የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሚገኘው የአጂማ ጫጫ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት ዝግጅትና አፈጻጸም ላይ በ2013/2014 በጀት ዓመት ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት መሠረት በርካታ ክፍተቶች መታየታቸው ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥር 3 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት ላይ ነው፡፡
ለመስኖ ልማት ፕሮጀክቱ ከተመደበው ብልጫ ብር 47.1 ሚሊዮን መከፈሉ፣ ከግንባታው ተቋራጭ ጋር በተደረገ ውል መሰረት ጊዜውን ጠብቆ የመነሻ ስራ ፕሮግራም ያለመቅረቡና ዋናው ስራ በወቅቱ ያለመጀመሩ፣ የፕሮጀክቱ አማካሪ ሳያጸድቃቸው ስራዎች መከናወናቸው፣ ለፕሮጀክቱ ሥራ የሚያስፈልገውን መሬትና መሬቱ የሚገኝበትን ትክክለኛ ስፍራ መሬቱን ለሚያስለቅቁ የመንግስት አካላት በወቅቱ ያለመላኩና የአካባቢ ተጽዕኖን የሚከታተል ባለሙያ በፕሮጀክት ሳይት ላይ ያለመኖሩ እንዲሁም ስለዚሁ ጉዳይ የሚገልጽ ሪፖርት ያለመዘጋጀቱ በኦዲት ሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡
ከዚህም ባለፈ የአፈጻጸም ሪፖርቶችን በወቅቱ በመገምገም ግብረ መልሶችን በወቅቱ ያለመስጠት፣ የአዋጭነት ጥናትና የዲዛይን ስራ ላይ ክፍተቶች መኖራቸው እና ለፕሮጀክቱ ስራ ከቦታቸው ለሚነሱ አርሶ አደሮች በሚከፈለው የካሳ አከፋፈል ሥርዓትና አካሄድ ላይ የጎላ ክፍተት መታየቱና ተነሺዎች ቅሬታ ስለሚያቀርቡበት መንገድ ተገቢ ግንዛቤ ያለመሰጠቱ በውይይቱ ላይ ከተነሱ የኦዲት ግኝቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
በመድረኩ የተነሱትን የኦዲት ግኝቶች መሰረት በማድረግ በመድረኩ ላይ የተገኙት የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታውን ክቡር አቶ ብርሃኑ መገረሳን ጨምሮ ምላሽ የሰጡት የሚኒስቴር መ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች የኦዲት ግኝቶቹ ተገቢና ትክክለኛ መሆናቸውን ጠቅሰው ከኦዲቱ በኋላ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በሰጠው የማሻሻያ ሀሳብ መሰረት እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውንና በአሁን ሰዓት ያለው የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 44% የደረሰና በመጪው የ2016 ዓ.ም በተያዘለት ዕቅድ መሰረት እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል፡፡
የካሳ አዋጅ የማሻሻል ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቀሱት የስራ ኃላፊዎቹ በርከታዎቹ ችግሮች ቀደም ሲል ሚኒስቴር መ/ቤቱ በአዲስ አደረጃጀት ከመዋቀሩ በፊት በነበሩ የአሠራር ስርዓቶች ሳቢያ የተከሰቱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በሀገሪቱ እየተሰሩ ያሉትን መሰል ፕሮጀክቶች ዝግጅትና አፈጻጸም በመስክ ምልከታ ማየታቸውንና ችግሮችንም መለየታቸውን ጨምረው የጠቀሱት የስራ ኃላፊዎቹ የጸጥታ ሁኔታዎች፣ የካሳ አከፋፈል ሥርዓት፣ በመስኖ ሴክተሩ ላይ ያሉ የተቋራጮችና የአማካሪዎች የአቅም ክፍተቶች እንዲሁም የግንባታ ግብአቶች እጥረት በፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ የሚታዩ ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው በመስኖና ግድብ ፕሮጀክት ዝግጅትና አፈጻጸም ላይ ስፋት ያላቸው ችግሮች መታየታቸውን የኦዲት ሪፖርቱ የሚያሳይ በመሆኑ ክፍተተቶቹ በአፋጣኝ መታረም አለባቸው ብለዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ የሚኒስቴር መ/ቤቱን የስራ ኃላፊዎች ምላሾች ተከትሎ በሰጡት አስተያየት አዋጭነት ጥናት በአግባቡ ያለመደረጉ እና በአማካሪ ሳያረጋግጥ ክፍያ መፈጸም፣ አማካሪዎች በፕሮጀክቶች ሳይት ላይ ያለመገኘታቸው፣ የካሳ ክፍያ ግምት በአግባቡ ያለመፈጸሙ እና ሌሎች ሰፊ ክፍተቶች መሰረታዊ ክፍተቶች በመሆናቸው ከግኝቶቹ ትምህርት ተወስዶ የተስተካከለ ስራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው ሚኒስቴር መ/ቤቱ በተሰጠው የኦዲት ግኝት ማሻሻያ መሰረት የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ የፕሮጀክቱን አፈጻጸም መግለጽ መቻሉ የሚያበረታታ ቢሆንም ቀደም ሲል የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በበርካታ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ዝግጅትና አፈጻጸም ላይ ኦዲት ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡አያይዘውም ቀደም ሲል በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ ሲታዩ የነበሩ ችግሮች አሁንም ድረስ እያታዩ በመሆኑ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለኦዲት ግኝቶቹ ትኩረት ሰጥቶ ጠንካራ የማሻሻያ ስራዎችን መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
የፕሮጀክት ስራዎች መጀመር ያለባቸው በሀሳብ ደረጃ መጠናቀቅ ያለባቸው የዝግጅት ስራዎች ከተሰሩ በኋላ መሆኑን በአስተያየታቸው የጠቀሱት ክብርት ዋና ኦዲተር የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሳያጸድቅ ስራዎቹ መጀመር እንደሌለባቸውና ገንዘብ ሚኒስቴርም የፕላንና ልማት ሚኒስቴርን ማረጋገጫ ሳያገኝ በጀት መልቀቅ እንደማይገባው አሳስበዋል፡፡
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ አስተየታቸውን የሰጡት የቋሚ ኮሚቲው ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በተሰጠው የኦዲት ግኝት መሻሻያ መሰረት የእርምት እርምጃ መውሰድ መጀመሩና በመድረኩ ለተነሱ ጥያቄዎች የተደራጀና ግልጽ ሪፖርት ማቅረቡ በበጎ ጎኑ የሚታይ ነው ብለዋል፡፡
የመስኖና ግድብ ስራዎች እንደ ሀገር ለተያዙት የልማት ዕድገትና በተለይም የግብርና ስራ ዕቅዶች የጎላ ሚና የሚጫወቱ በመሆናቸው ሚኒስቴር መ/ቤቱ ይህን ከማስፈጸም አንጻር ከፍተኛ ሀገራዊ ሀላፊነት አለበት ብለዋል፡፡
ለቀጣይ መሰል ፕሮጀክቶች የኦዲት ግኝቶቹን መሰረት ያደረጉ የተሻሉ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ ያሳሳቡት ም/ሰብሳቢዋ ካለፉት ክፍተቶች በመማር የፕሮጀክት አካባቢዎችንና ማህበረሰቡን ያማከሉ ስራዎች መስራት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ የሚመለከታቸው ባለድርሻና ሌሎች አካላት የማሻሻያ እርምጃዎች አወሳሰዱ ላይ ክትትል እንዲያደርጉና ሚኒስቴር መ/ቤቱም ፕሮጀክቱ የደረሰበትን አፈጻጸም ሪፖርት እንዲያቀርብ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡