News

የአፍሪካ እንግሊዝኛ ተናጋሪ አገሮች የኦዲት ሴሚናር በቻይና ተካሄደ

ለአፍሪካ እንግሊዝኛ ተናጋሪ አገራት ዋና ኦዲተሮች የ2019 የኦዲት ሴሚናር በቻይና አዘጋጅነት እ.ኤ.አ. ከኦክቶበር 14-23/2019 በቤጂንግ ከተማ እና በጉያንግ ግዛት ጉዡ (Guizhou) ከተማ ተካሄደ፡፡

በሴሚናሩ ላይ ከ16 የአፍሪካ አገራት 35 ተሳታፊዎች የታደሙ ሲሆን አገራችንም በሁለት ተሳታፊዎች ተወክላለች፡፡

የቻይና መንግስት ዋና ኦዲተር መ/ቤት ዋና ኦዲተር ሚስ ሁ ዘጁን  ሴሚናሩን ሲከፍቱ ተሳታፊዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ የቻይና እና የአፍሪካ ግንኙነት ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ መሆኑን በመግለጽ ግንኙነቱ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ዋና ኦዲተሯ በመቀጠልም ይህ ሴሚናር አንዳችን ከሌላው የምንማርበትና ልምድ የምንለዋወጥበት እንደሚሆን እተማመናለሁ ብለዋል፡፡ የቻይናን የኦዲት አሰራር ልምድ የምናካፍልበት መድረክ ይሆናል ያሉት ዋና ኦዲተሯ በተለይም ድህነት ቅነሳ ላይ የተሰሩ ስራዎችና ከዚህ አንፃር ኦዲቱ ያደረገውን ድጋፍ ልምድ የምናካፍልበት ይሆናል በማለት ሴሚናሩን አስጀምረዋል፡፡

በሴሚናሩ የቻይና መንግስት ኦዲት ንድፈ ሃሳብና አሰራር እድገት (Chinese Government Auditing Theory and Practices Development)፣ በድህነት ቅነሳ ላይ የሚሰራ ኦዲት (Poverity Allevation Auditing)፣ የአካባቢ ጥበቃ ኦዲት አሰራር (Environmental Auditing)፣ በመሰረተ ልማት ላይ የሚውል መዋዕለ ንዋይ የኦዲት አሰራር (Infrastructure Investment Audit) እንዲሁም በጉያንግ ግዛት የድህት ቅነሳ ፕሮግራም ላይ የተሰራው ስራ እና የግዛቱ የኦዲት ጽ/ቤት በድህነት ቅነሳ ላይ እያከናወነ ያለው ኦዲት ተዳሷል፡፡

በእያንዳንዱ ቀን በተደረገው ውይይት የአፍሪካ አገራት ዋና ኦዲተሮች በርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ልምድ በማቅረብ ሰፊ የእርስ በርስ የልምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡

ከሴሚናሩ ጎን ለጎን በቻይና ኦዲት መ/ቤት  የተከናወኑ ስራዎች በተለይም ከድህነት ቅነሳ ጋር ተያይዞ የተሰሩ ስራዎችና ሌሎች የልማት ስራዎችን የተመለከቱ ጉብኝቶች ተደርገዋል፡፡

በጉያንግ አስተዳደር ግዛት የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ፣ የጉያንግ ግዛት ገዥ እና ሌሎችም የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ለሴሚናሩ ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ዝግጅት አድርገዋል፡፡ ሁለቱ የስራ ኃላፊዎች የግዛቱን የስራ እንቅስቃሴ በተመለከተ ንግግር አድርገዋል፡፡ በዚህ ዝግጅት የአፍሪካ ተሳታፊዎችን በመወከል የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ንግግር እንዲያደርጉ ተጋብዘው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ክቡር ዋና አዲተር ባስተላለፉት መልዕክት አፍሪካ ከቻይና የምትማራቸው በርካታ ጉዳዮች ያሉ ቢሆንም አፍሪካም ለቻይና የምታካፍላቸው ልምዶች ያሏት በመሆኑ ግንኙነታችን የጋራ  ተጠቃሚ ያደርገናል ብለዋል፡፡ ክቡር ዋና ኦዲተር አክለውም ቻይና ከግማሽ ምዕተ ዓመት ባነሰ ጊዜ ያስመዘገበችው እድገት በጣም ከፍተኛ እና አስገራሚ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ቻይና አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው እድገት በማስመዝገብ የዓለም ሁለተኛውን ግዙፍ ኢኮኖሚ ማስመዝገቧን አፍሪካዊያን ልንከተለው የሚገባን ነው ብለዋል፡፡ ጠንካራ የስራ ባህላቸው፣ ታታሪነት የተሞላበት የማህበራዊ የኢኮኖሚ እድገት እና የተመዘገበው የድህነት ቅነሳ ስኬት  እንዲሁም በቴክኖሎጂ የተደረሰበት እድገት የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የቻይና የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በሚያከናውነው የተፈጥሮ ሃብት አጠባበቅ የተጠያቂነት ኦዲት የታገዘው የተፈጥሮ ሃብትና የአካባቢ ጥበቃ ስራ የቻይና መንግስት ያለውን ቁርጠኝነት በተለየ ሁኔታ ያሳያል በማለት ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም ክቡር ዋና ኦዲተር እንደዚህ ዓይነቱ የእድገት ስኬት ትክክለኛ የፖሊሲ አቅጣጫ በመከተልና በመተግበር፣ ቀጣይነት ያለው ተቋማዊ አሰራርና ተጠያቂነትን ያረጋገጠ አመራር በመስጠት የመጣ መሆኑን እገነዘባለሁ ብለዋል፡፡ በዚህም አፍሪካ እንደ ታዳጊ አህጉር ከዚህ ልምድ ብዙ መማር እናዳለባት እና አገራትም እንደተጨባጭ ሁኔታቸው ከቻይና የተገኘውን ተሞክሮ መተግበር እንዳለባቸው በአጽዕኖት አስገንዝበዋል፡፡ ለዚህም የአፍሪካ የዋና ኦዲተር መ/ቤቶች  የቻይናን ልምድ ወደየአገሮቻቸው በመውሰድ በሚከናወነው የልማት ስራ ተገቢውን እገዛ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል በማለት ገልጸዋል፡፡

አፍሪካ በርካታ የተፈጥሮ ሃብት የታደለች እና በፈጣን እድገት ላይ ያለች አህጉር መሆኗን የገለፁት ክቡር አቶ ገመቹ የአፍሪካ መሪዎች የየአገሮቻቸውን እቅድ ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እና ከተባበሩት መንግስታት የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦች እቅድ ጋር በማጣጣም ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ ለተግባራዊ ለውጥ መትጋት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የእነዚህን አጀንዳዎች ተግባራዊነት ለማረጋገጥ ለአፍሪካ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አስፈላጊ መሆኑን የገለፁት አቶ ገመቹ ቻይና በአፍሪካ የምታደርገው ኢንቨስትመንት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢመጣም ተጨማሪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ሊኖር እንደሚገባና በተለይም በሰው ኃይል አቅም ግንባታና በቴክኖሎጂ እድገት አህጉሩን ለመለወጥ የቻይና ድጋፍ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

ክቡር አቶ ገመቹ በመጨረሻም የጉዡ ካምፓኒዎች ወደ አፍሪካ በመምጣት በኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ፣ በባህልና በትምህርት ፕሮግራሞች የግንኙነት መድረኮች እንዲፈጥሩ እና በግዛታችሁ ብሎም እንደ አገር ያሳካችሁትን የድህነት ቅነሳ ልምድ ለአፍሪካ እንድታካፍሉ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *