NewsUncategorized

በተደጋጋሚ የማይታረሙ የኦዲት ግኝቶች ህጋዊ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትሉ ተጠቆመ

  • በ2012 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የታዩ የሂሳብ ኦዲት ግኝቶችን ለማስተካከል የተወሰዱ እርምጃዎችን የተመለከተ ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ ተካሂዷል

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2012 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ባካሄደው የሂሳብ ኦዲት  መሰረት የተሰጡ የማሻሻያ አስተያየቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን ለማረጋገጥ ጥር 4 ቀን 2014 ዓ.ም ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት አካሄደ፡፡ በውይይቱ በባለስልጣን መ/ቤቱ ላይ የተካሄደውን የሂሳብ ኦዲት ተከትሎ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተሰጡ የማሻሻያ አስተያየቶች ተግባራዊ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዝርዝር ጥያቄዎች በተቋሙ የስራ ኃላፊዎች ምላሽ እንዲሰጥባቸው ቀርበዋል፡፡

በሚመለከተው አካል የሽያጭ ተመን ሳይጸድቅ የፖስት ካርድ፣ ፖስተር፣ መጽሔትና ቲ- ሸርት ሽያጭ መፈጸሙና አገልግሎቱን በማይመጥን የሙዚየም መግቢያ ተመን አገልግሎት መሰጠቱ፣ ከጥናትና ምርምር ማድረጊያ የተሰበሰበ 10% እና ከማመልከቻ ክፍያ የተሰበሰበ ብር 1,025,129.29  በሂሳብ እንቅስቃሴ መዝገብ ያለመካተቱና በገቢ ሂሳብ ሪፖርት ያለመገለጹ፣ በሚመለከተው አካል ሳይፈቀድ በ2012 በጀት ዓመት ከልዩ ልዩ ፕሮጀክት ፈንድና ከምርምር ፈቃድ ማመልከቻ ፎርም የተሰበሰበ ብር  1,478,900.10 በበጀት ዓመቱ ሂሳብ ውስጥ ያለመካተቱና በወቅቱ ለገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት ያለመደረጉ እንዲሁም ከዚሁ ገቢ ላይ  ብር 1,153,048.93 ለውሎ አበልና ለስልጠና ወጪ መደረጉ፣ የክፍያ መመሪያን ባልተከተለ ሁኔታና የስቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሳይፈቅድ በውሎ አበል ተመን ለሠራተኞች የትርፍ ሰዓት ክፍያ በሚል ብር 26,504.93 መከፈሉና ክፍያው በበጀት ዓመቱ ላልተሰራ ስራ መፈጸሙ እንዲሁም በወቅቱ መወራረድ ሲገባው ከ 1-5 ዓመት ሳይወራረድ በውዝፍ የቆየ የብር 2,859,681.45  የግዥና የውሎ አበል ቅድመ ክፍያ ሂሳብ መገኘቱ በኦዲቱ ወቅት የታዩ ግኝቶች በመሆናቸው በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተሰጡ አስተያየቶች መሰረት እርምጃ ስለመወሰዱ ጥያቄ ቀርቧል፡፡

በተጨማሪም ለቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ ከካፒታል በጀት ብር 30,754,257.50 ድጎማ ለክልሎች መላኩና  ቅድመ ክፍያዎች አስፈላጊ የሆኑ ህጋዊ ውሎች ሳይፈጸሙ የሚከፈሉበት ሁኔታ በመኖሩና የተላከው ገንዘብም በትክክል ለታቀደው ዓላማ ስለመዋሉ መከታተልና መቆጣጠር የሚያስችል ስርዓት ያለመዘርጋቱ፣  ጥቅም ላይ የዋለና ትክክለኛ ዕዳ ስለመሆኑ ማረጋገጥ የሚያስችል የቁጥጥር ስርዓት ሳይዘረጋ ከ1-5 ዓመት  የቆየ የብር  752,970.00 ተከፋይ ውዝፍ ሂሳብ መገኘቱና ከዚህ ውስጥ ብር 20,561.89 የሰነድ ማስረጃ የሌለው ሆኖ መገኘቱ፣ የበጀት ዝውውር መመሪያ ሳይጠብቅ የብር 540,400.00 የበጀት ዝውውር መደረጉ ፣ ከ2012 በጀት ዓመት የባለስልጣን መ/ቤቱ የካፒታልና መደበኛ በጀት ብር 170,938,611.43 ጥቅም ላይ ሳይውል መገኘቱ እና በአንድ የገቢ ደረሰኝ ከአንድ በላይ ገቢ ሰብሳቢዎች ሂሳብ የሚሰበስቡበት ሁኔታ መኖሩ እንዲሁም የተሰበሰቡ ሂሳቦችም በዕለቱ ወደ ባንክ ገቢ የማይደረጉ መሆኑ በኦዲቱ የተረጋገጠ በመሆኑ ክፍተቱን ለማረም የተሰጡ የማሻሻያ ሃሳቦች ተግባራዊ ስለመሆናቸው ምላሽ እንዲሰጡ የባለስልጣን መ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ተጠይቀዋል፡፡

የንብረት አያያዝና አጠቃቀምን በተመለከተ የበጀት ዓመቱ የንብረት ቆጠራ የንብረት ማመዛዘኛን ያላካተተና  የቢሮ ቋሚ ንብረቶች መለያ ቁጥር ያልተሰጣቸው እንዲሁም የተለያዩ ተሸከርካሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ ንብረቶችና ቅርሶች ለብልሽት በሚዳርግ ሁኔታ ከመቀመጣቸው ባሻገር መወገድ የሚገባቸው ንብረቶች በአግባቡ ያለመወገዳቸው እንዲሁም ተገዝተው ያለ አገልግሎት ተከማችተው የተቀመጡና በቢን ካርድ ያልተቀናነሱ ንብረቶች ጭምር መኖራቸው  በኦዲቱ ወቅት የተረጋገጠ በመሆኑ ስህተቶቹን ለማረም የተወሰዱ እርምጃዎች እንዲብራሩ ተጠይቋል፡፡ በተጨማሪም  በ2011 በጀት ዓመት  በባለስልጣን መ/ቤቱ ላይ በተካሄደው ኦዲት መሰረት እርምጃዎች ስለ መወሰዳቸው ለማረጋገጥ  በ2012 ኦዲት ወቅት በተካሄደው ማጣራት እርምጃ እንዲወሰድባቸው አስተያየት ከተሰጠባቸው ግኝቶች መካከል 60% የአሠራር እና  75.47% ገንዘብ ነክ ክፍተቶች ሳይታረሙ መገኘታቸው እና ተቋሙ ላለፉት ተከታታይ ዓመታት ተቀባይነት በሚያሳጣ (adverse) ደረጃ ላይ መገኘቱ  በመድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር ረ/ፕሮፌሰር አበባው ኤያሌውን ጨምሮ በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ ምላሽ የሰጡት የባለስልጣን መ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ተቋሙ የቆዩ ውስብስብ ችግሮች ያሉበት መሆኑን በመጥቀስ ችግሮቹን ለመቅረፍ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ድረስ ተንከባለው የመጡት ችግሮች በዋናነት ቀደም ሲል ከነበሩ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች የእርስ በእርስ ያለመግባባትና ተናቦ ያለመስራት የመነጩ መሆናቸውን የጠቆሙት ኃላፊዎቹ ከወቅቱ አሠራር ጋር ሊሄድ የሚችል ደንብና መመሪያ ያለመኖርም የህግ ክፍተቶች እንዲፈጠሩና በዚህም አሠራሮች በስርዓት እንዳይመሩ ማድረጉን  አመላክተዋል፡፡

በወቅቱ የታዩት ከፊሎቹ የኦዲት ግኝቶች በአሁን ሰዓት የተስተካከሉና ከፊሎቹንም ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት የባለስልጣን መ/ቤቱ ኃላፊዎች ከአቅም በላይ በመሆናቸው ያልተፈቱ ችግሮች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ በተለይም ከአቅም በላይ የሆኑ አንዳንዶቹን ችግሮች ለመቅረፍ እንዲቻል ለገንዘብ ሚኒስቴር ጥያቄ መቅረቡን የጠቀሱት ኃላፊዎቹ ተመን ያልወጣላቸውን  የሙዚየም መግቢያና የሽያጭ ገቢዎች ላይ ያለውን ችግር ለመፍታትና ገቢ ማስገኛ አገልግሎቱን ለማስፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑንና ከመመሪያ ውጪ ለትርፍ ሰዓት የተከፈለውን ክፍያ ለማስመለስ የሚያስችል ውሳኔ መወሰኑን አመላክተዋል፡፡ ያልተወራረዱ የውሎ አበል ሂሳቦች በአብዛኛው ቀደም ሲል ከነበሩ ዓመታት ተንከባለው የመጡና ከክትትል ማነስ ሳይወራረዱ የቆዩ  መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊዎቹ ችግሩ በአሁን ሰዓት እየተቀረፈ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ ለክልሎች የሚደረገው ድጎማ በወቅቱ ያልተወራረደ መሆኑን ጠቅሰው አንዳንድ ክልሎች ሂሳቦቹን ለማወራረድና አስፈላጊ የአፈጻጸም ሰነዶችን ለማቅረብም ሆነ የአፈጻጸም ሪፖርት ለማቅረብ ፍቃደኛ ያለመሆናቸውና በሰነድ አያያዝና ትክክለኛውን የፋይናንስ ስርዓት በመተግበር  ረገድም ክፍተት መኖሩን ጠቁመው ለቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ ለክልሎች ከሚደረገው ድጎማ ጋር በተያያዘ የሌሎች አካላት ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከርና ኮሚቴ በማቋቋም እንዲሁም ከክልሎች ጋር የመግባቢያ ውል በማድረግ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አቅጣጫ መቀመጡንና ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዝውውር ረገድ የነበሩ ክፍተቶች በአሁን ሰዓት የታረሙ መሆኑን የጠቀሱት የስራ ኃላፊዎቹ በበጀት ዓመቱ በስራ ላይ ያልዋለው በጀት ከአክሱም ሀውልት ጥገና ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቅሰው ቅድመ ክፍያ ተከፍሎ ስራውን ለመጀመር ሂደቱ ቢጀመርም ቀደም ሲል በኮረና ወረርሽኝ በኋላም በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በጀቱን ለመጠቀም ያለመቻሉንና ለጥገናው የተገዙት ንብረቶችም  በአሁን  ሰዓት በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ለማወቅ ያለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በንብረት አያያዝና አጠቃቀም በኩል የታዩት ችግሮች በስራ ክፍሎች አደረጃጀትና አወቃቀር ምክንያት የተፈጠሩና በአሁን ሰዓት የንብረት አስተዳደሩ እራሱን ችሎ እንዲዋቀር በመደረጉ ችግሮቹን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው አንዳዶቹ ከአቅም በላይ የሆኑ በመሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መፍትሔ ለመስጠት እየተሞከረ መሆኑን ገልጸው ድጋፍ የሚያስፈልገውን ድጋፍ በመጠየቅ ችግሮቹን ለመፍታት ቀጣይ ጥረቶች እንደሚደረጉና የሀገሪቱን ቅርሶች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ  ለመያዝም ለዳታ ቤዝ ግንባታ ሂደት የሚረዱ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን አንስተዋል ፡፡ የቱሪዝም ሚኒስተሯ ክብርት አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው የባለስልጣን መ/ቤቱ ችግሮች ስር የሰደዱና አጣዳፊ መፍትሔ የሚፈልጉ በመሆናቸው በአዋጅና በአሰራር ደንቦች ረገድ ያሉ የህግ ክፍተቶችን ከመድፈን ጀምሮ ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረግ ተቋሙ አሁን ካሉበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዲላቀቅ ለማድረግ በሚኒስቴር መ/ቤቱ በኩል እየተደረገ ያለውን ጥረት የበለጠ ለማጠናከር ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል፡፡

በባለስልጣን መ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች የተሰጡትን ምላሾች አስመልክቶ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ በተጋባዥነት የተገኙ የንግድና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ አባላትና በመድረኩ የተሳተፉ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እስተያየቶቻቸውን ሰጥተዋል፡፡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሂሳብ አሠራርና አጠቃቀም እንዲሁም በንብረት አያያዝና አጠቃቀም ረገድ ያሉበት አብዛኛዎቹ ችግሮች አሳሳቢና  በተግባር የሚገለጹ ተመጣጣኝ እርምጃዎችን የሚፈልጉ መሆናቸውን  ጠቁመው ባለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት በተደረገው ኦዲት ተቋሙ ተቀባይነት በሚያሳጣ የኦዲት ግኝት ደረጃ ላይ በመሆኑ የቱሪዝም ሚኒስቴርን ጨምሮ ባለስልጣን መ/ቤቱም ሆነ ሌሎች አካላት የተቋሙን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ከፍተኛ ትኩረትና ርብርብ ማድረግና ወቅቱን የሚመጥኑ የአሠራር  ደንብና መመሪያዎችንም አውጥቶ ባለስልጣን መ/ቤቱን ወደ ተጨባጭ መሻሻልና ለውጥ ሊያሸጋግሩ የሚችሉ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ የኦዲት ግኝቶቹ ከአሠራር ፣ ከህግ ክፍተትና በግዴለሽነት ከሚመነጭ ህገ ወጥ አካሄድ የመነጩ መሆናቸውን የጠቆሙት የቋሚ ኮሚቴ አባላቱና ባለድርሻ አካላቱ በስራ ኃላፊዎቹ የተሰጡት ምላሾች በሚጠበቀው ደረጃ አጥጋቢ ያለመሆናቸውንና አንዳንዶቹ ችግሮችም ለብልሹ አሠራርና ለሙስና የሚያጋልጡ በመሆናቸው ተጠያቂነትን ሊያስከትሉ የሚችሉ መሆናቸውን ተገንዝቦ ችግሮቹን ለመቅረፍ የሚያስችሉና ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ እንዲሁም ቋሚ በሆነ ተቋማዊ  የአሠራር ስርዓት በመመራት በየጊዜው በሚለዋወጡ  አመራሮች ላይ ያልተንጠለጠሉ ህጋዊ አሠራሮችን መከተል እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ባለስልጣን መ/ቤቱ ላለፉት ተከታታይ ዓመታት ያሉበትን የሂሳብ አሠራር እንዲሁም የንብረት አያያዝና አጠቃቀም ችግሮች በሚፈለገው ደረጃ ሳይቀርፍ  መቀጠሉን ጠቁመው ተቋሙን ከሚገኝበት ችግር ለማውጣት የባለስልጣን መ/ቤቱን አመራሮች ያላሰለሰ ጥረትና የቱሪዝም ሚኒስቴርን ጨምሮ የሌሎች ባለድርሻ አካላትን  ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በበጀት ዓመቱ በተደረገው ኦዲትና ቀደም ብሎ በነበሩ ዓመታትም በተደረጉ አዲቶች  የተሰጡ የኦዲት ግኝት አስተያየቶችን በተጨባጭ መተግበር እንደሚገባ የገለጹት ም/ዋና ኦዲተሯ ተከፋይና ተሰብሳቢ ሂሳቦችን በአግባቡና በፋይናንስ መመሪያ መሰረት  መፈጸምና በሂሳብ መዝገብ በመመዝገብ ወቅታዊ ሪፖርት ለሚለከታቸው አካላት ማቅረብ፣ ህጋዊ የበጀት አጠቃቀምና ዝውውርን መተግበር፣ የህግና የመመሪያ ክፍተቶችን በአፋጣኝ በመድፈን ህግና ስርዓት የተከተለ የሂሳብ አሠራር እንዲኖር ማድረግ፣ የወጪና ገቢ ሂሳብ ሰነዶችን በአግባቡ አደራጅቶ መያዝ እና ህጋዊና መመሪያን የተከተለ የንብረት አያያዝና አጠቃቀም ስርዓት መዘርጋት ከተቋሙ የሚጠበቅ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር  መሆኑን ጠቅሰው ተቀባይነት ከሚያሳጣ የኦዲት ግኝት በመውጣት ወደተሻለ ደረጃ መራመድ የሚያስፈልግ መሆኑን በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለና ም/ሰብሳቢዋ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው በባለስልጣን መ/ቤቱ የታዩትን የአሰራር ክፍተቶች ለማረም ተቋማዊ የአሠራር ስርዓት መዘርጋትና የህግና የመመሪያ ክፍተቶችን በመድፈን ለተሻለ ሥራ መዘጋጀት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ተቋሙ አሠራሩን ለማሻሻልና ያሉበትን ችግሮች ለመቅረፍ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የንግድና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርጉ የጠቀሱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢዎች ቀጣይ የሆኑ ክትትልና የአካል ምልከታዎች እንደሚደረጉ ጠቁመዋል፡፡ በመጨረሻም የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ የቱሪዝም ሚኒስቴር እና ባለስልጣን መ/ቤቱ በተሰጡት አስተያየቶች መሰረት እርምጃ ሰለመወሰዳቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት እንዲያደርጉ አሳስበው የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የፍትህ ሚኒስቴር እና የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የባለስልጣን መ/ቤቱን የኦዲት ግኝቶች ለመቅረፍ በሚመለከታቸው ጉዳዮች ዙሪያ አስፈላጊውን ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ተቋሙን ለውጤት የሚያበቃ ተጨባጭ እርምጃ እንዲወስዱ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *