የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከክልልና ከአዲስ አበባ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ለመጡ የኦዲት ስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የፋይናንስ አሠራር ግልጸኝነትና ተጠያቂነት አተገባበርን በሚመለከት የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የጋራ ምክክር አካሄደ፡፡
መስከረም 25 ቀን 2015 ዓ.ም ለ1 ቀን የተካሄደው ግንዛቤ ማስጨበጫና የጋራ ምክክር ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ ከሲዳማ እና ከአዲስ አበባ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የመጡ 19 የኦዲት ስራ ኃላፊዎችንና ባለሙያዎችን ያሳተፈ ነው፡፡
የግንዛቤ ማስጨበጫና የጋራ ምክክር መድረኩን በቦታው ተገኝተው በንግግር የከፈቱት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ የግንዛቤ ማስጨበጫውና የጋራ ምክክሩ ዋና ዓላማ በክልልና በወረዳ ደረጃ ያለውን የፋይናንስ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት አተገባበር የመረጋገጥ ሥራዎችን (Verification of budget transparency) የበለጠ ለማሻሻልና በዚህም ላይ በጋራ ለመስራት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አክለውም መ/ቤቱ በሁሉም ክልሎችና ወረዳዎች ደረጃ በአካል ተገኝቶ ግንዛቤውን ተደራሽ ማድረግ ስለማይችል ይህንኑ ግንዛቤ እስከታችኛው እርከን ድረስ ተደራሽ አድርጎ ለመተግበርና ወጥ የሆነ አሠራር ለመፍጠር በመድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በተለይም በክልልና በወረዳ ደረጃ ያለውን የፋይናንስ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት አተገባበር ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የአሠራር ስታንዳርድ ጋር ማቀናጀትና በጋራ ምክክር ወጥ የሆነ አሠራር መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት ም/ዋና ኦዲተሩ በተለይ በወረዳዎች ደረጃ በጋራ ዕቅድ አቅዶ በቀጣይ የተሻለ አሠራር በመፍጠር አፈጻጸማችንን ማሻሻል ይገባል ብለዋል፡፡
በግንዛቤ ማስጨበጫውና የጋራ ምክክሩ ማጠናቀቂያ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ተሳታፊዎች ግንዛቤ ማስጨበጫው በኦዲት አሠራራቸው ላይ የፋይናንስ አሠራር ግልጸኝነትንና ተጠያቂነትን በተመለከተ ቀደም ሲል የነበራቸውን ዕውቀት ያዳበሩበት መሆኑን ጠቅሰው እቅዱን በጋራ ለማሳካት ጥረት እንደሚያደርጉና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩም አሠራሩን እንዲያውቁት እንዳገዛቸው ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ወደየመጡበት ክልል ሲመለሱ በወረዳዎች ደረጃ ይህንኑ አሠራር ሊያጠናክር የሚችል ስልጠና በመስጠት ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡




