News

በመ/ቤቱ አለም አቀፍ የሴቶች ቀን በተለያዩ ስነስርዓቶች ተከበረ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አመራርና ሰራተኞች የ2017 ዓ.ም አለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች አከበሩ፡፡

በበዓሉ መክፈቻ የተገኙት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ ባስተላለፉት መልዕክት የዘንድሮ አለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ለየት የሚያደርገው የመ/ቤቱን 80ኛ ዓመት የምስረታ መታሰቢያ እያከበርን ባለንበት እና የመ/ቤቱን የህንጻ እድሳት ግንባታ ተጠናቆ ለሥራ ይበልጥ ምቹ የሆነ የሥራ አከባቢ በተፈጠረበት ወቅት ላይ መገኘታችን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ክብርት ዋና ኦዲተሯ አክለውም በዓሉን ስናከብር እንደ ተቋም የመጣውን ለውጥ መፈተሸ፣ ወደፊት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት መስራትና በሥራ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ተልዕኳችንን ለማሳካት ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

አያይዘውም የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማጠናከር እና ያለባቸውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫናዎች ለመቀነስ የተለያዩ ስራዎች በተቋም ደረጃ እየተከናወኑ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

አክለውም መ/ቤቱ በዓለም አቀፍ እና በአገር ደረጃ የወጡ የአካታችነት ድንጋጌዎችን ተግባራዊ ከማድረጉ ባሻገር እነዚህ ድንጋጌዎች በሌሎች ተቋማትም ተግባራዊ ስለመሆናቸው ለመከታተል በተለይ በክዋኔ ኦዲቶች የአካቶ ትግበራ እራሱን የቻለ አንድ የኦዲት መስፈርት በማዘጋጀት እንዲሰራ እየተደረገ መሆኑን ክብርት ዋና ኦዲተር ገልጸዋል፡፡

በመርሀ-ግብሩ ሴቶች ወደ አመራርርነት እንዳይመጡ የሚያጋጥማቸው ተግዳሮቶች እና ሊወሰዱ በሚገቡ የመፍትሄ ሀሳቦች ዙሪያ በመ/ቤቱ በተለያዩ አመራርነት ላይ የደረሱ ሴት ሠራተኞች የህይወት ተሞክሯቸውን ያካፈሉበት የፓናል ውይይትም ተካዷል፡፡

በተጨማሪም የተሻለ የስራ አፈፃፀም ላሳዩ የመ/ቤቱ የሰራተኞች መዝናኛ ክበብ ሠራተኞች እንዲሁም የሴቶች ፎረም እና የሴቶች ብድርና ቁጠባ ማህበር አስተባበሪ ሴት ሠራተኞች እውቅና የመስጠት መርሀ ግብር ተከናውኗል፡፡

የዘንድሮው አለም አቀፍ የሴቶች ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ114ኛ ጊዜ በአገራችን ለ49ኛ ጊዜ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *