የኦዲት ስራ ድግግሞሽንና በኦዲተሮችና በኦዲት ተደራጊ ተቋማት ላይ ሊፈጠር የሚችለውን አላስፈላጊ ጫናና የጊዜ ብክነት ለማስወገድ እንዲቻል የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የነጠላ ኦዲት አዋጅ ትግበራ ስልጠና ለክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች መሰጠት ጀመረ፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1146/2011 በተሰጠው ተግባርና ስልጣን መሰረት ለክልል መንግስታት የሚሰጠውን የበጀት ድጋፍና ልዩ ድጎማዎችን ኦዲት ማድረግና ማስደረግ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡
ይኸው የክልል መንግስታት ድጋፍና ድጎማ በክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶችም ኦዲት የሚደረግበት ሁኔታ ያለ በመሆኑና ይህ አሠራር የኦዲት ድግግሞሽን የሚፈጥርና በኦዲት አድራጊውም ሆነ ተደራጊ ተቋማት ላይ የስራ ጫናንና የጊዜ ብክነትን የሚፈጥር በመሆኑ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ባዘጋጃቸው ተከታታይ መድረኮች ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ የጋራ ምክክሮች ተደርገው የነጠላ ኦዲት አዋጅ 1251/2013 እና የአዋጁ ማስፈጸሚያ መመሪያ ቁጥር 2/2014 እንዲወጡ ተደርጓል፡፡
በዚሁ መሰረት በክልሎች ላይ ይህንኑ አዋጅ ለመተግበር እንዲቻል ከጥቅምት 22 ቀን 2015 ጀምሮ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የትግበራ ማስጀመሪያ ስልጠና መሰጠት ተጀምሯል፡፡
ይህንኑ ተከትሎ ጥቅምት 22 ቀን 2015 ዓ.ም ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ዋና ኦዲተር መ/ቤት የፋይናንሽያል ኦዲት ዳይሬክተሮችና ስራ አስኪያጆች የነጠላ ኦዲት አዋጅ የአፈጻጸም መመሪያን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በሀዋሳ ከተማ ተሰጥቷል፡፡
በቦታው ላይ በመገኘት ስልጠናውን ያስጀመሩትና በነጠላ ኦዲት አዋጅ ላይ ገለጻ ያደረጉት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አሰልጣኝ አቶ እዮብ ጉታ የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ በማንሳት እንደገለጹት የነጠላ ኦዲት አሠራር አሜሪካን ጨምሮ በሌሎች ሀገራትም የሚተገበር መሆኑንና ለክልል መንግስታት የሚሰጡ ድጎማዎችና ሽልማቶች በዚህ አሠራር ኦዲት እንደሚደረጉ ጠቅሰዋል፡፡
የነጠላ ኦዲት ትግበራ የሚያካትታቸውን የኦዲት ዓይነቶችና በኦዲቱ የሚሰሩ ስራዎችን በገለጻቸው ያብራሩት አቶ እዮብ የነጠላ ኦዲት አሠራር የውስጥ ቁጥጥር ስርዓትንና የፋይናንስ አስተዳደርን ለማጠናከር፣ የድጋፍና ድጎማ ሂሳቦች ኦዲት ወጥ በሆነ ስርዓት እንዲመራ ለማድረግ፣ ውጤታማ የኦዲት ሀብት አጠቃቀም እንዲኖር ለማስቻል፣ በኦዲት ድግግሞሽ ሳቢያ ሊፈጠር የሚችለውን ጫና ለመቀነስ እና ድጋፍ ያደረጉ ተቋማት በኦዲት ውጤቱ ላይ እምነት እንዲጥሉ ለማስቻል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስቀምጠዋል፡፡
ስልጠናው በቀጣይ ለሲዳማ እና ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስታት እና ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የሚሰጥ ሲሆን ወደፊትም ለሌሎች ክልልሎች ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ተመሳሳይ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ታውቋል፡፡