News

የመ/ቤቱ አመራሮችና ሠራተኞች 6ኛውን ሀገር አቀፍ የአረንገዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር አካሄዱ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አመራሮችና ሠራተኞች ዘንድሮ በ2016 ዓ.ም “የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለውን የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር መሠረት በማድረግ በርካታ ችግኞችን ተክለዋል፡፡

ሀምሌ 12 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 የካ ጣፎ ኮንዶሚንየም ልዩ ስሙ ጮሪሶ 2 በተባለው ስፍራ በተካሄደው ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤና ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሠን ጨምሮ ሌሎች የመስሪያ ቤቱ አመራሮችና ሠራተኞች የተሳተፉ ሲሆን የተለያዩ የዛፍ ዝርያ ያለቸውን 3,000 የሚሆኑ ችግኞችን በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡

ክብርት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩን ሲያስጀምሩ ባደረጉት አጭር ንግግር ሀገራዊው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር የሀገሪቱን የአየር ንብረት አመቺ ከማድረግ ባለፈ የተራቆቱ መሬቶችን በእጽዋት የተሸፈኑ ለማድረግ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም መ/ቤቱ ሀገራዊው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ያሉ ቦታዎችን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች በየአመቱ በርካታ ችግኞችን በመትከል የነቃ ተሳትፎው ማድረጉን ክብርት ዋና ኦዲተሯ ገልጸዋል፡፡

የተተከሉትን ችግኞች ተንከባክቦ ማሳደግም የመርሀ ግብሩ አንድ አካል በመሆኑ በዘንድሮው ዓመትም መ/ቤቱ የተተከሉትን ችግኞች ተንከባክቦ የማሳደግ ሃላፊነት ያለበት በመሆኑ ከአካባቢው የአስተዳደር አካላት ጋር በመቀናጀት ቀጣይ የመንከባከብና የማሳደግ ስራዎች የሚሰሩ መሆኑን የጠቀሱት ክብርት ወ/ሮ መሠረት በችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩ ቅድመ ዝግጅትና ሂደት ለመ/ቤቱ ከፍተኛ ትብብር ላደረጉ በየደረጃው ለሚገኙ የአካባቢው አስተዳደር አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በየአመቱ በተለያዩ ቦታዎች በርካታ ችግኞችን በመትከል የሀገሪቱን የአረንጓዴ አሻራ የማስቀመጥ ግብ ለማሳካት የበኩሉን ጉልህ ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *