News

ሀሮማያ ዩኒቨርስቲ የፋይናንስ አሰራሩን ፈትሾ ማስተካካል እንዳለበት ተገለጸ

የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ያሉበትን በርካታ የፋይናንስና የንብረት አስተዳደር ችግሮች በስፋት በመፈተሽ ማስተካከል እንዳለበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በዩኒቨርሲቲው የ2010 በጀት ዓመት ሂሳብ ላይ ያደረገውን ኦዲት መሰረት በማድረግ ታህሳስ 17 ቀን 2012 ዓ.ም ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ አድርጓል፡፡

ኦዲቱ በዩኒቨርሲቲው ላይ እንዳሉ ካሳያቸው ድክመቶች ውስጥ የፕሮጀክት ሂሳብና የውስጥ ገቢ ሒሳብ ወጪ በሒሳብ ምዝገባው ላይ ተጠቃሎ ስለተመዘገበ መለየት ባይቻልም በወጪ የመዘገበው ብር 6.9 ሚሊዮን በዩኒቨርሲቲው የተጠቃለለ ሂሳብ ውስጥ አለመካተቱና ሪፖርቱ ለገንዘብ ሚኒስቴርም አለመቅረቡ፣ በህግ ስልጣን በተሰጠው አካል የወጣ የክፍያ ተመን ሳይኖር ከብር 8.02 ሚሊዮን በላይ ለዩኒቨርሲቲው መምህራን አለአግባብ የትርፍ ሰዓት ክፍያ መከፈሉ እንዲሁም ወደ ዩኒቨርሲቲው ከሚመጡ ተጋባዥ መምህራን ላይ በህጉ መሰረት መሰብሰብ የሚገባውን ትክክለኛ የገቢ ግብር መጠን ባለመሰብሰብ  የቅድመ ታክስ 2% ብቻ በመቀነሱ 1.08 ሚሊዮን ብር ሳይሰበሰብ መቅረቱ ይገኙበታል፡፡

ከዚህ ሌላም የህክምና መድኃኒቶች፣ መሣሪያዎች የላቦራቶሪ ግብዓቶች ግዥ ሲፈፀም የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ መድኃኒቶቹና ግብአቶች እንደሌሉት ሳያረጋግጥ ከሌሎች የግል አቅራቢዎች የብር 1.7 ሚሊዮን ግዥ ፈፅሞ መገኘቱና አቅራቢዎች በውል መሠረት ግዴታቸውን ሳይፈጽሙ ሲቀሩ በቅጣት መልክ መሰብሰብ የነበረበት የጉዳት ካሳ ብር 822 ሺህ ሳይሰበሰብ መቅረቱ በኦዲቱ ተገኝቷል፡፡

ለአቅራቢዎች በቅድመ ክፍያ የተከፈለና ከመጨረሻ ክፍያ ላይ መቀነስ ሲገባው ያልተቀነሰ ብር 3.05 ሚልየን እንዳለና ቅድመ ክፍያውን ወስዶ ውል ያፈረሰውን አቅራቢ በህግ ለመጠየቅ ዩኒቨርስቲው ጥረት አለማድረጉንም ኦዲቱ አመልክቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በወቅቱ ያልተወራረደ ብር 153.2 ሚሊዮን ተሰብሰቢ ሂሳብ እንዳለና 7.4 ሚሊዮን ብር ለባለመብቱ ያልተከፈለ ገንዘብም እንዳለ ኦዲቱ አሳይቷል፡፡

በንብረት አያያዝ ረገድም በድምሩ ብር 1.5 ቢሊዮን በላይ የሚያወጡ ርክክብ የተደረገባቸው ግንባታዎች የንብረት ገቢ ማድረጊያ ደረሰኝ እንዳልተቆረጠላቸውና በቋሚ ንብረት መቆጣጠሪያ ካርድ ላይም እንዳልተመዘገቡ ኦዲቱ አሳይቷል፡፡

እንደዚሁም አገልግሎት ሳይሰጡ የተቀመጡ፣ በአግባቡ ያልተቀመጡ እንዲሁም በብልሽትና በሌሎች ምክንያቶች አገልግሎት መስጠት የማይችሉና ያልተወገዱ ንብረቶች መኖራቸውን ኦዲቱ አመልክቷል፡፡ በተሽከርካሪ ረገድም 64 መረጃቸው ያልተሟላና የንብረት ገቢ ደረሰኝ ያልተቆረጠላቸው፣ 45 የባለቤትነት መታወቂያ ደብተር በማህደራቸው ያልተያያዘላቸው፣ 17 ተጠግነው አገልግሎት ላይ መዋል ስለመቻላቸው ውሳኔ ያልተሰጠባቸው ተሽከርካሪዎች እንዳሉ  እንዲሁም 1 ካለ አገልግሎት ለ6 ዓመታት የቆመ ተሽከርካሪ መኖሩ፣ 8 ትራክተሮች በብልሽት እንደማይሰሩ እና አራቱ ሞተር የሌላቸው መሆኑ፣ 11 ትራክተሮች ደግሞ ተገቢው መረጃ የሌላቸው መሆኑ በኦዲቱ ተመልክቷል፡፡

በነዚህና በሌሎች ግኝቶች ዙሪያ ስለተወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎች ማብራሪያ እንዲሰጥ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሰቢ የተከበሩ አቶ መሀመድ ዩሱፍ በጠየቁት መሠረት የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከአመዘጋገብ ጋር በተያያዘ በዩኒቨርሲቲው ሂሳብ ውስጥ የሚታየውን 6 ሚሊዮን ብር በተመለከተ ቀድሞ የሂሳብ ምዝገባው በIBEX ስርዓት እንዳልነበረና ከ2010 በጀት ዓመት ወዲህ ምዝገባው በIBEX ተመዝግቦ ችግሩ እንደተፈታና ለገንዘብ ሚኒስቴርም ሪፖርት እንደተደረገ ገልጸዋል፡፡

የትርፍ ሰዓት ክፍያዎችን በተመለከተም ሲከፈል የነበረው በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ካውንስል በማጸደቅ እንደነበረ፣ በኦዲቱ ጊዜ ቃለ ጉባኤ ማቅረብ አለመቻላቸውን በመግለጽ ከ2011 በኋላ ግን በወጣው ተመን መመሪያ መሰረት እየተፈጸመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከተጋባዥ መምህራን መቀነስ ስለነበረበት የገቢ ግብር ሲገልጹም አስቀድሞ ከመምህራኑ ጋር ውል የተገባው 2% ተቀናሽ እንደሚደረግ እንደሆነና ውል ከተገባ በኋላ በመንግሥት 30% እንዲቀነስ መመሪያ እንደተሰጠ ገልፀው ይሁን እንጅ መምህራኑ ባለመስማማታቸው ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት በማቅረብና በማስወሰን ዩኒቨርሲቲው አስቀድሞ የገባውን ውል መሰረት በማድረግ 2% ብቻ ተቀናሽ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የመድኃኒት ግዥንም በተመለከተ የመድኃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ መድኃኒቱ በመጋዘን እንደሌለ አስቀድሞ መጠየቁን ነገር ግን ምላሹን የሚገልጽ ህጋዊ ማረጋገጫ ዩኒቨርስቲው ሳይቀበል ግዥውን መፈፀሙ ትክክል እንዳልነበረ በመቀበል አሰራሩ መስተካከሉን ገልፀዋል፡፡

በቅድሚያ ክፍያ ስለተሰጠው ገንዘብም ከተከፈላቸው ሁለት የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ውስጥ የአንዱ እንደተስተካከለ ገልጸው የሌላኛው ግን ውሉ ፈርሶ ጉዳዩ ወደፍርድ ቤት ስለተመራ በፍርድ ሂደት ላይ እንደሆነና በውሳኔው መሰረት እንደሚፈጸም ተናግረዋል፡፡

በውል መሰረት ግዴታቸውን ካልተወጡ አቅራቢዎች የጉዳት ካሳ ቅጣት ጋር በተያያዘም አቅራቢዎች በጊዜያዊነት ላቀረቡት አቅርቦት ዋናው ርክክብ እስኪፈጸምና የንብረት ገቢ ደረሰኝ እስኪቆረጥ ድረስ በጊዜያዊ መረከቢያ ዩኒቨርስቲው በመረከቡ ምክንያት ቅጣቱን መፈጸም ተገቢ አይደለም በሚል እንዳልፈጸመ ገልጸዋል፡፡

በተሰብሳቢ ሂሳብ በኩል ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ ያሉ ውዝፍ ሂሳቦች እንዳሉና ታሪካቸው የማይታወቅ፣ ሰነድም የሌላቸውና ከማን እንደሚሰሰበሰቡ የማይታወቁ ሂሳቦች ጭምር እንዳሉበት በመግለጽ ዩኒቨርስቲው ሂሳቦቹን በእድሜ የመለየት ስራ ማከናወኑን እንዲሁም ሰነድ ያልተገኘላቸውን ማደራጀቱንና ለገንዘብ ሚኒስቴር ማሳወቁን ነገር ግን የተሰብሳቢው ሂሳብ ባለቤት መገኘት ስላለበት የቆዩ ሂሳቦችን ለማሰረዝ ከዩኒቨርስቲው አቅም በላይ የሆነ ችግር መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡ የሩቅ ጊዜ ሂሳቦችን ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በመነጋገርና ኮንሰልታንት በመቅጠር ለማሰረዝ መታሰቡንና የቅርብ አመታት ሂሳቦችን ግን ተከታትሎ ለማስመለስ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ እስካሁን በተሰራው ስራም በታቀደው መሰረት ባይሆንም 18 በመቶ በላይ ተሰብሳቢ ሂሳብ መቀነሱን ገልጸዋል፡፡

በተከፋይ ሂሳብ ረገድም ከፕሮጀክት ወደ ፕሮጀክት የሚከፈሉ ክፍያዎች እንደነበሩ በመግለጽ ሂሳቡ መቀነሱንና በዚህም 19% ያህሉን መክፈል እንደተቻለ ገልፀዋል፡፡

ካለክፍያ ተመን ስለተከፈሉ የተለያዩ ክፍያዎች ሲገልጹም አንዳንድ የማበረታቻ ክፍያዎች ለተመራማሪዎችና ሌሎች አካላት መከፈላቸውንና ከ2010 አስቀድሞ የክፍያ ተመን መመሪያ ያልነበረ በመሆኑ ሁሉም ዩኒቨርሲቲ በራሱ ተመን ይከፍል እንደነበረ አስታውሰው ዩኒቨርስቲው በአሁኑ ወቅት በመመሪያው መሠረት እየተከፈለ ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን በአካባቢው ከነበረው ፀጥታ መደፍረስ ጋር ተያይዞ ያሉትን ጥበቃዎች በትርፍ ሰዓት ሲያሰራ መቆየቱንና ከመንግስት ጠይቆ የተፈቀደለት የትርፍ ሰአት ክፍያ በቂ ባለመሆኑ በራሱ ከተፈቀደው በላይ መክፈሉን መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

በመጋዘን የተከማቹ ንብረቶችን በተመለከተም እየተገነቡ የነበሩ ህንፃዎች ባለመጠናቀቃቸው ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን ገልጸው ህንፃዎቹ በመጠናቀቃቸው ንብረቶቹ ተገቢውን ግልጋሎት እንዲሰጡ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ የተበላሹ ቁሳቁሶችን፣ አገልግሎት የማይሰጡ ተሽከርካሪዎችንም ለማስወገድ፣ እንዲሁም ለሌሎች ለማስተላለፍ መሰራቱንና በሂደት ላይ ያሉ ጉዳዮች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡ የተሽከርካሪዎችን የጎደሉ መረጃዎች የማሟላት ስራ መሰራቱንና ቀሪ ስራዎችንም ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በህንፃዎች ምዝገባ በኩልም ከ2009 በፊት ህንፃዎች የንብረት ገቢ ደረሠኝ ይቆረጥላቸው እንዳልነበረና ከግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት በመጣ ሰርተፍኬት መሰረት ክፍያ ይፈጸም እንደነበረ ገልፀው ከኦዲቱ በኋላ ግን የንብረት ገቢ ደረሰኝ እየተቆረጠላቸው ክፍያ እየተፈጸመ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ ኦዲቱ ብዙ እንዳስተማራቸው እና ለወደፊቱም ግኝቶቹን በእቅድ ይዘው እንደሚሰሩ የዬኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

በዩኒቨርስቲው የስራ ኃላፊዎች የተደረገውን ገለፃና የኦዲት ግኝቱን መነሻ በማድረግ በቋሚ ኮሚቴው አባላት በኩል ተጨማሪ ጥያቄና አስተያየት ቀርቧል፡፡

በሰጡት አስተያየትም በዋናነት ዩኒቨርሲቲው እንደ አንጋፋነቱ የፋይናንስ ስርአቱ የዘመነ እንደሚሆን ቢጠበቅም በዛ ልክ እየሰራ እንዳልሆነ፣ በንብረት አያያዝና አጠቃቀሙ ላይ መሠረታዊ የሆነ ውሱንነት እንዳለበትና አለአግባብ የተከፈሉ ክፍያዎች ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው በስራ ሀላፊዎቹ ከተሰጡት ምላሾች ውስጥ ተገቢ አይደሉም ባሏቸው አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን ገልፀዋል፡፡ በዚህም የገቢ ግብር 2% የሚሰበሰበው ከነጋዴዎች እንደሆነና ከመምህራኑ መሰብሰብ የነበረበት 35% መሆኑን በመግለጽ ዩኒቨርሲቲው አላግባብ ሳያስከፍል የቀረውን  ገንዘብ መሰብሰብ አለበት ብለዋል፡፡ በጊዜያዊ መረከካቢያ ቅጽ ዩኒቨርሲቲው በተረከባቸው ንብረቶች ላይ የኦዲት ግኝት እንዳልቀረበና ግኝት ሆኖ የቀረበው በርክክብ ሰነዱ ከተቀመጠው የማስረከቢያ ጊዜ በኋላ አዘግይተው ላስረከቡት አቅርቦት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በተሰብሳቢ የተያዘው ገንዘብም ሁሉም ከ1968 ጀምሮ እንደሆነ አስመስሎ ማቅረቡ ትክክል እንዳልሆነ ክቡር ዋና ኦዲተሩ ገልጸው ለአብነት ያህል ከተሰብሳቢው 153 ሚልየን ብር ውስጥ ከ10 አመታት በላይ ሆነው ተሰብሳቢ 32.7 ሚሊዮን ብር (21%) ብቻ መሆኑንና የቀረውም ተሰብሳቢ ገንዘብ በሙሉ እስከ 1968 ዓ.ም ላይደርስ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ተሰብሳቢ ሂሳቡ በቆየ ቁጥር ለመሰብሰብ አስቸጋሪ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ ማወራረድና መሰብሰብ ይገባል ብለዋል፡፡

ክቡር ዋና ኦዲተሩ ከንብረት ጋር ተያይዞ ያለውን ሁኔታ ዩኒቨርሲቲው በአግባቡ ሊያየው እንደሚገባ የገለጹ ሲሆን የጥበቃ ትርፍ ሰዓት ክፍያን በራስ ወስኖ ከመክፈል ይልቅ መዋቅሩ ችግር ካለበት የሚመለከታቸውን አካል ማስፈቀድና መዋቅሩን ማሻሻል ይገባል ብለዋል፡፡ እንደዚሁም ኦዲቱ በናሙና የተሰራ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ይህንን መነሻ በማድረግ ውስጡን በስፋት በመፈተሽ በጥናት ላይ ተመስርቶ በድክመቶቹ ላይ ዘላቂ እርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መህመድ ዩሱፍ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከኦዲቱ በመነሳት የስጋት ምንጩን በጥናት በመለየትና የውስጥ ኦዲት ክፍሉን በማጠናከር በአስቸኳይ ችግሮቹን በማረም ለዋና ኦዲተር መ/ቤት ሪፖርት ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *