News

በደብረ ማርቆስ እና በሰመራ ዩኒቨርስቲዎች የኦዲት ግኝቶች ላይ ይፋዊ ስብሰባ ተካሄደ

በደብረ ማርቆስ እና በሰመራ ዩኒቨርስቲዎች የኦዲት ግኝቶች ላይ ይፋዊ ስብሰባ ተካሄደ

በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የደብረ ማርቆስ እና የሰመራ ዩኒቨርስቲዎችን የ2006 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝቶች ሪፖርት ላይ ይፋዊ ስብሰባ /Public Hearing/ ጥር 4፣ 2008 ዓ.ም አካሄዷል፡፡ በይፋዊ ስብሰባው በሁለቱም ዩኒቨርስቲዎች በ2006 በጀት ዓመት የታዩ የኦዲት ግኝቶች በንባብ ቀርበው የተቋማቱ አመራሮች ምላሽ እንዲሰጡባቸው ተደርገዋል፡፡


ስሰባውን የመሩት በኢፊዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙን ሲሆኑ በስብሰባው ከዋና ኦዲትር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ እና ከተለያዩ ባለደርሻ አካላት የተውጣጡ የቋሚው ኮሚቴው አባላት ተገኝተዋል፡፡ በሁለቱም ዩኒቨርስቲዎች ከበጀት አኳያ የአጠቃቀም ጉድለት እንደነበረ በመግለጽ ባልተፈቀደ በጀት የመጠቀምና በተፈቀዱ በጀቶች ላይም ከተፈቀደ ገንዘብ መጠን በላይ የመጠቀም ችግሮች እንደነበሩ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ከንብረት አያያዝና አስተዳደር አኳያም በከፍተኛ ገንዘብ ግዢ የተገዙ መሣሪያዎች አገልግሎት ላይ ሳይውሉ ለብልሽት ተዳርገው እንደተገኙና በተለያየ ጊዜ መምህራን ከተቋማቱ ሲለቁ በእጃቸው ያሉ ንብረቶችን ሳያስረክቡ እንደሚለቁ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
በውስጥ ገንዘብ አሰባሰብ አንፃርም ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በማያውቀው አሰራር ገቢና ወጪ ሲደረጉ ሞቆየታቸው ተገልጿል፡፡


የተገኙትን የኦዲት ሪፖርቶች ተከትሎ ቋሚ ኮሚቴው የሁለቱንም ዩኒቨርስቲዎች ምላሽና መብራሪያ ያዳመጠ ሲሆን ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ተቋማቱ የፋይናንስ ህጉ እና መመሪያው ከሚያዘው ውጪ የሚፈፅሟቸው ተግባራት ከተጠያቂነት እንደማድናቸው አውቀው ትክክለኛ አሰራርን ተከትለው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የተከበሩ ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙን በበኩላቸው ዩኒቨርስቲዎቹ የውስጥ ኦዲትን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ገልፀው ከንብረት አያያዝና አስተዳደር አኳያ እየታዩ ያሉ ጉድለቶች ለመልካም አስተዳደር ችግር እንደሚሆኑ በመግለፅ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡


 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *