News

በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ዓለም አቀፍ የፀረ-ፆታዊ ጥቃት፣ የኤድስ እና የአካል ጉዳተኞች ቀን ተከበረ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አመራሮችና ሠራተኞች ጾታን መሠረት አድርጎ የሚፈጸም ጥቃትን ለመከላከልና ለመቃወም በሀገር አቀፍና በአለም አቀፍ ደረጃ ከህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ አስከ ወሩ መጨረሻ ቀናት የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የፀረ-ፆታዊ ጥቃት፣ የኤድስ እና የአካል ጉዳተኞች ቀንን አስመልክቶ የአንድ ቀን የመታሰቢያ መርሀ ግብር አካሂደዋል፡፡

ህዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም በመ/ቤቱ የተከበረውን ስነ-ስርዓት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩ ሲሆን በንግግራቸው ቀኑ የጸረ- ጾታዊ ጥቃትን ንቅናቄ ለማጠናከርና በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ አግኝቶ ጾታን መሠረት በማድረግ ከሚፈጸሙ ህገ ወጥ ተግባራት እራስን ለማራቅ አልፎም ጾታዊ ጥቃት ፈጻሚዎችን በጋራ ለመታገል የሚያስችል ዝግጁነት የሚፈጥር መሆኑን በመግለጽ የጸረ- ጾታዊ ጥቃት ንቅናቄን አለም አቀፍ መነሻ ታሪክ አንስተው የንቅናቄውን የመጀመሪያ አራማጆች ፈለግ መከተል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ተቆጣጣሪ ተቋም እንደመሆኑና በኦዲት ስራውም ውስጥ የስርዓተ ጾታ ጉዳዮችን አካቶ የሚሰራ እንደመሆኑ ጉዳዩ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ጨምረው የገለጹት ክብርት ዋና ኦዲተሯ የመ/ቤቱ መላው ሠራተኞች በመርሀ ግብሩ የሚተላለፉ ግንዛቤ ማስጨበጫዎችን በንቃት በመከታተል በተቋም ደረጃም ሆነ እንደ ሀገር ሊፈጸሙ የሚችሉ ጾታዊ ጥቃቶችን ለመታገል ቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

ክብርት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ የነጭ ሪባን ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች በሚከበሩባቸው ቀናት ውስጥ በሀገር አቀፍና በአለም አቀፍ ደረጃ የሚከበሩ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ እና የአካል ጉዳተኞች ቀናት እንዲሁም ሌሎች በእነዚህ ቀናት ታስበው የሚውሉ ተዛማጅ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በንግግራቸው ጨምረው ያነሱ ሲሆን እነዚህ ሀገራዊ ችግሮች ሊቃለሉ የሚችሉት ተቋማትና መላው የህብረተሰብ ክፍል የጉዳዮቹን አሳሳቢነት ተረድተው ልዩ ትኩረት ሲሰጡ ነው ብለዋል፡፡

በየአመቱ ከህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ ባሉት አስራ ስድስት የንቅናቄ ቀናት ከላይ ከተጠቀሱት ሌላ ዓለም አቀፍ የጥቃት ሰለባዎች ቀን ፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተከላካዮች ቀን እና ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ቀን በዚሁ ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ቀናት ታስበው የሚውሉ ሲሆን ይህ በመ/ቤቱ የተካሄደው መርሀ ግብርም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡

መርሀ ግብሩን የመ/ቤቱ የሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ዳይሬክቶሬት እና የሰው ሃብት ሥራ አመራር ዳይሬክቶሬት በመቀናጀት ያዘገጁት ሲሆን በዕለቱ  የሴቶችን መብቶች፣ የአካል ጉዳተኞች እና የኤች አይ. ቪ. ኤድስን በሚመለከት የሀገሪቱንና አለም አቀፍ ህጎችና ስምምነቶችን መሰረት ያደረገ  ዝርዝር ገለጻ በመ/ቤቱ የህግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ቀርቦ በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *