱ በኦዲት ግኝቱ የታዩትን ችግሮች በሙያና ብቃት ማነስ ወይም በኪራይ ሰብሳቢነትና መልካም አስተዳደር ችገር ምክንያት የተፈጠሩ ስለመሆናቸው ለይቶ የሠራው ሥራ ካለ ማብራሪያ እንዲሠጥበት ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡

የኦዲት ግኝቱንም መሠረት በማድረግ ቋሚ ኮሚቴው ሚንስቴር መ/ቤቱ በደንብና መመሪያ እንዳይመራ ያደረገውንና የተፈጠሩትን ስህተቶች ለማስተካከል የተወሰዱ እርምጃዎችን እንዲያብራሩ ለሚኒስቴር መ/ቤቱ አመራሮች ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል፡፡ 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ አብተው እንደገለፁት በመውጫ ስብሰባ ጥሩ መማማር እንደነበረና ለሥራቸው እንደጠቀማቸው፤ የኦዲት ሪፖርቱን ተከትሎ የቅርብ ክትትል ለማድረግ እንዳስቻላቸው፤ የፋይናንስ ስርዓታቸውን ሊያሻሽሉ የሚችሉ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዳቸውንና በተለይም ከገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር በተሠጣቸው ግብረመልስ መሠረት ያልታረቁና ያላለቁ ሥራዎችን በኮንትራት በማሰራት እንደሚያስተካክሉ ገልፀው የሒሳብ ምዝገባ በወቅቱ ሚኒሰቴር መ/ቤቱ እንዲያደርግ የተሰጠውን አስተያየት በመቀበል በቀጣይ የተቋሙን መዋቅር የማሻሻልና በስልጠና ሙያተኛውን ማብቃት ላይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ገልፀዋል፡፡

በኦዲት ግኝቱ ስህተት ተፈፅሞባቸዋል ተብለው በተነሱ ጉዳዮች ላይ  ሚኒስትሩ ምላሽ ሲሰጡ እንደገለፁት የመደበኛ ተከፋይ ሒሳብን በተመለከተ የተፈጠረውን ስህተት ላይ የማስተካከያ እርምጃ መወሰዱን፣ የወጪ ሒሳብን በተመለከተ ለመስተንግዶ በሚል ይፈፀም የነበረን ክፍያ ከመንግስት ግዢና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ ጋር በመነጋገር መስተካከሉን፤ ዩኒቨርስቲዎችን አላግባብ ተጨማሪ እሴት ታክስ በማስከፈል ለገቢዎችና ጉሙሩክ ባለሥልጣን ተከፍሎ የነበረውን ክፍያ ተመላሽ ለማድረግ ለባለሥልጠኑ እንደተገለጸና ምላሽ እየጠበቀ እንደሆነ፤ መረጃ ያልተገኘባቸው የሒሳብ ማስተካከያዎች መረጃቸው ተፈልጎ እንዲያያዝና ሒሳቡ በትክክለኛው አሠራር እንዲጣጣም (Balance) መደረጉን፤ የወጪ ማስተካከያ ሰነድን በሚመለከት (በሀላፊ ያልተረጋገጡ የሂሳብ ሰነዶችን ለማለት የተፈለገ ይመስለኛል ፋይናንስ፣ ግዢና ንብረት ዳይሬክተር ባለመኖሩ  በቦታው ተወካይ በማስቀመጥ በሰነዶች ላይ ፊርማ እንዲኖር እየተደረገ መሆኑን ጨምረው አስረድተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር መብራህቱ መለሠ ሲያስረዱ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ዋነኛ ችግሮች የሰው ሃይል አለመኖርና ጥልቅ ክትትልና ቁጥጥር ይልነበረ መሆናቸውን ጠቁመው የውስጥ ኦዲተርን በተመለከተ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመቅረፍ እየሠሩ መሆኑን፣ የኪራይ ሰብሳቢነትና መልካም አስተዳደር ችግርን ከመቅረፍ አኳያ በተቋሙ የለውጥ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሰራ ያለ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የፌደራል ዋና ኦዲተር ክቡር ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በመጨረሻ በሰጡት አስተያየት ሚኒስቴር መ/ቤቱ የኦዲት ሪፖርቱን መሠረት አድርጎ የማስተካከያ እርምጃዎች መውሰዱን በጥሩ ጎኑ እንደሚያዩት፤ ተሰብሳቢ ሒሳብን በተመለከተ የተፈጠረው ስህተትን መ/ቤቱ በአግባቡ ሊለየውና ትክክለኛውን ማስተካካያ ሊወስድ እንደሚገባ፤ የመስተንግዶ አገልግሎትን በተመለከተ ከግዢ ኤጀንሲ ጋር በመነጋገር የተወሰደው መፍትሔ ጊዚያዊ እንጂ ዘላቂ ሊሆን ስለማይችል  ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መ/ቤት ጋር በመነጋገር ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት እንደሚያስፈልግና የኃላፊዎች የህክምና ወጪ በተመለከተ ለተፈፀመው ክፍያ ማስረጃው  መያያዙ ጥሩ ቢሆንም እንዲህ አይነቱ ችግር በሌሎች የመንግስት መ/ቤቶች ላይ የሚታይ ስለሆነ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብበር ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ ማስረጃዎቹን መ/ቤቶቹ እንዲያቀርቡ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

የቋሚው ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በመጨረሻ በሰጡት ሃሳብ ቋሚ  ኮሚቴው ሚኒስቴር መ/ቤቱ የኦዲት ግኝቱን መሠረት አድርጎ የሠራቸው ስራዎች በመልካም ጎነ እንደሚያየው፤ አደረጃጀትን በተመለከተ ለማስተካከል የተጀመረው ሥራ እንደሚበረታታ እና የኦዲቱን ሥራ እንደ አቅም መገንቢያ ተወስዶ ወደ ሥራ መገባቱ ጥሩ ጅምር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሆኖም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ትልልቅ ግቦች ከተሰጣቸው ተቋማት አንዱ እንደመሆኑ ምክር ቤቱ አጽድቆ የሚመድብለትን በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል እንደሚጠበቅበት፤ በአጠቃላይ በአገሪቱ የፋይናንስ ባለሙያ እጥረት ቢኖርም ተቋሙ የሰው ሃብት ማብቃት ላይ መስራት እንደሚኖርበት፣ የውስጥ ቁጥጥርና ክትትል ሥርዓትን መሻሻል እንደሚገባ፤ ከጨረታ እና ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚደረጉ ወጪዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያሻ፤ ሚኒስቴተር መ/ቤቱ በስሩ ያሉ ተጠሪ መ/ቤቶችን የመደገፍ ስራ ሊሠራ እንደሚገባ እና የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ በመቀጠል መልካም አስተዳደርን ሊያሰፍን እንደሚገባ አምባሳደሩ አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *